ሪፖርት | አርባምንጭ ወደ 7ኛ ደረጃ ከፍ ብሏል

አርባምንጭ ከተማ በሀቢብ ከማል ድንቅ የመጀመሪያ አጋማሽ ጎል ባህር ዳር ከተማን 1-0 አሸንፏል።

ባህር ዳር ከተማ ከወልቂጤው የፎርፌ ድል አንፃር መሳይ አገኘሁ ፣ ሄኖክ ኢሳይያስ እና አደም አባስን በአህመድ ረሺድ ፣ አብዱልከሪም ኒኪማ እና ዓሊ ሱለይማን በመተካት ጨዋታውን ጀምሯል። ከ4-4ቱ ውጤት የተመለሱት አርባምንጮች ደግሞ ጉዳት የገጠመው አህመድ ሁሴን እና አሸናፊ ፊዳን በሀቢብ ከማል እና ፍቃዱ መኮንን ለውጠው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ጨዋታው በጀመረበት ቅፅበት ሁለቱም ወደ ጎል ለመድረስ ፈጠን ያለ እንቅስቃሴ ለማድረግ ቢጥሩም ደቂቃዎች ሲሄዱ እየተቀዛቀዘ መጥቷል። አመዛኙን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የያዙት ባህር ዳር ከተማዎች ወደ አርባምንጭ አጋማሽ በሚደርሱባቸው አጋጣሚዎች የቅብብል ጥራት ማነስ ሙከራዎችን ከማረግ አግዷቸዋል። ቡድኑ ባደረገው የተሻለ ሙከራ 10ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ የተሻማውን ኳስ ኦሴ ማዉሊ ከአርባምንጭ ተከላካዮች ጋር በመፋለም ወደ ግብ አፋፍ ቢያደርሰውም ዓሊ ሱለይማን ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ለጥቂት በተከላካዮች ጥረት ድኗል።

አርባምንጭ ከተማዎችም የባህር ዳርን የኳስ ፍሰት አደጋ መቀነስ ቢችሉም ፍቃዱ መኮንን ያነጣጠሩ ቀጥተኛ ኳሶቻቸው በበቂ ሁኔታ ስጋት የሚፈጥሩ አልሆኑም። 17ኛው ደቂቃ ላይ ብቻ ፍቃዱ ከኋላ ከተጣለ ረጅም ኳስ የዘጋጀውን ሀቢብ ከማል ባይጠቀምበትም መልሶ በማግኘት ከሳጥን ውስጥ ያደረገው ሙከራ በፋሲል ገብረሚካኤል ድኖበታል።

ጨዋታው በሚቆራረጡ የማጥቃታ ጥረቶች ቀጥሎ አጋማሹ ያለግብ ሊጠናቀቅ ነው ተብሎ ሲጠበቅ 39ኛው ደቂቃ ላይ ሀቢብ ከማል የጨዋታውን መቀዛቀዝ የምታስረሳ ድንቅ ግብ አስቆጥሯል። ጥሩ ሲንቀሳቀስ ከነበረው ፍቃዱ ከግራ መስመር የደረሰውን ኳስ በተከላካዮች መሀል በደረቱ አብርዶ ዞሮ አክርሮ በመምታት የፋሲል መረብ ላይ አሳርፎታል።

ከግቡ በኋላ ጨዋታው በተለየ ሁኔታ ሲጋጋል ባህር ዳሮች በዓሊ ሱለይማን እና ፍፁም ዓለሙ ከሳጥኑ መግቢያ ላይ የተሻሉ ሙከራዎችን ሲያደርጉ አርባምንጭ ከተማም ጥሩ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን ፈጥረው ታይተዋል።

ከዕረፍት መልስ ጨዋታው የተሻለ ንቃት ታይቶበታል። የኳስ ፍሰቱ በፈለገው መጠን ባይሳለጥም ባህር ዳር የሜዳውን ስፋት ይበልጥ ጥቅም ላይ በማዋል ወደ አርባምንጭ ሜዳ በመግባት መጫወት ጀምሯል። 50ኛው ደቂቃ ላይ ግርማ ዲሳሳ በግራ መስመር በጥልቀት ገብቶ ያደረሰውን ኳስ ፍፁም ከሳጥን ውስጥ ሞክሮ በሳምሶን አሰፋ ድኖበታል። አርባምንጮችም ከኳስ ውጪ ወደ ኋላ ይሳቡ እንጂ የመልሶ ማጥቃት ቅፅበቶችን ይጠባበቁ ነበር። 55ኛው ደቂቃ ላይ ፍቃዱ ከሳጥን ውጪ ሞክሮት በግቡ አናት የወጣው ኳስ ቀዳሚው የቡድኑ ሙከራ ሆኗል።

የጣና ሞገዶቹ ለግብ በቀረቡበት የ60ኛ ደቂቃው አጋጣሚ የፉዓድ እና የፍፁም ጥምረት በግራ መስመር በሰነዘረው ጥቃት ፉዓድ ወደ ግብ የላከው ኳስ በአርባምንጮች ርብርብ ድኗል። ባህርዳሮች ግብ ለማግኘት አርባምንጮች ደግሞ ውጤት ለማስጠበቅ የሚረዱ ቅያሪዎችን አድርገው ሲቀጥሉ የባህር ዳሮች ማጥቃት ከተሻጋሪ ኳሶች መምጣት ጀምሯል። 74ኛው ደቂቃ ላይ ፍቅረሙካኤል ዓለሙ ከግራ መስመር ወደ ሳጥን ያደረሰው ኳስ የተሻለ የማጥቃት ዕድል ቢፈጥርም ተቀይሮ የገባው ሣለአምላክ ተገኘ በግንባሩ ሊደርስበት አልቻለም። እንዲሁ ከአራት ደቂቃዎች በኋላ ሣለአምላክ ከቀኝ ያሻገረውን ኳስ ማዉሊ በግንባር ገጭቶ ወደ ወጥቶበታል።

ጨዋታው በጉሽሚያዎች ታጅቦ እስከፍፃሜው ሲዘልቅ የባህር ዳር ከተማዎች የመጨረሻ ደቂቃ ጫና የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በቂ አልሆነም። የተሻለ በሚባል ሙከራ 86ኛው ደቂቃ አለልኝ አዘነ ከሳጥን ውጪ አክርሮ ቢመታም ጥሩ አቋቋም ላይ የነበረው ሳምሶን ተረጋግቶ ይዞታል። ጨዋታው ወደ ጭማሪ ደቂቃ ሲያመራ ሁለቱም ቡድኖች ኳስ እና መረብን ለማገናኘት ከጫፍ ደርሰው ነበር። በላይ ገዛኸኝ የሙና በቀለን የማዕዘን ምት በተከላካዮች መሀል ሳይታሰብ ጨርፎ ፋሲል ለጥቂት ሲያድንበት በሌላኛው ጫፍ ማዉሊ ከፍፁም የግራ ወገን የቅጣት ምት በተሻገረለት ኳስ ያደረገው የግንባር ሙከራ በሳምሶን ተጨርፎ ወጥቶበታል። ጨዋታውም በአዞዎቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

በውጤቱ አርባምንጭ ከተማ ነጥቡን 26 አድርሶ 7ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ 26 ላይ የቀረው ባህር ዳር ከተማ ወደ 9ኛነት ተንሸራቷል።