የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ የ10ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ሪፖርት

በቶማስ ቦጋለ

ትናንት እና ዛሬ በተደረጉ የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተከታዩ ሀዋሳን በመረታት ልዩነቱን ሲያሰፋ በሰንጠረዡ ግርጌ ጌዲዮ ዲላ ወሳኝ ድል ተቀዳጅቷል።

አዲስ አበባ ከተማ 0-1 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ትናንት ረፋድ ላይ አዲስ አበባ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሲገናኙ አዲስ አበባዎች በ9ኛ ሳምንት አራፊ የነበሩ ሲሆን በ8ኛ ሳምንት በሐዋሳ ከተማ 4 ለ 3 ከተሸነፉበት አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም ስርጉት ተስፋየ ፣ ሰላማዊት ኃይሌ ፣ ዘይነባ ሰይድ እና ቤተልሔም ከፍያለው በቤተልሔም ዮሐንስ ፣ ሩታ ደስታ ፣ ንግሥት ኃይሉ እና መሠረት ገ/ሔር ተተክተዋል። ፈረሰኞቹ በበኩላቸው በ9ኛ ሳምንት በሐዋሳ ከተማ 3 ለ 0 ከተረቱበት ጨዋታ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ሶፋኒት ተፈራ እና ዓይናለም ዓለማየሁ በብዙዓየሁ ፀጋየ እና ዳግማዊት ሰለሞን ተለውጠዋል።

ቀዝቀዝ ያለ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ፈረሰኞቹ ከፍቅርአዳስ ገዛኸኝ ፣ ዓይናለም ዓለማየሁ እና እቴነሽ ደስታ የቅጣት ምት ኳሶች የግብ እድል ለመፍጠር ቢሞክሩም ውጤታማ መሆን አልቻሉም ነበር። 33ኛው ደቂቃ ላይ ሠላማዊት ኃይሌ ግብ ጠባቂዋን አልፋ ወደግብ የሞከረችውና የግራውን የግብ ቋሚ ታክኮ የወጣው ኳስ በአዲስ አበባ ከተማዎች በኩል ያስቆጨ አጋጣሚ ነበር። በተደጋጋሚም ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት አዲስ አበባዎች በሠላማዊት ኃይሌ ፣ ቤተልሔም ሰማኸኝ እና ትርሲት መገርሣ የግብ እድል ለመፍጠር ቢሞክሩም የመጨረሻ ኳሳቸው ደካማ ነበር። 42ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም መንተሎ በቀኙ የሜዳ ክፍል ከዓይናለም ዓለማየሁ የተቀበለችውን ኳስ በአግባቡ ወደግብ ቀይራ ፈረሰኞቹ የመጀመሪያውን አጋማሽ መርተው እንዲወጡ አስችላለች።

ሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ የተቀዛቀዘ እና ለተመልካችም አሰልቺ የነበረ ክፍለ ጊዜ ነበር። 52ኛው ደቂቃ ላይ ግን ፍቅርአዲስ ገዛኸኝ ከቤተልሔም መንተሎ የተሻገረላትን እና ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ያገኘቸውን ኳስ ሳትጠቀምበት ቀርታለች። አዲስአበባ ከተማዎች በሠላማዊት ኃይሌ ፣ የአብስራ ይታይህ እና ትርሲት መገርሣ የተለያዩ የግብ እድሎች መፍጠር ቢችሉም የመጨረሻ ኳሳቸው ውጤታማ አልነበረም። 70ኛው ደቂቃ ላይ ትርሲት መገርሣ ወደግብ ሞክራው የላይኛውን አግዳሚ ታክኮ የወጣው ኳስ በአዲስአበባ ከተማዎች በኩል የተሻለው ሙከራ ነበር። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት የባከነ ደቂቃዎች ሲቀሩ በጨዋታው ምርጥ እንቅስቃሴ ስታደርግ የነበረችው ቤተልሔም መንተሎ በግራ መስመር ወደግብ የሞከረችውና ግብ ጠባቂዋ በጥሩ ብቃት ያስቀረችው ኳስ የጨዋታው የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ ጨዋታው በቅዱስ ጊዮርጊስ አሸናፊነት ተጠናቋል።

