በሦስተኛው የዐበይት ጉዳዮች ፅሁፋችን አሰልጣኞች ላይ ያተኮሩ ጉዳዮችን ተዳሰዋል።
👉 ያሳደገውን ክለብ በተቃራኒ የገጠመው ተመስገን ዳና
በቅርቡ በፕሪሚየር ሊጉ ወልቂጤ ከተማን በዋና አሰልጣኝነት የተረከበው ተመስገን ዳና በትልቅ ደረጃ የመጀመሪያውን የአሰልጣኝነት ኃላፊነቱን በመወጣት ላይ የሚገኝ ሲሆን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት የቀድሞ ክለቡን በተቃራኒ ገጥሟል።
በሀዋሳ ከተማ ወጣቶችን በማሰልጠን በጀመረው የሥልጠና ህይወቱ በመቀጠል በሀዋሳ ከተማን ከ17 እና 20 ዓመት በታች ቡድኖች በማሰልጠን የተሳኩ ዓመታት ማሳለፉ አይዘነጋም። በኋላ ላይም በዋናው የሀዋሳ ከተማ ቡድን ውስጥ በረዳት አሰልጣኝነት ሆኖ ማገልገል ችሏል።
በአሁኑ ወቅት በሀዋሳ ከተማ በዋናው ቡድን ደረጃ እየተጫወቱ ከሚገኙ ተጫዋቾች መካከል ዳግም ተፈራ ፣ ሄኖክ ድልቢ ፣ ተባረክ ሂፋሞ ፣ መስፍን ታፈሰ ፣ ቸርነት አውሽ ፣ ወንድማገኝ ማዕረግ ፣ ዳዊት ታደሰ ፣ ዮሐንስ ሰጌቦ የመሳሰሉት ተጫዋቾች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ የአሰልጣኝ ተመስገን ሥልጠና ስር ያለፉ ናቸው።
በተለይ አሰልጣኙ በሀዋሳ ከተማ የዕድሜ እርከን ቡድኖች በነበረው ቆይታ በአሁኑ ሰዓት በፕሪሚየር ሊጉ በዋናው ቡድን ሀዋሳ ከተማን እያገለገሉ የሚገኙ በርካታ ተጫዋቾች ማፍራት የቻለ ሲሆን ከሀዋሳ ከተማ ተጫዋቾች እና ክለቡ ጋር ካለው የስሜት ትስስር ጋር በተያያዘ ወልቂጤ ከተማ ከሀዋሳ ከተማ ጋር ያደረጉት ጨዋታ ትልቅ ትርጉም የነበረው ነው።
👉 የፀጋዬ ኪዳነማርያም አስተያየቶች
በዘንድሮው የውድድር ዘመን ወላይታ ድቻን በዋና አሰልጣኝነት እየመሩ የሚገኙት ፀጋዬ ኪዳነማርያም ምናልባት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ካሳለፏቸው የውድድር ዘመናት ውጤታማውን ጊዜ በዘንድሮው የውድድር ዘመን እያሳለፉ ይገኛሉ።
ታድያ አሰልጣኙ ሁሌም ቢሆን ከጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ በሚሰጧቸው አስተያየቶች ያላቸው ስብብስ ከሌሎች አንፃር ጠባብ ስለመሆኑ እና ባላቸው ስብስብ የተቻላቸውን ለማድረግ እንደሚጥሩ ሲያነሱ በተደጋጋሚ አድምጠናል። መሰል ይዘት ያላቸው አስተያየቶችን ቡድኑ ሲሸነፍም ሆነ አሸንፎ ከአሰልጣኙ አንደበት ማድመጥ የተለመደ ነው።
እርግጥ ነው የወላይታ ድቻ ስብስብ የትኛውም የእግርኳስ ቤተሰቡ በሚረዳው ልክ ጠባብ ስለመሆኑ ለመረዳት አስታዋሽ የሚያስፈልገው ጉዳይ አይደለም። ታድያ አሰልጣኙ በተደጋጋሚ መሰል አስተያየት ከመስጠታቸው በስተጀርባ ያለውን እሳቤ ግን ለመረዳት መሞከር ተገቢ ነው።
አሰለልጣኙ ምናልባት ይህን “ስብስባችን ደካማ ነው” የሚለውን እሳቤ ይበልጥ ተጫዋቾቹን ለማነሳሳት እየተጠቁመበት ሊሆን እንደሚችል መገመት ይቻላል። አሰልጣኞች በአመዛኙ በቡድናቸው እና በሌሎች ተፎካካሪዎቹ መካከል በግልፅ የሚታይ የጥራት ልዩነት መኖሩን ሲረዱ በተጫዋቾቻቸው “እኛ እና እነሱ” የሚል አዕምሯዊ ትርክትን በመፍጠር ተጫዋቾቻቸውን ሆነ ደጋፊዎችን ለማነሳሳት ሲጠቀሙበት እንመለከታለን።
