ጎፈሬ ከወላይታ ድቻ ጋር የትጥቅ አቅርቦት ስምምነት ፈፀመ

ሀገር በቀሉ የስፖርት ትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ ለወላይታ ድቻ የመጫወቻ ትጥቅ እንዲሁም የደጋፊዎች መለያን ለማቅረብ ተስማምቷል።

በሁለቱም ፆታዎች ከዋናው የሊግ እርከን እስከ ታችኞቹ ውድድሮች ድረስ በርካታ ቡድኖችን በምርቶቹ እያደመቀ የሚገኘው ሀገር በቀሉ የትጥቅ አምራች ተቋም ጎፈሬ በትናንትናው ዕለት በቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እየተሳተፈ ከሚገኘው ወላይታ ድቻ ጋር በትጥቅ አቅርቦት ስራዎች ላይ ስምምነት ፈፅሟል።

ቦሌ በሚገኘው የጎፈሬ ዋና ቢሮ የተቋሙ መስራች እና ሥራ-አስኪያጅ አቶ ሳሙኤል መኮንን እንዲሁም የወላይታ ድቻ ሥራ-አስኪያጅ አቶ ወንድሙ ሳሙኤል ተገኝተው ስምምነታቸውን በፊርማቸው ካፀኑ በኋላ ይፋ አድርገዋል።

የበርካታ ደጋፊዎች ባለቤት የሆነው ወላይታ ድቻ በአሁኑ ሰዓት በሊጉ የዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኝ ሲሆን በርካታ ተጓዥ ደጋፊዎቹም ወደ ሀዋሳ፣ ድሬዳዋ እንዲሁም አዳማ አቅንተው ከቡድናቸው ጎን መሆናቸውን ሲገልፁ እንታዘባለን።

 

በርካቶቹ ደጋፊዎች ደግሞ የመለያ ጥያቄዎችን ሲያቀርቡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ስንሰማ የነበረ ሲሆን ክለቡም ይህንን የደጋፊዎችን ጥያቄ ለመመለስ ከጎፈሬ ጋር ንግግሮችን ሲያደርግ ከቆየ በኋላ ትናንት ቀትር ስምምነት በመፈፀም ምላሽ ለመስጠት ተንቀሳቅሷል።

ስምምነቱን በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የሁለቱ አካላት ስራ አስኪያጆች በዚህ ዓመት ለደጋፊዎች እስከ 10 ሺ መለያ ድረስ ለማቅረብ እንደታሰበ አመላክተውናል። በተለይ አቶ ወንድሙ “የክለባችን ደጋፊዎች ብዙ ናቸው። ደጋፊዎቻችን ደግሞ መለያ ይፈልጋሉ። አሁን ለስምምነት እስከ 10 ሺ ድረስ እንበል እንጂ እያየን የምንጨምራቸው ነገሮች አሉ። ጎፈሬ መለያዎችን ብቻ አይደለም የሚያቀርብልን። ስካርቮች፣ ፎጣዎች፣ ኮፍያዎች እና ሌሎች ድጋፍ መስጫ ምርቶችንም ያቀርብልናል። ይሄ ለደጋፊዎቻችን ትልቅ ነገር ነው።”

አቶ ወንድሙ አያይዘው መለያዎቹ የክለቡ እና የጎፈሬ አርማ የሚያርፍባቸው በመሆኑ ደጋፊዎች ከህገ ወጦች በመጠበቅ በተገቢ ሁኔታ ዋናውን መለያ እንዲገዙ መልዕክት አስተላልፈው መለያዎቹን ህገ ወጥ በሆነ መንገድ ለማሰራጨት የሚሞክሩ አካላት ላይ ክትትል ተደርጎ እርምጃ እንደሚወሰድ በአፅንኦት ተናግረዋል።

አቶ ሳሙኤል በበኩላቸው “ወላይታ ድቻ የራሱ መገለጫ የሆነውን ቀለም ይዞ እንዲቀጥል በዲዛይኑ ላይ ሞክረናል። የክለቡ የቅፅል ሥም የጦና ንቦቹ ነው። ይህንንም ታሳቢ ባደረገ መልኩ በመለያዎቹ ላይ የንብ ማር እንጀራን የሚወክል ነገር አስገብተናል።” ካሉ በኋላ የደጋፊዎች መለያን ለክለቡ ሲያቀርቡ ለቡድኑ ደግሞ ሁለት አይነት የመጫዎቻ ትጥቅ በነፃ እንደሰጡ አመላክተዋል።

የደጋፊዎቹ መለያ በቅርብ ጊዜ ለገበያ እንደሚቀርቡ ሲገለፅ ቡድኑም ከዚህ በኋላ ሜዳ ላይ ጎፈሬ ያቀረበለትን ምርት ብቻ እንደሚጠቀም ተጠቁሟል።