አዳማ ከተማ 0-3 አርባምንጭ ከተማ

ትናንት 8፡00 ላይ አዳማ ከተማ ከ አርባምንጭ ሲጫወቱ አዳማዎች በ9ኛ ሳምንት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሠፊ የግብ ልዩነት ከተሸነፉበት ስብስብ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ምርቃት ፈለቀ እና ቅድስት ቦጋለ በናርዶስ ጌትነት እና ትዕግሥት ዘውዴ ተተክተው ገብተዋል። በአርባምንጭ ከተማ በበኩሉ ቦሌ ክፍለከተማን በካምላክነሽ ሀቆ ብቸኛ ግብ ከረታበት ስብስብ የአንድ ተጫዋች ብቻ ለውጥ ሲያደርግ በዚህም ለምለም አስታጥቄ ርብቃ ጣሠውን ተክታ ጨዋታውን ጀምራለች።

የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ያደረጉት አዳማዎች ሲሆኑ 9ኛው ደቂቃ ላይ ድንቅነሽ በቀለ ከቀኝ መስመር ወደግብ የሞከረችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ በቀላሉ ይዛዋለች። በቀጣዮቹ ደቂቃዎች በተደጋጋሚ ወደግብ መድረስ የቻሉት አዞዎቹ ደግሞ በወርቅነሽ ሚልሜላ፣ መሠረት ወርቅነህ እና ድንቅነሽ በቀለ የተለያዩ የግብ እድሎች መፍጠር ችለው ነበር። በተለይም 15ኛው ደቂቃ ላይ መሠረት ወርቅነህ ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝታ ያመከነችው ወርቃማ እድል አዞዎቹን ያስቆጨ አጋጣሚ ነበር። በጨዋታው ጥሩ እንቅስቃሴ ስታደርግ የነበረችው ድንቅነሽ በቀለ ደግሞ ከመሠረት ወርቅነህ የተሻገረላትን ኳስ በግሩም ሁኔታ አስቆጥራ ክለቧ የመጀመሪያውን አጋማሽ መርቶ እንዲወጣ አስችላለች።

በሁለተኛው አጋማሽ በጨዋታ ቁጥጥሩም በግብ ሙከራም የተሻሉ ሆነው የቀረቡት አዞዎቹ ሲሆኑ መሠረት ወርቅነህ ከወርቅነሽ ሚልሜላ የተሻገረላትን ኳስ በድጋሚ ከግብ ጠባቂ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝታ የሞከረችውን ኳስ የአዳማዋ ግብ ጠባቂ በአስደናቂ ሁኔታ ይዛዋለች። ከተጋጣሚ የሜዳ ክፍል እንደፈለጉት ኳስ መቀባበል ያልቻሉት አዳማዎቹ 64ኛው ደቂቃ ላይ በተሻለ ሁኔታ ወደግብ መድረስ ቢችሉም ምሕረት ፈለቀ ከቅድስት ቦጋለ በቀኝ መስመር የተሻገረላትን ኳስ ልታገኘው ባለመቻሏ ትልቅ እድል አምክናለች። 75ኛው ደቂቃ ላይ እንዲሁ ሠርካዲስ ጉታ ከግራ መስመር ከፀባኦት መሀመድ የተቀበለችውን ኳስ ወደግብ ብትሞክርም በአስቆጪ ሁኔታ የቀኙን ቋሚ ታኮ ወጥቶባታል።

በቀሪዎቹ ደቂቃዎች ሙሉ በሙሉ የበላይ የነበሩት አዞዎቹ ሲሆኑ 82ኛው ደቂቃ ላይ በተደጋጋሚ የግብ እድል እየፈጠረች ያልተጠቀመችው መሠረት ወርቅነህ ከሳጥን ውጪ ድንቅ ግብ አስቆጥራ የክለቧን መሪነት ማሳደግ ችላለች። ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር ተጭነው የተጫወቱት አዞዎቹ ተሳክቶላቸው ድንቅነሽ በቀለ ከመስከረም ገላና ተቀበላ በግሩም አጨራረስ ለራሷ ሁለተኛውን ለክለቧ ሦስተኛ ግብ አስቆጥራ ጨዋታው በአርባምንጭ 3 ለ 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ሀዋሳ ከተማ 1-5 ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ

