ቅድመ ዳሰሳ | ባህር ዳር ከተማ ከ አርባ ምንጭ ከተማ

የ19ኛ ሳምንት የማሳረጊያ ጨዋታ ላይ ያተኮረው ዳሰሳችን እንደሚከተለው ተሰናድቷል።

በዘንድሮ የውድድር ዓመት የመጀመሪያው የፎርፌ ውጤት ያገኘ ቡድን የሆነው ባህር ዳር ከተማ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ያገኘውን ሦስት ነጥብ ዳግም ለማሳካት እና ከደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ ወደ 6ኛ ደረጃ ከፍ ለማለት ወደ ሜዳ ሲገባ ያለፉትን ስምንት ጨዋታዎች ያልተረታው አርባ ምንጭ ከተማ በበኩሉ በአስቆጪ ሁኔታ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር የጣለውን ሁለት ነጥብ እያሰላሰለ በጨዋታው ያሳየውን ከፍተኛ የማሸነፍ ፍላጎት ለመድገም እና ድል ለማሳካት ጨዋታውን ይቀርባል።

በአሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ የሚመራው ባህር ዳር ከተማ ባሳለፍነው ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ ጋር ሁለት አቻ ቢለያይም ተጋጣሚው በጨዋታው ቀይሮ ወደ ሜዳ ካስገባቸው ተጫዋቾች ጋር በተያያዘ በተነሳ ክስ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎሎ አግኝቷል። ይህ ቢሆንም ግን ቡድኑ በጨዋታው ያሳየው እንቅስቃሴ ካለፉት ጨዋታዎች ከፍተኛ መሻሻል የተስተዋለበት ነበር። በተለይ ተጫዋቾቹ የነበራቸው የተነሳሽነት ስሜት እና ፍላጎት ቀድሞ ግብ ተቆጥሮባቸውም አልቀዘቀዘም ነበር። ማሸነፍ ናፍቆት የነበረው ቡድኑ በጨዋታው ከወትሮ በተለይ ሁኔታ አምስት የጠራ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን በመጠቀም በላይኛው ሜዳ በተደጋጋሚ በመገኘት በድምሩ 18 የግብ ማግባት ሙከራዎችን አድርጓል። ይህ ደግሞ ቡድኑ ከወገብ በላይ ይታይበት የነበረውን የወረደ እንቅስቃሴ በመጠኑ አስተካክሎ እንደመጣ ይጠቁማል። በነገው ጨዋታም ይህ ተሻሽሎ ይቀርባል ተብሎ ሲጠበቅ በዋናነትም ከቅጣት ተመልሶ ጥሩ የተንቀሳቀሰው ግርማ ዲሳሳ በሚሰለፍበት መስመር (ግራ) ላይ ያተኮረ ጥቃት ለመሰንዘር እንደሚጥሩ ይገመታል።

ባህር ዳር በወልቂጤው ጨዋታ የተሻሻለው ከወገብ በላይ ብቻ ሳይሆን በታችም ነው። እርግጥ ቡድኑ በቆሙ ኳሶች ሁለት ግቦችን ቢያስተናግድም በክፍት ጨዋታ ከ3 ጊዜ በላይ ጥቃት አልተሰነዘረበትም። መረሳት የሌለበት ግን ወልቂጤ ቀድሞ ግብ በማስቆጠሩ ዘለግ ያሉትን ደቂቃዎችን ወድድ ብሎ ለመከላለል በመፈለጉ ማጥቃቱን በሚገባ አለመከወኑ ነው። የነገው ተጋጣሚው አርባ ምንጭ ከተማም በክፍት ጨዋታ በተደጋጋሚ የተጋጣሚን ግብ ክልል የሚጎበኝ ባይሆንም በሽግግሮች ግን ያለው ስልነት ለጣና ሞገዶቹ ከባድ መሆኑ አይቀሬ ነው። በዚህም በሁለቱ መስመሮች የሚደረጉትን ፈጣን የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴዎች እንዲሁም ተሻጋሪ ኳሶችን በአግባቡ መመከት ይገባቸዋል።

