የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፪) – ተጫዋች ትኩረት

ሁለተኛው ትኩረታችን የሚሆነው የጨዋታ ሳምንቱ የታዘብናቸው ትኩረት የሳቡ ተጫዋቾች ይሆናሉ።

👉 ደምቆ የዋለው ክሌመንት ቦዬ

ጋናዊው ግብ ጠባቂ ወደ ኢትዮጵያ እግርኳስ ዳግም ከተመለሰ በኋላ ምናልባትም ምርጡን የጨዋታ ዕለት በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ሲጫወት አሳልፏል ብንል ማጋነን አይሆንም።

ከዚህ ቀደም በደደቢት ቆይታ የነበረው ክሌመንት ቦዬ ከጥቂት ዓመታት የኢትዮጵያ ውጪ ቆይታ በኋላ ዳግም በክረምቱ የዝውውር መስኮት አዲስ አዳጊው መከላከያን በመቀላቀል በሊጉ ዳግም እየተመለከትነው እንገኛለን። የአሁኑን የጨዋታ ሳምንት ጨምሮ ቡድኑ ባደረጓቸው የ1710 ደቂቃ ጨዋታዎች በሙሉ ተሳትፎ ማድረግ ቢችልም ከአሉታዊ ጉዳዮች ባለፈ እስካሁን በበጎ ጎኑ ርዕሰ ዜናዎችን መፍጠር ሳይችል ቆይቷል።

ተደጋጋሚ የጊዜ አጠባበቅ ስህተቶችን በመስራት እንዲሁም በሌሎች መሰረታዊ የግብ አጠባበቅ ስህተቶችን በመፈፀም በርካታ ትችቶችን ሲያስተናግድ የቆየው ግብ ጠባቂው በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ቡድኑ ከቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ነጥብ እንዲወስድ በማስቻሉ ውዳሴዎች እየተዥጎደጎዱለት ይገኛል።

በጨዋታው ቅዱስ ጊዮርጊሶች እንደነበራቸው ብልጫ ጥቂት ኳሶችን ከክፍት ጨዋታ እንዲሁም ተደጋጋሚ ሙከራዎችን ደግሞ ከቆሙ ኳሶች መነሻቸውን ባደረጉ ሙከራዎችን የመከላከያን ግብ ቢፈትሹም ግብ ጠባቂው ክሊመንት ቦዬ የሚቀመስ አልነበረም። በአስደናቂ ቅልጥፍና ኳሶችን ማምከን የቻለው ግብ ጠባቂው በተለይ የፍሪምፖንግ ሜንሱን ከቅርቡ ቋሚ የገጨውን እንዲሁም በጨዋታው መገባደጃ ላይ ከምኞት ደበበ ያዳነቸው ኳሶች እጅግ የላቁት አጋጣሚዎች ነበሩ።

ከጨዋታው በኋላ ከሱፐር ስፖርት ጋር ቆይታን ያደረገው ግብ ጠባቂው ሁሌም ቢሆን ከጨዋታ ጨዋታ ስመሻሻል ጥረት እንደሚያደርግ እና በቀጣይ እስከ ውድድሩ መጨረሻ ራሱን በማሻሻል የተሻለ ብቃት ለማሳየት ጥረት እንደሚያደርግ ተናግሯል።

👉 ባለ ሐት-ትሪኩ ሳላዲን ሰዒድ

ይገዙ ቦጋለ ላይ ጥገኛ ይመስል የነበረው የሲዳማ ቡና ማጥቃት አሁን ላይ ሁነኛ አማራጭ በሳላዲን ሰዒድ ያገኘ ይመስላል።

ከ18ኛ ሳምንት መጠናቀቅ በኃላ 21 ግቦችን ማስቆጠር የቻሉት ሲዳማዎች ከእነዚህ ግቦች ውስጥ 43%(9 ግቦች) የሚሆነው የተቆጠሩት በይገዙ ቦጋለ ነበር ይህም ቡድኑ ይገዙ ላይ ስለነበረው ጥገኛ ማሳያ ነበር።

ታድያ በውድድር ዘመኑ አጋማሽ የዝውውር መስኮት ሲዳማ ቡናን የተቀላቀለው ሳላዲን ሰዒድ ለ134 ደቂቃ በዘለቁት የመጀመሪያ ሁለት ጨዋታዎች ቆይታ ግብ የማስቆጠርያ መንገዱን ሲፈልግ ቆይቶ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ቡድኑ ሰበታ ከተማን ሲረታ ሐት-ትሪክ በመስራት ለሲዳማ ቡና የዋንጫ ህልም ተስፋን ፈንጥቋል።