10 ሰዓት ላይ ተጠባቂው የሐዋሳ ከተማ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጨዋታ ሲደረግ ሐዋሳ ከተማዎች ቅዱስ ጊዮርጊስን ሦስት ለምንም ሲያሸንፉ ከተጠቀሙበት ስብስብ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ በማድረግ ሲሣይ ገ/ዋህድ እና ረድኤት አስረሳኸኝን በዙፋን ደፈርሻ እና አፍያ አብዱልራህማን ተተክተው ሲገቡ ኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ደግሞ አዳማ ከተማን በሠፊ የግብ ልዩነት ሲረቱ የተጠቀሙበትን ስብስብ ሳይለውጡ ጨዋታውን ጀምረዋል።

በኳስ ቁጥጥሩም በግብ ሙከራም የበላይ የነበሩት ንግድ ባንኮች ሲሆኑ የመጀመሪያ ሙከራቸውን 11ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ አማካኝነት አድርገዋል። በግራው የሜዳ ክፍል እጅግ ጠንካራ የነበሩት ንግድ ባንኮች ተደጋጋሚ የግብ እድል የፈጠሩትም ከዚህ አቅጣጫ በአረጋሽ ካልሳ በሚነሱ ኳሶች ነበር። በተደጋጋሚ የግብ እድል መፍጠር የቻለችው ሰናይት ቦጋለም ዕድለኛ ሳትሆን ኳሶችን አምክናለች። ሐዋሳዎች ደግሞ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ያደረጉት በመንደሪን ክንድሁን የረጅም ኳስ ነበር።

23ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ ወደ ሳጥን ይዛው የገባችውን ኳስ የሐዋሳ ተከላካዮች ሲመልሱት ያገኘችው ሰናይት ቦጋለ ድንቅ የግብ ማግባት ሙከራ ብታደርግም የቀኙን ቋሚ ታኮ ወጥቶባታል። በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ሰናይት ቦጋለ እና እፀገነት ብዙነህ በጥሩ አንድ ሁለት ቅብብል ይዘውት የሄዱትና ሰናይት ወደግብ ሞክራው ግብ ጠባቂዋ በጥሩ ብቃት ወደ ውጪ ያስወጣችው ኳስም ሌላው ባንኮችን ያደረጉት ጥሩ አጋጣሚ ነበር። በ40ኛው ደቂቃም በቀኝ በኩል ከእመቤት አዲሱ ከረጅም ርቀት ተሰንጥቆ የደረሳትን ኳስ መዲና አወል የግብ ጠባቂዋን መውጣት አይታ ከፍ አድርጋ ሞክራው የግራውን ቋሚ ታክኮባት ወጥቷል።

43ኛው ደቂቃ ላይ ግን ሎዛ አበራ በግራ መስመር ከአረጋሽ ካልሳ የተሻገረላትን ኳስ በአግባቡ ተጠቅማ በማስቆጠር ንግድ ባንኮችን መሪ አድርጋለች። ከግቧ መቆጠር በኋላ ሳይረጋጉ ኳሱን የጀመሩትን ሐዋሳዎች ስህተት የተጠቀሙት ንግድ ባንኮቹ ሎዛ አበራ የግብ ጠባቂዋን መውጣት አይታ ከፍ አድርጋ ልካ ባስቆጠረችው ግብ 2 ለ 0 መምራት ችለዋል። ሐዋሳዎችም ከራሳቸው የግብ ክልል መውጣት ሳይችሉ የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቋል።

በሁለተኛው አጋማሽም ይበልጥ ተጭነው እና በልጠው የተጫወቱት ንግድ ባንኮች ሲሆኑ 61ኛው ደቂቃ ላይ ሎዛ አበራ ከአረጋሽ ካልሳ ተቀብላ ልታስቆጥር በምትችልበት ሁኔታ ላይ ከኋላ ምሕረት መለሰ ጥፋት በመሥራቷ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ራሷ ሎዛ አበራ አስቆጥራ ሐት-ሪክ መሥራት ችላለች። ከግቧ መቆጠር በኋላ ከረጅም ርቀት የግብ እድል ለመፍጠር የሞከሩት ሐዋሳዎች በረድኤት አስረሳኸኝ እና ዙፋን ደፈርሻ የተለያዩ እድሎች ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም። 76 ኛው ደቂቃ ላይ ፀሐይነሽ ጅላ በቀኝ ቀኩል ያገኘችውን የቅጣት ምት በጥሩ ሁኔታ ብትሞክርም ለጥቂት ወጥቶባታል። በአንድ ደቂቃ ልዩነት የመልስ ምት ሆኖ የተመለሰውን ኳስ አረጋሽ ካልሳ የሐዋሳን ተከላካዮች አታላ በማለፍ ድንቅ ግብ አስቆጥራ የክለቧን የጎል ልዩነት ከፍ አድርጋለች።

82ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባችው ዙፋን ደፈርሻ ቱሪስት ለማ ላይ የተሠራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት አስቆጥራ ክለቧን ወደ ጨዋታው ለመመለስ ጥራለች። 90ኛው ደቂቃ ላይ እመቤት አዲሱ ከረጅም ርቀት ድንቅ ቅጣት ምት መታ ግብ ጠባቂዋ መቆጣጠር ተስኗት ግብ ሆኗል። ጨዋታው ከመጠናቀቁ በፊት ጥሩ የግብ ማግባት እድል ያገኘችው የሐዋሳዋ ቱሪስት ለማ ኃይል ባልነበረው ኳስ እድሏን አባክናለች። ይሄም የጨዋታው የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው በንግድ ባንክ 5-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ጌዲዮ ዲላ 2-0 ባህር ዳር ከተማ

ዛሬ ረፋድ 3፡00 ላይ የጌዴኦ ዲላ እና የባህርዳር ከተማ ጨዋታ ሲደረግ ጌዴኦ ዲላዎች በዘጠነኛ ሣምንት በኢትዮ ኤሌክትሪክ በምንትዋብ ዮሐንስ ብቸኛ ግብ ከተረቱበት ስብስብ ምንም የተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ ሲቀርቡ የጣና ሞገዶች በበኩላቸው በዘጠነኛ ሣምንት በመከላከያ 2 ለ 1 ሲሸነፉ ከተጠቀሙበት ስብስብ የአንድ ተጫዋች ለውጥ ሲያደርጉ ቅድስት ዓባይነህ በጥሩወርቅ ወዳጅ ተተክታ ገብታለች።

በመጀመሪያው አጋማሽ በኳስ ቁጥጥሩ በኩል ሞገደኞቹ የተሻለ የነበሩ ሲሆን ወደተጋጣሚ የግብ ክልል በመድረስ የግብ ዕድል በመፍጠር ጌዴኦ ዲላዎች የተሻሉ ነበሩ። የጨዋታው የመጀመሪያ ሙከራ 5ኛ ደቂቃ ላይ ምስር ኢብራሂም ከረጅም ርቀት ወደግብ በሞከረችው እና ግብ ጠባቂዋ በቀላሉ በያዘችው ኳስ ነበር። በሁለት ደቂቃ ደቂቃዎች ልዩነት ጌዴኦ ዲላዎች በመልሶ ማጥቃት ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ ሲያደርጉ አልማዝ ብርሃኔ አመቻችታ ያቀበለችውን ኳስ የግብ ጠባቂዋ ስህተት ተጨምሮበት ያገኘችው ቤተል ጢባ ኳሱን ወደግብ ከመሞከር ይልቅ ወደቀኙ የሜዳ ክፍል በመውሰድ እና ለጽዮን ማንጁራ አመቻችታ ብታቀብልም ጽዮን ያደረገችው ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ የግራውን ቋሚ ታክኮ ወጥቶባታል። 11ኛው ደቂቃ ላይ ከተጋጣሚው ሳጥን አጠገብ የተሰጠውን የቅጣት ምት አዲስ ንጉሤ በግሩም ሁኔታ አስቆጥራ ክለቧን መሪ አድርጋለች።

