በዓምላክ ተሰማ ወሳኙን ጨዋታ ለመምራት ደቡብ አፍሪካ ደርሷል

በአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ከሚደረጉ ወሳኝ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታዎች መካከል አንዱ የሆነውን ፍልሚያ ኢትዮጵያዊው አልቢትር ይመራዋል።

የ2021/22 የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ ውድድር ወደ ወሳኝ ምዕራፍ እየተሸጋገረ ሲሆን በሳምንቱ መጨረሻም አራት ውስጥ የሚገቡ ክለቦች የሚለዩበት የሩብ ፍፃሜ የመልስ ጨዋታዎች ይደረጋሉ። ከእነዚህ ጨዋታዎች አንዱ የሆነውን ተጠባቂ መርሐ-ግብር ደግሞ የሀገራችን ዋና ዳኛ በዓምላክ ተሰማ ለመዳኘት ወደ ስፍራው አምርቷል።

በዓምላክ የሚመራው ጨዋታ ነገ በኤፍ ኤን ቢ ስታዲየም የሚደረገው የማሜሎዲ ሰንዳውንስ እና ፔትሮ አትሌቲኮን ጨዋታ ነው። በመጀመሪያው ዙር የተደረገውን የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ የአንጎላው ክለብ ፔትሮ የ2016 የውድድሩን ዋንጫ ባለቤት ሰንዳውንስ 2ለ1 አሸንፎ እንደነበር አይዘነጋም። ከ2006 ጀምሮ በቻምፒየንስ ሊጉ ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ (37 አሸንፎ 8 አቻ) የተሸነፉት ሰንዳውንሶች ከሜዳቸው ውጪ ባለፉት 18 የውድድሩ ጨዋታዎች አራቱን ብቻ ካሸነፉት ተጋባዦቹ ጋር የሚያደርጉት ጨዋታ ትልቅ ግምት ሲሰጠው በዓምላክም ጨዋታውን እንዲመራ በካፍ ተመርጦ ወደ ስፍራው አቅንቷል።

የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ አሸናፊ ከ ሲ አር ቤሉይዝዳድ እና ዋይዳድ ካሳብላንካ ጋር በግማሽ ፍፃሜው የሚገናኙ ይሆናል።