በቀላሉ የማይሸነፈው የአሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቡድን አርባ ምንጭ ከተማ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች የዓመቱ ምርጥ ብቃቱ ላይ ያለ ይመስላል። ከሁለቱ ደግሞ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር የነበረው እንቅስቃሴ እጅግ ምርጥ ነበር። ከጠቀስነው ጨዋታ በፊት በተደረጉት 17 ጨዋታዎች ከሁለት ጎል በላይ አስቆጥሮ የማያውቀው ቡድኑ ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት አላቸው ተብሎ ከሚታሰቡ ቡድኖች መካከል አንዱ የሆነው ሀዲያ ላይ አራት ግቦችን ማስቆጠሩ ትልቅ ሙገሳ የሚያሰጠው ነው። ግብ ብቻ ሳይሆን ለመጀመሪያ ጊዜ 26 ሙከራዎች ያደረገበት ጨዋታ መሆኑ እጅን አፍ ላይ የሚያስጭን ነው። በዚህ ያደገ እንቅስቃሴ ሐት-ሪክ ሰርቶ ተጎድቶ የወጣው አህመድ ሁሴን ተጠቃሽ ቢሆንም በነገው ጨዋታ አለመኖሩ ግን ትልቅ ማጣት ነው። እርሱ 72ኛው ደቂቃ ላይ ተጎድቶ ከወጣ በኋላ የታየው የቡድኑ እንቅስቃሴ ደግሞ እጅግ የወረደ በመሆኑ መሻሻል አለበት።

ባሳለፍነው ሳምንት እስከ 80ኛው ደቂቃ ድረስ 4ለ1 እየመራ የነበረው ቡድኑ እብደት በተሞላባቸው የመጨረሻ ደቂቃዎች ሦስት ግቦችን አስተናግዶ በእጁ የገባውን ሦስት ነጥብ ማጣቱ የሚያስቆጨው ይመስላል። ለወትሮ ጠጣር የነበረው የኋላ መስመርም በጥቂት ደቂቃዎች ተከፋፍቶ መታየቱ የሚያስገርም ነው። ነገ የሚገጥመው ባህር ዳር ደግሞ ፈጣን እና ስል አጥቂዎችን ስለሚይዝ መሰል ስህተቶችን ከደገመ ዋጋ መክፈሉ አይቀርም። ከዚህ ውጪ ግን ከላይ እንደገለፅነው የባህር ዳር የኋላ መስመር በወልቂጤው ጨዋታ መሻሻል ቢያሳይም በደንብ ከተፈተነ እንከኖች የማይጠፉበት በመሆኑ የኳስ ምስረታቸውን ለማጨናገፍ እና ለስህተት እንዲዳረጉ ማድረግ ዋጋ ሊያስገኝ ይችላል።

ባህር ዳር ከተማ እንደ ባለፈው ሳምንት ሁሉ ምንም የጉዳት እና የቅጣት ዜና የለበትም። አርባ ምንጭ ከተማ ግን አጥቂዎቹ ኤሪክ ካፓይቶ እና አህመድ ሁሴንን በጉዳት አያገኝም።

እርስ በርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹ ለመጀመርያ ጊዜ የተገናኙት በዚህ ዓመት ሲሆን አርባምንጭ 2-1 ማሸነፉ ይታወሳል።

ግምታዊ አሠላለፍ


ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ፋሲል ገብረሚካኤል

መሳይ አገኘሁ – ፈቱዲን ጀማል – መናፍ ዐወል – ሔኖክ ኢሳይያስ

ፍፁም ዓለሙ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ፉዐድ ፈረጃ

ዓሊ ሱሌይማን – ኦሴ ማውሊ – ግርማ ዲሳሳ

አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ወርቅይታደስ አበበ – አሸናፊ ፊዳ – ማርቲን ኦኮሮ – ተካልኝ ደጀኔ

ሙና በቀለ – አቡበከር ሸሚል – እንዳልካቸው መስፍን – ፀጋዬ አበራ

በላይ ገዛኸኝ – ሀቢብ ከማል

ያጋሩ