ከግቧ መቆጠር በኋላ የተሻለ ተጭነው የተጫወቱት ባህር ዳሮች ሲሆኑ የመጨረሻ ኳሳቸው ግን ውጤታማ አልነበረም። 31ኛው ደቂቃ ላይ ሜላት ደመቀ ከማዕዘን ያሻማችውን ኳስ ትዕግሥት ወርቄ በግንባሯ የጨረፈችውን ኳስ ነጻ ሆና ያገኘችው ምስር ኢብራሂም ኳሱን ባለመቆጣጠሯ ቡድኗን አቻ ሊያደርግ የሚችል ወርቃማ ዕድል አምክናለች። በተደጋጋሚም ሞገዶኞቹ በ መንደሪን ታደሠ ፣ በምስር ኢብራሂም እና በ ቤተልሔም ግዛቸው የተለያዩ የግብ እድሎች መፍጠር ቢችሉም ውጤታማ አልነበሩም። 39ኛው ደቂቃ ላይ ቤተል ጢባ ሳጥን ውስጥ በቀኝ በኩል ከ ይታገሡ ተገኝወርቅ የተቀበለችውን ኳስ በጥሩ አጨራረስ አስቆጥራ የቡድኗን መሪነት አጠናክራለች። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት ግብ ለማስቆጠር ወደተጋጣሚ ክልል ይበልጥ ተጠግተው የተጫወቱት ባህር ዳሮች በምስር ኢብራሂም እና በሜላት ደመቀ ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራዎችን ቢያደርጉም አልተሳካላቸውም በተለይም ሜላት በጥሩ ሁኔታ ከረጅም ርቀት የሞከረችውና ግብ ጠባቂዋ የያዘችው ኳስ የተሻለው ሙከራ ነበር።

ሁለተኛው አጋማሽ ጌዴኦ ዲላዎች ወደኋላ ተመልሰው ባህርዳር ከተማም የተሻለ የማጥቃት አጨዋወት ሲሞክር ያየንበት ሲሆን 54ኛው ደቂቃ ላይ ምስር ኢብራሂም ከርቀት የሞከረችውን ኳስ በግብ ጠባቂዋ ሲመለስ ግብ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረችው ትዕግሥት ወርቄ ኳሱን ሳትጠቀምበት ቀርታ ወደ ቀኝ መስመር እየገፋች ወስዳ ከበረኛዋ ከፍ አድርጋ ለሊዲያ ጌትነት ብታቀብላትም ክፍት ጎል ለብቻዋ ያገኘችው ሊዲያ ጌትነት ኳሱን ከላይኛው አግዳሚ ጋር በማጋጨት ወርቃማ ዕድል ስታመክን ወደ ጨዋታው ለመመለስ የፈለጉትን ሞገደኞች በጣም ያስቆጨ አጋጣሚ ነበር። በተደጋጋሚ ሞገደኞቹ ከቆሙ ኳሶች በሣባ ኃይለሚካኤል እና በአዳነች ጌታቸው ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ ሲያደርጉ በተለይም 75ኛው ደቂቃ ላይ ሣባ በቀኝ መስመር ያገኘቸውን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ብትሞክርም ከግብ ጠባቂዋ ያለፈውን ኳስ በጨዋታው ምርጥ እንቅስቃሴ ስታደርግ የነበረችው አዲስ ንጉሤ በአስደናቂ ሁኔታ በግንባሯ በመግጨት አውጥታዋለች።

ከዕረፍት መልስ ተረጋግተው የራሳቸው የሜዳ ክፍል ውስጥ ሲጫወቱ የነበሩት ጌዴኦ ዲላዎች 85ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ንጉሤ ከቅጣት ምት የሞከረችውና ግብ ጠባቂዋ የያዘችው ኳስ በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ የግብ ሙከራቸው ነበር። በተደጋጋሚ በ ትዕግሥት ወርቄ ፣ ምስር ኢብራሂም ፣ ሊዲያ ጌትነት እና ሜላት ደመቀ የተለያዩ የግብ እድሎች ቢፈጥሩም ውጤታማ ስላልነበሩ ጨዋታው ከረፍት በፊት በተቆጠሩት ግቦች ጨዋታው በጌዴኦ ዲላ 2 – 0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ቦሌ ክፍለ ከተማ 0-2 ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ከሰዓት 8፡00 ቦሌ ክፍለከተማ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሲገናኙ ቦሌዎች በዘጠነኛ ሣምንት በአርባምንጭ ከተረቱበት ጨዋታ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ብዙነሽ እሸቱ እና ሒሩት ተስፋዬ በየምሥራች ሞገስ እና ምርጥነሽ ዮሐንስ ተተክተው ገብተዋል። ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው በዘጠነኛ ሣምንት ጌዴኦ ዲላን በምንትዋብ ዮሐንስ ብቸኛ ግብ ከረቱበት ስብስብ የአንድ ተጫዋች ብቻ ለውጥ ሲያደርጉ ዘለቃ አሠፋ በመስከረም ኢሳይያስ ተተክታ ገብታለች።