በዚህ ሂደት ውስጥ ተጫዋቾች በወረቀት ላይ ያለውን የጥራት ልዩነት ለማጥበብ የአቅማቸውን 110% እንዲሰጡ በማነሳሳት ያንን ልዩነት ፉርሽ የማድረግ ፍላጎት ይስተዋላል። ይህን አስተሳሰብ በተጫዋቾች ላይ ይበልጥ ማስረፅ ከተቻለ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ራሱ ወላይታ ድቻን ጨምሮ በርካታ ክለቦችን በምሳሌነት ማንሳት ይቻላል።
የአሰልጣኝ ፀጋዬም እሳቤ ከዚህ የተለየ አይመስለም። ብዙዎች በክረምቱ እጅግ ጥቂት ተጫዋቾችን እንደማዘዋወራቸው እና በስብስቡ ውስጥ ያለው ጥቅል የተጫዋቾች ጥራትን ከነበራቸው ደካማ የቅድመ ውድድር ዝግጅት ጋር በማስተሳሰር ቡድኑ ሊቸገር ይችላል ብለው ቢገምቱም ወላይታ ድቻ ግን ከ19 የጨዋታ ሳምንት በኋላ ከመሪው በስምንት ነጥብ ርቆ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በቀጣይ አሰልጣኙ ክለቡ ላይ እየፈጠሩት የሚገኘው ይህ አስተሳሰብ ምን ድረስ ያደርሳቸዋል የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
👉 ኢትዮጵያ ቡና እና የአቡበከር ናስር አጠቃቀም
አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ ኢትዮጵያ ቡና ወላይታ ድቻን ከገጠመበት ጨዋታ መጀመር አስቀድሞ በሰጡት አስተያየት አቡበከር ናስር ከጉዳት ጋር እየተጫወተ እንደሚገኝ እና በዚህም ከጨዋታው በፊት በነበሩ አራት ልምምዶች ላይ ባለመካፈሉ ተጠባባቂ እንደሆነ ሲያስረዱ አድምጠናል።
ባለፈው የጨዋታ ሳምንት ቡድኑ ሰበታ ከተማን ሲረታ ከነጉዳቱ ሲጫወት የተመለከትነው አቡበከር ናስር በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ በተጠባባቂነት በጀመረበት ጨዋታ በ62ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለ ደባልቄን ቀይሮ በመግባት ጨዋታውን አድርጓል።
ምንም እንኳን ከጉዳት ጋር ቢጫወትም በሰበታ ከተማ ላይ ግብ ሲያስቆጥር በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ሮቤል ላስቆጠራት ግብ ኳሷን አመቻችቶ በማቀበልም አሁንም ለቡድኑ ማጥቃት እና የራስ መተማመን ምን ያህል አስፈላጊ ተጫዋች እንደሆነ ማረጋገጥ ችሏል።
በሁለቱም ጨዋታዎች ታድያ ተጫዋቹ በሙሉ ጤንነት እንዳለመገኘቱ በእንቅስቃሴዎቹ ላይ በተወሰነ መልኩ ምቾት እየተሰማው እንደማይገኝም እንዲሁ ተመልክተናል። ታድያ ዋነኛው ጥያቄ የሚነሳው እዚህ ጋር ነው። አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ እና ረዳቶቹ የአቡከርን አስፈላጊነት ይረዳሉ ነገር ግን ደግሞ ተጫዋቹ ከጉዳት ጋር እየታገለ ይገኛል።
ብዙውን ጊዜ ወጣት ተጫዋቾች በየትኛውም ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ቢሆኑ የመጫወት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ይታመናል። እንደ አቡበከር ናስር ያለ ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ጋር የላቀ የስሜት ትስስር ያለው ተጫዋች ሲሆን ነገሩ እንዴት ጠንከር ያለ እንደሚሆን ማሰብ ከባድ አይሆንም። ነገር ግን አሰልጣኞች ምንም ያህል ጫናዎች ቢኖሩ ተጫዋቹ ያለበት የጤንነት ሁኔታ በመገምገም ለቡድኑም ሆነ ለተጫዋቹ ይበጃል የሚሉትን ነገር ከግምት ውስጥ በማስገባት የተጫዋቹን ጤንነት ያማከሉ የጨዋታ ደቂቃዎች መመጠን የግድ ይላቸዋል።
