ቅድመ ዳሰሳ | ሀዋሳ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ

የ19ኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ጨዋታዎች ነገ ሲቀጥሉ በቅድሚያ በሚደረገው ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።

ከቡድኖቹ ስብስብ እና አጨዋወት አንፃር ጥሩ የማጥቃት ምልልስ ልንመለከትበት የምንችለው የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ በደረጃ ሰንጠረዡ ለሚኖራቸው መሻሻልም ወሳኝ ይሆንላቸዋል። ሀዋሳ ከተማ ከበላዩ ያሉት ቡድኖች ቀድመው ጨዋታቸውን ያደረጉ ሲሆን ይህንን ተከትሎ ወደ አምስተኛ ደረጃ የተንሸራተተበትን ሁኔታ የነገውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ ወደ ሁለተኝነት በመምጣት ሊቀለብሰው ይችላል ፤ ይህ ከሆነም ከመሪው ጋር ያለው ልዩነት ወደ ሰባት ይቀንሳል። በመጨረሻው ጨዋታው ፎርፌ የተሰጠበት ወልቂጤ ከተማም ከ10ኛ ወደ 6ኛ ደረጃ የሚያመጣው የነጥብ ድምር ላይ ለመድረስ የሚያስችለውን ጨዋታ ነው የሚያደርገው።

ጨዋታው ከታክቲካዊ ጉዳዮች ውጪ በሥነልቦናው ረገድ ቡድኖቹ የሚኖራቸው አቀራረብ ካሳለፉት ሳምንት አንፃር ትኩረትን ይስባል። ሀዋሳ ራሱን በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ካገኘ በኋላ በተከታታይ አምስት ጨዋታዎች ሽንፈት ሳያስተናግድ ቆይቶ ነው በ18ኛው ሳምንት የወንድማማቾች ደርቢ በሲዳማ ቡና የተረታው። ቡድኑ ከዛ ቀደመም ከቅርብ ተፎካካሪው ወላይታ ድቻ ነጥብ መጣሉ ሲታውስ በሰንጠረዡ ያላይኛው ክፍል በሚደረጉ ወሳኝ እና የፉክክር ሚዛኑን በሚቀይሩ ጨዋታዎች ላይ ሙሉ ነጥብ አለማሳካቱ ያለበት የአዕምሮ ጥንካሬ ለዋንጫ ፉክክር ይመጥን እንደሆነ ጥያቄ ያሰነሳበት ነበር። በስብስብ የዕድሜ እና የብቃት ስብጥር ለዋንጫ መፋለም የማይበዛበት ሀዋሳ ከተማ በሥነልቦናውም ተመሳሳይ ደረጃ እንዳለው ለማሳየት ወልቂጤ ከተማን በመርታት በፍጥነት ወደ ድል አድራጊነት መመለስ ይጠበቅበታል።

በሌላ በኩል ሜዳ ላይ በሚያሳየው እንቅስቃሴ ጥሩ ሁኔታ ላይ የሰነበተው ወልቂጤ ከተማ በተለይም በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታዎቹ የአስተዳደራዊ ጉዳዮች ትኩሳት ተፅዕኖ አሳድሮበት ተመልክተናል። አራት ነጥብ ባሳካባቸው ጨዋታዎች ሁለቴ ክሶች ሲያገኙት የመጨረሻው የባህር ዳር ከተማ የአቻ ውጤት ወደ ፎርፌ ተቀይሮ አንድ ነጥብ እና ሦስት የግብ ልዩነት አሳጥቶታል። በመሆኑም ነገ ከዚህ ውጣ ውረድ መልስ ወደ ሜዳ የሚገባው ወልቂጤ ከተማ የሚኖርበት የተነሳሽነት ደረጃ ጨዋታው ላይ ትልቅ ተፅዕኖ ይኖረዋል። ከአንድ ቀን የልምምድ ማቆም በኋላ ወደ ዝግጅት የተመለሱት የቡድኑ ተጫዋቾች ከክለቡ አስተዳደሮች ጋር ባደረጉት ውይይት ወደ ዝግጅት መመለሳቸው የተሰማ ሲሆን ሁኔታው የሚፈጥርላቸው የተነሳሽነት ደረጃ በሜዳ ላይ የሚንፀባረቅበት መንገድ በነገው ጨዋታ ይጠበቃል።