የመጀመሪያው አጋማሽ መጠነኛ ፉክክር የታየበት ሲሆን የመጀመሪያውን ሙከራ ያደረጉት ኤሌክትሪኮች ሲሆኑ ጨዋታው በጀመረ በአንድ ደቂቃ ውስጥ ዓይናለም አሳምነው በቀኝ መስመር ከምንትዋብ ዮሐንስ የተሻገረላት እና ወደግብ ሞክራው ግብ ጠባቂዋ በያዘችው ኳስ ነበር። ኤሌክትሪኮች በተደጋጋሚ በተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ውስጥ ገብተው በቤተልሔም አስረሳኸኝ እና ሠላማዊት ጎሣየ የግብ ዕድል መፍጠር ሲችሉ የመጨረሻ ኳሳቸው ግን ውጤታማ አልነበረም። ቦሌዎች የተሻለ ሙከራ ያደረጉት 11ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ንግሥት በቀለ በቀኝ መስመር ይዛው ገብታ ባደረገችው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ ነበር።


ቦሌዎች የራሳቸው የሜዳ ክፍል ውስጥ ኳሱን ተቆጣጥረው የመጨረሻ ኳሳቸውን በንግሥት በቀለ በኩል በማድረግ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሲሞክሩ ኤሌክትሪኮች በበኩላቸው የተጋጣሚ የሜዳ ክፍል ውስጥ በዝተው ተገኝተው በተጠጋጋ አቋቋም ኳስ ተቀባብለው የግብ ዕድል ለመፍጠር ሞክረዋል። በኤሌክትሪክ በኩል ዓይናለም አሳምነው ወደግብ ሞክራው የግቡን አግዳሚ ታክኮ የወጣባት ኳስና የቦሌዋ ንግሥት በቀለ ከ ብዙነሽ እሸቱ ተቀብላ በጥሩ ሁኔታ ወደግብ ሞክራው በኤሌክትሪክ ተከላካዮች የተመለሰው ኳስ የሁለቱም ክለቦች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ያላቸውን ፍላጎት የጨመረ ነበር።

20ኛው ደቂቃ ላይ ንቦኝ የን በግራ መስመር ትርሲት ወንድወሰን ራሷ ላይ የሰራችውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጣትን የቅጣት ምት በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ሞክራው የላይኛው የግቡ አግዳሚ የመለሰው ኳስ ኤሌክትሪኮችን ያስቆጨ አጋጣሚ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት በኤሌክትሪኮች በኩል ምንትዋብ ዮሐንስ ፣ ዓይናለም አሳምነው ፣ ንቦኝ የን ፣ ዙሌይካ ጁሃር እና ፀጋ ንጉሤ የተለያዩ የግብ ዕድሎች ሲፈጥሩ ቦሌዎች በበኩላቸው በንግሥት በቀለ በቆሙ ኳሶች የግብ ዕድል ለመፍጠር ቢሞክሩም በመጨረሻ ኳሳቸው ውጤታማ አልነበሩም። በተለይ 42ኛው ደቂቃ ላይ ዓይናለም አሳምነው ከምንትዋብ ዮሐንስ የተቀበለችውና ወደግብ በግሩም ሁኔታ ሞክራው የቀኙን ቋሚ ታክኮ የወጣው ኳስ ሌላኛው ኤሌክትሪኮችን ያስቆጨ አጋጣሚ ነበር።

በሁለተኛው አጋማሽ ኤሌክትሪኮች ይበልጥ ተሻሽለው ሲቀርቡ 51ኛው ደቂቃ ላይ ዓይናለም አሳምነው ከምንትዋብ ዮሐንስ ምርጥ የመጨረሻ ኳስ ብታገኝም ኳሱን በትክክል ባለመግፋቷ ዘግይታ የሞከረችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ ወደማዕዘን ምት አውጥታባታለች። 57ኛው ደቂቃ ላይ ሰላማዊት ንጉሤ በግሩም ሁኔታ ያቀበለቻትን ኳስ ዓይናለም አሳምነው ግብ ጠባቂዋን በማለፍ በምርጥ አጨራረስ አስቆጥራ ቡድኗን መሪ አድርጋለች።