ገና በ43ኛው ሰከንድ በአንተነህ ተስፋዬ ስህተት ታግዞ አንድ ያለው ሳላዲን በ28ኛው እና በ72ኛው ደቂቃ በሰበታ ተከላካዮች የአደረጃጀት ስህተት ታግዞ ሁለት ተጨማሪ ግቦችን በማከል አስደናቂ ምሽትን ማሳለፍ ችሏል።

ባለፈው የውድድር ዘመን ግንቦት 14 ቅዱስ ጊዮርጊስ አዳማ ከተማን 2-0 በረታበት ጨዋታ የመጀመሪያዋን ግብ ካስቆጠረ ወዲህ በሊጉ የአስቆጣሪዎች ዝርዝር ውስጥ ጠፍቶ የነበረው ሳላዲን ሰዒድ ለአንድ ዓመት ከቀረበ ጊዜ ቆይታ በኋላ በሊጉ ሐት-ትሪክ በመስራት ወደ አግቢነት ተመልሷል።

👉 ያልተደነቁት የሄኖክ አዱኛ ክሮሶች

የሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከክፍት ጨዋታዎች ባልተናነሰ በቆሙ ኳሶች ተጋጣሚ ላይ የሚደቅነው ስጋት ቀላል የሚባል አይደለም። ከእዚህ ኳሶች አስፈሪነት በስተጀርባ ታድያ የግራ መስመር ተከላካዩ ሄኖክ አዱኛ ሁነኛ መሳርያ ነው።

ለአብነትም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከመከላከያ ጋር ምንም እንኳን ያለ ግብ ቢለያይም በርካታ ዕድሎችን ከቆሙ ኳሶች መፍጠር ችለዋል።

የቆሙ ኳሶችን ለማጥቃት በሚደረገው ጥረት ውስጥ ጊዜያቸውን የጠበቁ እና የታለመላቸውን ሰው በአግባቡ ማግኘት የሚችሉ ክሮሶች ከፍ ያለን ድርሻ ይይዛሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በሄኖክ አዱኛ በኩል የሚፈልጉትን እያገኙ ይገኛል።

በተለይ ደግሞ ከማዕዘን ምቶች እና ወደ መስመር ያደሉ (Wide Free Kicks) በሚያገኙበት ወቅት ሄኖክ አዱኛ የቡድኑን ተጫዋቾች በተለይም ጋናዊውን የመሀል ተከላካይ ፍሪምፖንግ ሜንሱን ታሳቢ ያደረጉ ጥራታቸው የላቁ ኳሶችን በማድረስ ወደር አይገኝለትም።

ስለ ቅዱስ ጊዮርጊስ የቆመ ኳስ ማጥቃት ስናስብ በመጨረሻው ወቅት ኳሷ ላይ ንክኪ አድርገው ኳሶቹን ወደ ግብ የሚልኩትን ተጫዋቾች በምናደንቅበት ልክ ኳሶቹንም አመቻችተው ለሚያደርሱ ተጫዋቾች ተገቢውን ክብር መስጠት ይገባናል።

👉 ከመስመር መነሳት የተመቸው ዊልያም ሰለሞን

ዊልያም ሰለሞን ከመከላከያ ወደ ኢትዮጵያ ቡና ከደረሰ በኋላ አብላጫውን የጨዋታ ደቂቃ በመሀል አማካይነት በመጫወት ቢያሳልፍም ወደ መስመር ወጥቶ ሲጫወት የተሻለ ተጫዋች መሆኑም ከሰሞኑ ዳግም እያስመሰከረ ይገኛል።

ከግራ መስመር መነሻውን ማድረግ ከሰሞኑ እየተጫወተ የሚገኘው ዊልያም ወደ መስመር ከተለጠጠ አቋቋም ኳሶችን በመቀበል ከውጭ ወደ ውስጥ አስደናቂ ፍጥነቱን እና ተጫዋቾችን የመቀነስ አቅሙን በመጠቀም ተደጋጋሚ ኳሶች ወደ ውስጥ ይዞ በመግባት ለቡድኑ ማጥቃት የተሻለ ነገር ለማበርከት ጥረት ሲያደርግ ተመልክተናል።