እምብዛም የጉዳት ታሪክ የሌለው ተጫዋቹ ዘንድሮ በብሔራዊ ቡድን ሆነ በክለብ ቆይታው መሰለ መጠነኛ የሚመስሉ ጉዳቶች እየተደጋገሙበት ይገኛል። የጉዳቶቹ መጠኖች አነስተኛ ቢሆኑም ምናልባት ተጫዋቹ ከአምና ጀምሮ ያለ ዕረፍት ያደረጋቸው ጨዋታዎች ሊሆኑ ስለሚችሉ የጨዋታ ደቂቃዎች ላይ የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኞች በቀጣይ ትኩረት ማድረግ ይገባቸዋል።
በመሆኑም አሰልጣኝ ካሳዬ አራጌ በቀጣይ ቡድኑ በሊጉ የተሻለ ደረጃን ይዞ ለማጠናቀቅ የሚረዱ ወሳኝ ጨዋታዎች ከፊታቸው የሚጠብቋቸው ቢሆንም በቀጣይ ሙሉ ጤንነት ላይ የማይገኘውን አቡበከር ናስርን በምን መልኩ ይጠቀሙበታል የሚለው ጉዳይ ይይጠበቃል።
👉 ጫና ውስጥ እየገቡ የሚገኙት ፋሲል ተካልኝ እና አብርሃም መብራቱ
19ኛ የጨዋታ ሳምንት ላይ በደረሰው የሊግ ውድድር እስካሁን በርካታ ክለቦች የውድድር ዘመኑን አብረዋቸው ከጀመሩ አሰልጣኞች ጋር ተለያይተው በምትካቸው ሌሎች አሰልጣኞችን በመቅጠር የውድድር ዘመናቸውን እየቀጠሉ ይገኛል።
የአሰልጣኝነት ሥራ ከምንም በላይ ከውጤት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ውጤት ሲጠፋ አሰልጣኞች ላይ ጫና መበርታቱ አይቀሬ ነው። በዚህም መነሻነት ከሰሞነኛ የውጤት መጥፋት ጋር በተያያዘ የአዳማ ከተማው ፋሲል ተካልኝ እና የባህር ዳር ከተማው አብርሃም መብራቱ ከፍ ባለ ጫና ውስጥ ያሉ ይመስላል።
በውድድር ዘመኑ በ12 ጨዋታዎች አቻ በመለያየት ቀዳሚ ቡድን የሆነው አዳማ ከተማ ከአንድ ነጥብ ባለፈ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ እየተቸገረ ይገኛል። በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ቡድኑ በሀዲያ ሆሳዕና መረታቱን ተከትሎ አሰልጣኙ ጫና ውስጥ የገቡ ይመስላል። በ24 ነጥብ 10ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከሰንጠረዡ አናት ይልቅ ለወራጅ ቀጠናው ቀርቦ የመገኘቱ ጉዳይ ለክለቡ ሰዎች ከፍተኛ ስጋትን ፈጥሯል።
በተመሳሳይ ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከወልቂጤ ከተማ ካገኙት የፎርፌ ውጤት ውጪ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ የተቸገሩት ባህር ዳር ከተማዎች በተመሳሳይ 24 ነጥብ በሊጉ በ9ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
በክረምቱ የዝውውር መስኮት ጠንካራ ቡድንን ለመገንባት በማሰብ ቡድናቸው ላይ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ያፈሰሱት ባህር ዳር ከተማዎች ሜዳ ላይ እየተመለከቱት የሚገኘው ውጤት ከቡድኑ የውድድር ዘመን ዕቅድ ጋር እስካሁን መጣጣም ያለመቻሉ ነገር በአሰልጣኙ ላይ ጥያቄዎችን ያስነሳ ሆኗል።