በሁለተኛው አጋማሽ ቦሌዎች አንድ ብቻ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጉ ሲሆን 65ኛው ደቂቃ ላይ መዓዛ አብደላ በግራ መስመር ከረጅም ርቀት ወደግብ የሞከረችውና ግብ ጠባቂዋ በያዘችው ኳስ ነበር። 76ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም አስረሳኸኝ ከቅጣት ምት ያሻማችውን ኳስ ያገኘችው ንቦኝ የን በትክክል ባለመግጨቷ ዕድሏን አባክናለች። 84ኛው ደቂቃ ላይ ንቦኝ የን በአጋጣሚ ባገኘችው ኳስ በተረጋጋ ሁኔታ በምርጥ አጨራረስ ሁለተኛ ግብ አስቆጥራለች። ጨዋታውም በኢትዮ ኤሌክትሪክ በ 2-0 አሸናፊነት ጨዋታውን ተጠናቋል።

መከላከያ 1-1 ድሬዳዋ ከተማ

የአስረኛ ሣምንት የመጨረሻ ጨዋታ 10፡00 ላይ በመከላከያ እና በድሬዳዋ ከተማ መካከል ሲደረግ መከላከያዎች በዘጠነኛ ሣምንት ባህርዳር ከተማን 2-1 ከረቱበት ስብስባቸው የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ቤተልሔም በቀለና መቅደስ ማሞ በመስከረም ኮንካ እና ካሠች ፍስሐ ተተክተው ሲገቡ ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው በዘጠነኛ ሣምንት ከአቃቂ ቃሊቲ ሁለት አቻ ከተለያዩበት ስብስብ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገው አበባየሁ ጣሠው ፣ ዘቢብ ኃይለሥላሴ ፣ ሠናይት ባሩዳ እና ታደለች አብርሃም በሀዳስ ዝናቡ ፣ የካቲት መንግሥቱ ፣ ቤዛዊት ንጉሤ እና ሔለን መሠለ ተተክተው ገብተዋል።

በሁለቱም በኩል ብርቱ ፉክክር በታየበት የመጀመሪያ አጋማሽ መከላከያዎች በመስመር በመሳይ ተመስገን በኩል ተደጋጋሚ የግብ ዕድል መፍጠር ሲችሉ በድሬዳዋ በኩል ሠናይት ባሩዳ የተሻሉ የግብ ዕድሎችን መፍጠር ችላለች። 15ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዋ ታደለች አብርሃም ከቀኝ መስመር ወደ ግብ የሞከረችውና የላይኛውን አግዳሚ ታክኮ የወጣው ኳስ በጨዋታው የተሻለው የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። ድሬዎች በተደጋጋሚ የግብ ዕድል መፍጠር ሲችሉ 19ኛው ደቂቃ ላይ ሠናይት ባሩዳ ቺፕ አድርጋ የሞከረችውን ምርጥ ሙከራ ግብ ጠባቂዋ ይዛባታለች።

በሁለት ደቂቃ ልዩነት ራሷ ሠናይት ባሩዳ በቀኝ መስመር ያሻማችውን ኳስ ነጻ ሆና ያገኘችው ሠርካለም ባሳ ኳሱን በትክክል ባለማብረዷ የግብ እድሏን ስታመክን ግብ ጠባቂዋ ደርሳ ይዛዋለች። የተሻለ ተጭነው እና በተጋጣሚ የግብ ክልል በዝተው የተጫወቱት ድሬዎች በቤተልሔም ታምሩ ከግራ መስመር ምርጥ የግብ ማግባት ቢያደርጉም ኳሱ የግቡን የቀኝ ቋሚ ታክኮ ወጥቶባታል። ከውሀ ዕረፍት መልስ የተሻለ እንቅስቃሴ ያደረጉት መከላከያዎች ሲሆኑ በሴናፍ ዋቁማ ፣ መሳይ ተመስገን እና ረሒማ ዘርጋው የተለያዩ የግብ ዕድሎች መፍጠር ችለዋል።

39ኛው ደቂቃ ላይ ሴናፍ ዋቁማ ከግራ መስመር ከመሳይ ተመስገን የተሻገረላትና ወደግብ ሞክራው የላይኛውን ቋሚ ተጠግቶ የወጣው ኳስ በመከላከያዎች በኩል የተሻለው የመጀመሪያ ሙከራ ነበር። የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ጭማሪ ደቂቃዎች ሲቀሩ ገነት ኃይሉ ከቀኝ መስመር ያሻማችውን ኳስ ረሒማ ዘርጋው በግሩም ሁኔታ ብትገጭም የላይኛው አግዳሚ መልሶባታል። ይሄም የመጀመሪያው አጋማሽ የመጨረሻ ሙከራ ሆኗል።