ይህን ሂደት በተለይ ቡድኑ ድቻን በገጠመበት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ኳሶችን ወደ ማጥቃት በማስገባት ረገድ ተቸግሮ ቢቆይም በሁለተኛው አጋማሽ በተለይም ዊልያም በተሰለፈበት የግራ መስመር በኩል በግሉ ከውጭ ወደ ውስጥ ያደርጋቸው የነበሩ ሩጫዎች ተጋጣሚን ሲፈትን እንዲሁም በተጋጣሚ ተጫዋቾች ጥፋት እየተሰራበት የቆሙ ኳስ አጋጣሚዎችን ሲያስገኝ አስተውለናል።

በመስመር አጥቂ ስፍራ ላይ ሁነኛ የተጫዋች ምርጫ እጥረት ያለበት ኢትዮጵያ ቡና የመስመር ተከላካዩን አስራት ቱንጆን ጨምሮ የመሀል አማካዩ አቤል እንዳለን ጭምር እየሞከሩ ለነበሩት አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ምናልባት ዊልያም ሰለሞን ጥሩ መፍትሄ ሊሆናቸው ይችላል።

👉 ዑመድ ኡኩሪ ጎል አስቆጥሯል

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አጋማሽ ዳግም ከዓመታት የግብፅ ቆይታ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የተመለሰው ዑመድ ዑኩሪ ከረጅም ጊዜያት በኋላ ወደ ግብ አግቢነት ተመልሷል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን አጋማሽ አንስቶ በሀዲያ ሆሳዕና ቆይታ እያደረገ የሚገኘው የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አጥቂ ከአምና አንሰቶ እስካሁን በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ግብ ማስቆጠር ተስኖት ቆይቷል። በዘንድሮው የውድድር ዘመን እንኳሁን የተጠናቀቀውን የጨዋታ ሳምንት ሳይጨምር በ13 ጨዋታዎች ላይ ለ783 ያህል ደቂቃዎች ተሳትፎ ያደረገው አጥቂው ከግብ ተራርቆ ቆይቷል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ሀዲያ ሆሳዕና አዳማ ከተማን ሲረታ ከወትሮ በተለይ በጨዋታ ወሳኝ ሂደቶች ላይ ተሳትፎን ያደረገው ዑመድ ዑከሪ ለበርካታ ጊዜያት ሲናፍቃት የነበረችውን ግብ በ28ኛው ደቂቃ ላይ ከቆመ ኳስ መነሻ በአዳማ ተከላካዮች ስህተት ታግዞ ማስቆጠር ችሏል።

የ2006 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የነበረው ዑመድ ዑኩሪ ከዚህች ግብ በኋላ የቀደመውን የግብ አግቢነት ደመነፍሱን መልሶ ያገኝ ይሆን የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉 ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ግብ አምራችነት ?

በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሲዳማ ቡናን ለቆ ፋሲል ከነማ ከደረሰ ወዲህ ብዙ የተጠበቀበት ኦኪኪ አፎላቢ በሚፈለገው ልክ ቡድኑን እያገለገለ አይገኝም በሚል ተደጋጋሚ ወቀሳዎችን እያስተናገደ ቆይቷል።

ፋሲል ከነማ የአሰልጣኝ ለውጥ ከማድረጉ በፊት በነበሩት 17 የጨዋታ ሳምንታት ሦስት ግቦችን ብቻ ያስቆጠረው ኦኪኪ በመጨረሻዎቹ ሁለት ጨዋታ ግን ሦስት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

በጅማ አባ ጅፋሩ ጨዋታ ከተጠባባቂነት የተነሳው እና በጨዋታው ወሳኟን የማሸነፊያ ግብ በጨዋታው መገባደጃ ላይ ማስቆጠር የቻለ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በቋሚነት በጀመረበት ጨዋታ ምንም እንኳን ቡድኑ የኋላ ኋላ ነጥብ ቢጋራም ሁለት ግቦችን ማስቆጠር ችሏል።

የ2010 የውድድር ዘመን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ኦኪኪ አፎላቢ በዘንድሮው የውድድር ዘመን ስድስት ግቦች ብቻ ያስቆጠረ ሲሆን ከዚህ በኋላ በሚኖሩ የጨዋታ ሳምንታት በተሻለ መጠን ግቦችን በማስቆጠር የቡድኑን በሰንጠረዡ አናት ወደ ላይ የመጠጋትን ህልም የማገዝ ምልክትን እየሰጠ ይገኛል።