ሪፖርት | ዐፄዎቹ ነጥብ ተጋርተዋል

አራት ግቦች በተቆጠሩበት እና ጥሩ የመሸናነፍ ፉክክር ባስመለከተን የምሽቱ ጨዋታ ፋሲል ከነማ እና አዲስ አበባ ከተማ ነጥብ ተጋርተዋል።

ፋሲል ከነማዎች በመጨረሻ ጨዋታቸው ጅማ አባጅፋርን ከረታው ስብስብ ሁለት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም ናትናኤል ገ/ጊዮርጊስ እና ሙጂብ ቃሲምን አስወጥተው በምትካቸው ሱራፌል ዳኛቸው እና ኦኪኪ አፎላቢን ተክተው አስገብተዋል ፤ በአንፃሩ መከላከያን አሸንፈው ወደዚህ ጨዋታ የመጡት አዲስ አበባ ከተማዎች ደግሞ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ መሀመድ አበራን በብዙዓሁ ሰይፉ ተክተው የዛሬውን ጨዋታ አድርገዋል።

ቀዝቃዛ አጀማመር በነበረው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ገና በ6ኛው ደቂቃ ነበር በድንገት የመጀመሪያዋ ግብ የተቆጠረችው ፤ 6ኛው ደቂቃ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ የቀኝ መስመር ተከላካይ የሆነው አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ሪችሞንድ አዶንጎ በፋሲል ከነማ ተጫዋቾች ስህተት ታግዞ በግሩም ሁኔታ በመዞር አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

ገና በማለዳ በተቆጠረችው ግብ መነሻት መምራት የጀመሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ከሪችሞንድ አዶንጎ ውጭ የተቀሩት ተጫዋቾች ወደ ራሳቸው ሜዳ ሸሽተው መጫወታቸውን ተከትሎ ፋሲሎች የተሻለ ኳሱን ተቆጣጥረው ለማጥቃት ጥረት አድርገዋል።

በ18ኛው ደቂቃ ላይ ታድያ ጥረታቸው ፍሬ አፍርቷል ሱራፌል ዳኛቸው ከመሀል ሜዳ ወደ ግራ የሳጥን ጠርዝ ያሻማውን ኳስ አሰጋኸኝ ጴጥሮስ በሁለት አጋጣሚዎች መቆጣጠር ባለመቻሉ የተገኘውን አጋጣሚ ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ግብነት ቀይሮ ቡድኑን አቻ አድርጓል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ በተወሰነ መልኩ አውንታዊ ለመሆን የሞከሩት አዲስ አበባ ከተማዎች ዳግም መሪ ለመሆን ጥረት ያደረጉ ሲሆን በተለይም ከቆሙ ኳሶች አደገኛ ሙከራዎችን ሲያደርጉ ተመልክተናል ፤ በ20ኛው ደቂቃ ሮቤል ግርማ ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም ያሻማውን የቆመ ኳስ ቴዎድሮስ ሀሙ በግንባሩ ገጭቶ የሞከራት እንዲሁም በ31ኛው ደቂቃ ራሱ ሮቤል ግርማ በቀኝ መስመር እጅግ ጠባብ ከሆነ አንግል በቀጥታ ወደ ግብ የላካት እና ሚኬል ሳማኪ ያዳነበት ኳስ አደገኛ አጋጣሚዎች ነበሩ።

በአንፃሩ ከደቂቃ ደቂቃ የጨዋታ ቁጥጥራቸው እያየለ የመጡት ፋሲል ከነማዎች የጠሩ የግብ እድሎችን ግን ለመፍጠር ፍፁም ተቸግረው ያስተዋልን ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ ከግቧ ውጭ ተጠቃሽ የነበረው አጋጣሚም በ33ኛው ደቂቃ ሱራፌል ዳኛቸው ከሳጥን ውጭ በግሩም ሁኔታ የመታው እና ዳንኤል ተሾመ ያዳነበት ኳስ ብቻ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ኦኪኪ አፎላቢ ከሳጥን ውጭ ባደረገው እና ዳንኤል ተሾመ ባደነበት ኳስ አጋማሹን የጀመሩት ፋሲል ከተማዎች በጨዋታው ወሳኙን ሦስት ነጥብ ለማግኘት ከፍተኛ ጥረቶችን ሲያደርጉ ተመልክተናል ፤ ጥረታቸውም በ57ኛው ደቂቃ የመሪነት ግብ አስገኝቶላቸዋል።

አዲስ አበባ ከተማዎች በፋሲል አጋማሽ የቆመ ኳስን ለማጥቃት በቁጥር በርክተው ፋሲል ሳጥን ውስጥ በተገኙበት አጋጣሚ ፋሲሎች በፈጣን የመልሶ ማጥቃት ሱራፌል ዳኛቸው ያደረሰውን ግሩም ኳስ ኦኪኪ አፎላቢ ለራሱም ሆነ ለቡድኑ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሯል።

ከግቧ መቆጠር በኃላ በተወሰነ መልኩ ማጥቃታቸው ጋብ ያለው ፋሲሎች ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ጥረት ከማድረግ ይልቅ ጨዋታውን ይበልጥ ለመቆጣጠር በማሰብ የአጥቂ አማካዩን በዛብህ መለዮን አስወጥተው በምትኩ ሀብታሙ ተከስተን በማስገባት ቀሪዎቹን ደቂቃዎች ለመጫወት መርጠዋል።

በአንፃሩ የአቻነቷን ግብ ማሰስ የጀመሩት አዲስ አበባ ከተማዎች በአውንታዊ ለውጦች ታግዘው በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ማሳየት በጀመሩበት ቅፅበት በ73ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለ ከበደ ከሳጥኑ የቀኝ ወገን ያሻማውን ኳስ ከድር ኩሊባሊ በእጅ መንካቱን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማዎች ያገኙትን የፍፁም ቅጣት ምት ፍፁም ጥላሁን አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

በ76ኛው ደቂቃ ፋሲል ከነማዎች በአምሳሉ ጥላሁን ከሳጥን ውጭ ባደረገው ሙከራ ፈጣን ምላሽ ለመስጠት ተቃርበው የነበሩ ቢሆንም ኳሷ ለጥቂት የግቡን ቋሚ ታካ ወጥታለች።

በተቀሩት ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ከጨዋታው ሦስት ነጥብ ይዘው ለማጥቃት ርብርብ ሲያደርጉ የተመለከትን ሲሆን በተለይም በአዲስ አበባ ከተማዎች በጭማሪ ደቂቃ ሪችሞንድ አዶንጎ እና ቢኒያም ጌታቸው ያደረጓቸው ሙከራዎች እጅግ አደገኞቹ ነበሩ።

ተጨማሪ ግብ ሳይቆጠርበት ሁለት አቻ ከተጠናቀቀው ጨዋታ በኃላ ፋሲል ከነማዎች በ31 ነጥብ 4ኛ ደረጃ ላይ ሲቀጥሉ በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማዎች ደግሞ በ19 ነጥብ ወደ 14ኛ ደረጃ ተንሸራተዋል።