ሁለተኛው አጋማሽ በግብ ዕድል ፈጠራዎች በኩል ከመጀመሪያው አጋማሽ በመጠኑም ቢሆን የተቀዛቀዘ ነበር። በሁለተኛው አጋማሽ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ረሂማ ዘርጋው ከሴናፍ ዋቁማ ምርጥ የመጨረሻ ኳስ አግኝታ መምታት ባትችልም ኳሱን በድጋሚ አግኝታ ለቤዛዊት ተስፋዬ አመቻችታ ስታቀብል ቤዛዊት ተስፋዬ ወደ ግብ ስትሞክር ኢላማውን ባለመጠበቋ ወርቃማ እድል አምክናለች። 51ኛው ደቂቃ ላይ ከግራ መስመር ማዕድን ሳህሉ ያሻማችውን ኳስ ረሒማ ዘርጋው በግሩም ሁኔታ በግንባሯ ብትገጭም ኢላማውን የጠበቀ አልነበረም።

ድሬዳዋ ከተማዎች ከዕረፍት መልስ የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጉት 66ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ቤተልሔም ታምሩ ከቀኝ መስመር ከቅጣት ምት ግሩም ሙከራ አድርጋ ግብ ጠባቂዋ በአስደናቂ ሁኔታ አስወጥታዋለች። 74ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ ገብታ አስደናቂ እንቅስቃሴ ያደረገችው ሥራ ይርዳው በቀኝ መስመር በግሩም ሁኔታ ገፍታ የወሰደችውን ኳስ ለረሒማ ዘርጋው አመቻችታ ብታቀብልም ረሒማ ኳሱን ሙሉ በሙሉ በግንባሯ ባለማግኘቷ ተጨርፎ ወጥቶባታል።

የጨዋታው ቀሪ 15 ደቂቃዎች አስገራሚ ትዕይንት የታየባቸው ሲሆን 79ኛው ደቂቃ ላይ ሥራ ይርዳው በቀኝ መስመር ወስዳ ያሻገረችውን ኳስ ነፃ ሆና ያገኘችው ረሒማ ዘርጋው ስታስቆጥር የመከላከያ ተጫዋቾች ጎሏ በተቆጠረችበት ቅፅበት እየሮጡ ደስታቸውን ለመግለጽ ወደ አሰልጣኛቸው በመጡበት እና አንድ ላይ ባሉበት ሰዓት በሴኮንዶች ልዩነት ድሬዳዋ ከተማዎች ኳሱን በፍጥነት ከመሐል ጀምረው ቤተልሔም ታምሩ ከረጅም ርቀት ግብ ስታስቆጥር የመሀል ዳኛው በማጽደቁ በመከላከያ በኩል ሜዳው ውስጥ ባልነበርንበት ጨዋታው መጀመር አልነበረበትም በሚል ከፍተኛ ቅሬታ ቀርቦ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ጨዋታው ሲቋረጥ የጨዋታው ኮሚሽነር ካሉበት ቦታ ወደሜዳ መጥተው የመከላከያን የቡድን አባላት በማረጋጋት ጨዋታው እንዲቀጥል አድርገዋል።

የጨዋታው መጠናቀቂያ ደቂቃዎች ላይ ሴናፍ ዋቁማ ኃይል ያልነበረው አክሮባቲክ ግብ ለማስቆጠር ብትሞክርም ግብ ጠባቂዋ ይዛዋለች። መሳይ ተመስገን እና ገነት ኃይሉ የተለያዩ የግብ ዕድሎች ቢፈጥሩም ውጤታማ አልነበሩም። በተለይም በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ገነት ኃይሉ ከሥራ ይርዳው የተቀበለችውን እና ወደግብ ሞክራው በዘቢብ ኃይለሥላሴ ድንቅ ብቃት የተመለሰው ኳስ መከላከያዎችን ያስቆጨ አጋጣሚ ነበር። ጨዋታውም በዚሁ አንድ አቻ ተጠናቋል።