የሀዋሳ ከተማ እንደተጋጣሚው ሁኔታ በኳስ ቁጥጥር ድርሻው ላይ የሚኖረው ፍላጎት በየጨዋታው ሲለያይ ይስተዋላል። ከዚህ አንፃር ቡድኑ ነገ ለመልሶ ማጥቃት ያደላ አቀራረብ እንደሚኖረው ይጠበቃል። በዚህ ሂደት በሲዳማው ጨዋታ የአማካይ ክፍሉን ሚዛን አጥቶ የነበረው ሀዋሳ ወንድምአገኝ ኃይሉን መልሶ ማግኘቱ የማጥቃት ሽግግሩ ፍጥነት መነሻቸውን ከመሀል ባደረጉ የመጨረሻ ኳሶች እንዲታገዝ ያደርገዋል። ሀዋሳ ይህንን ለማስፈፀም በፊት አጥቂዎቹ ፍጥነት ላይ እምነት ቢኖረውም የተከላከይ ክፍሉ ሁኔታ ግን የወልቂጤን አጥቂዎች ለመቆጣጠር እንዳይቸገር ያስጋዋል። በመጨረሻ ሁለት ጨዋታዎች ጎላቸውን አለማስደፈር የተሳናቸው ኃይቆቹ በሰንጠረዡ አናት ካሉ ተፎካካሪዎች ውስጥ በርካታ ግቦች በማስተናገድ ቀዳሚ መሆነቻውን (ከፋሲል ከነማ ጋር በእኩል 18 ግቦች) ስንመለከትም ነገ ቡድኑ የተከላካይ ክፍሉን በእርግጠኝነት ወደ መሀል ሜዳ አስጠግቶ ከመጫወት ይልቅ አቋቋሙን ወደ ራሱ ሜዳ ፈቀቅ አድርጎ በቀጥተኛ ኳሶች መውጣትን ሊመርጥ እንደሚችል ይገመታል።

ወልቂጤ ከተማ ሜዳ ላይ ተሻሽሎ ከታየባቸው ነጥቦች አንዱ የጌታንህ ከበደ እና የጫለ ተሺታ ጥምረት ነው። ሰራተኞቹ ከአሰልጣኝ ተመስገን ዳና መምጣት በኋላ እንደቡድን ከኳስ ጋር እና ያለኳስ ጥሩ መሻሻሎችን ሲያሳዩ በተናጠል የታዩ መነቃቃቶችም የሁለቱን ተጫዋቾች ወቅታዊ ሁኔታ ይገልፀዋል። ግብ በማስቆጠር እና በማመቻቸት በተደጋጋሚ ስማቸውን ማስፈር የቻሉት ተጫዋቾቹ ቡድኑ ወደ ማጥቃት ሽግግር ውስጥ ሲገባ ያላቸው መናበብ በነገው ጨዋታም ልዩነት ሊፈጥር ይችላል። ከዚህ በተጨማሪ ከኳስ ጋር ይበልጥ ነፃነት ያገኘው ዋናው የፈጠራ ምንጭ አብዱልከሪም ወርቁም ከሀዋሳው አቻው ወንድምአገኝ ጋር የሚገናኝበት የመሀል ሜዳ ፍልሚያ ተጠባቂ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ በፎርፌ በተቋጨው የባህር ዳሩ ጨዋታ ቡድኑ በቆሙ ኳሶች ላይ ያሳየው አፈፃፀምም እንዲሁ ለነገው ጨዋታ ግብዓት የሚሆን ነው። በሌላኛው ጫፍ ግን እንደተጋጣሚው ሁሉ ወልቂጤም ግቡን ባለማስደፈር በኩል ያለበት ድክመት በግልፅ የሚታይ ነው። ወልቂጤ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ይህንን ማድረግ አለመቻሉ ነገም የሀዋሳን ፈጣን ጥቃቶች ስለመቋቋሙ በሙሉ ልብ ለበመናገር አዳጋች ያደርገዋል።

ሀዋሳ ከተማ አዲስዓለም ንጉሴን በአራት ጨዋታዎች ቅጣት ሲያጣ ወንድምአገኝ ኃይሉን ከቅጣት መሀመፍ ሙንታሪን ደግሞ ከጉዳት መልስ ያገኛል። በወልቂጤ በኩል የተሰማ የቅጣትም ሆነ የጉዳት ዜና የለም።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ባሳለፍነው የውድድር ዓመት ሁለቱን ቡድኖች ለመጀመሪያ ጊዜ ያገናኙባቸው ሁለት ጨዋታዎች በተመሳሳይ ሁኔታ ያለግብ ሲጠናቀቁ በዘንድሮው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ ወልቂጤ ከተማ 1-0 ማሸነፍ ችሏል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ሀዋሳ ከተማ (3-4-3)

መሀመድ ሙንታሪ

ፀጋአብ ዮሐንስ – ላውረንስ ላርቴ – ፀጋሰው ድማሙ

ዳንኤል ደርቤ – ወንድምአገኝ ኃይሉ – በቃሉ ገነነ – መድሃኔ ብርሃኔ

ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ

ወልቂጤ ከተማ (4-4-2 ዳይመንድ)

ሮበርት ኦዶንካራ

ተስፋዬ ነጋሽ – ዳግም ንጉሴ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ

በኃይሉ ተሻገር – ሀብታሙ ሸዋለም – ሙሉጌታ ወልደጊዮርጊስ – አብዱልከሪም ወርቁ

ጌታነህ ከበደ – ጫላ ተሺታ

ያጋሩ