ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 19ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

በመጨረሻው የዐበይት ፅሁፋችን ሌሎች በሳምንቱ ትኩረት የሳቡ ጉዳዮች ተጠናቅረዋል።

👉 አነጋጋሪ የነበሩ የዳኝነት ውሳኔዎች…

በጨዋታ ሳምንቱ ከተደረጉት ጨዋታዎች መካከል ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመከላከያ እንዲሁም አዲስ አበባ ከተማ ከፋሲል ከነማ ያደረጓቸው ጨዋታዎች አነጋጋሪ የዳኝነት ውሳኔዎችን ያስተዋልንባቸው ነበሩ።

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመከላከያ ጋር ያለግብ አቻ በተለያዩበት ጨዋታ 70ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ ከግራ መስመር ያሻማውን የቅጣት ምት ፍሪምፖንግ ሜንሱ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብ የላካትን ኳስ ክሌመንት ቦዬ መስመር ካለፈች በኋላ በእጁ ቢመልስም ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት የመሩት ኢንተርናሽናል የመሀል ዳኛ ቴዎድሮስ ምትኩ እና የመስመር ዳኛው ኢንተርናሽናል ረዳት ዳኛው ተመስገን ሳሙኤል ሳያፀድቁት ቀርተዋል።

በሌላ በኩል አዲስ አበባ ከተማ ከፋሲል ከነማ ጋር ሁለት አቻ በተለያዩበት ጨዋታ በ73ኛው ደቂቃ እንዳለ ከበደ ከቀኝ የሳጥኑ ወገን ወደ ውስጥ ያሻማውን ኳስ የፋሲል ከነማው የመሀል ተከላካይ ከድር ኩሊባሊ ኳስ በእጅ ነክቷል በሚል ጨዋታውን የመሩት አልቢትር ባምላክ ተሰማ ለአዲስ አበባዎች የፍፁም ቅጣት ምት የሰጡ ሲሆን አጋጣሚዋንም ፍፁም ጥላሁን ወደ ግብ ቀይሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል።

ሁለቱም የዳኝነት ውሳኔዎች በጨዋታው ውጤት ላይ ዓይነተኛ አስተዋጽኦ እንደነበራቸው ባይካድም አሁንም ቢሆን ዳኞችን በቴክኖሎጂ ሊታገዙ የሚችልበትን አግባብ መፍጠር እስካልተቻለ ድረስ መሰል ስህተቶች በጨዋታዎች ላይ ተፅዕኗቸው የሚቀንስ አይመስልም።

👉 የተሻሻለው የወላይታ ድቻ መለያ ንድፍ

ከትጥቆች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ጥያቄ ይነሳበት የነበረው ወላይታ ድቻ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በ”ጎፈሬ” በተመረተ አዲስ መለያ ብቅ ብሏል።

በ2006 የውድድር ዘመን አንስቶ በፕሪሚየር ሊግ እየተሳተፈ የሚገኘው ቡድኑ ከ2008 ጀምሮ ተመሳሳይ ንድፍ ያለውን መለያ ጥቅም ላይ ሲያውል የቆየ ሲሆን በዚህ የውድድር ዘመን የሊጉ የስያሜ መብት ባለቤት የሆነው ቤትኪንግ የስፖርት ውርርድ ተቋም ያሰራላቸውን መለያ ከሁለተኛው ዙር ጅማሮ አንስቶ ጥቅም ላይ ቢያውሉም ከመለያው ቀለም ጋር በተያያዘ በደጋፊዎቻቸው ዘንድ ቅሬታን ስለመፍጠሩ ስንታዘብ ቆይተናል።

በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግን ቡድኑ የተጠቀመው መለያ የቀደመውን ወደ ቢጫነት ያደላውን አረንጓዴ ቀለም ያለው እና በደጋፊዎች የሚወደደውን መለያ ሲሆን አዲስ በጎፈሬ የቀረበው መለያ በተወሰነ መልኩ የንድፍ ማሻሻያዎችም የተደረጉበት ነበር።

ትላንት በ”ጎፈሬ” እና በወላይታ ድቻ ስፖርት ክለብ መካከል ይፋዊ ስምምነት ሲፈፀም እንደተገለፀው “የጦና ንቦች” በሚል መጠረያ የሚታወቀው ቡድኑ ይህን ታሳቢ በማድረግ በጥቁር ቀለም የማር እንጀራን የሚወክል ፓተርን በመለያው እና ቁምጣው የታችኛው ክፍሎች ላይ አርፎበት ተመልክተናል።

ለዘመናት ሳይለወጥ ጥቅም ላይ የዋለውን መለያ አሁን ላይ በ”ጎፈሬ” የተወሰነ መሻሻሎች ተደርገውበታል የመጣ ሲሆን ሁለቱ ተቋማት በጋራ መስራት መጀመራቸውን ተከትሎ በቀጣይ ወደ 10ሺህ የሚጠጉ መለያዎች ለደጋፊው እንደሚቀርብ ይጠበቃል።

👉 የሰበታ ከተማ ቁምጣ ጉዳይ

በእግር ኳስ ታሪክ ከተመለከተናቸው በቁምጣ ላይ ከሰፈሩ ቁጥሮች የሰበታ ከተማ መለያው ምናልባት ትልቁ ሳይሆን አይቀርም።

ከሁለተኛው ዙር አንስቶ በ”UMBRO” የተመረተን መለያ እየተጠቀሙ የሚገኙት ሰበታ ከተማዎች እንደሌሎች ክለቦች ሁሉ በመለያው ላይ በፍላጎታቸው ስያሜ እና ቁጥር ያፃፉ ሲሆን በተለይ በቁምጣው ላይ የሰፈረው ቁጥር የ”Font Size” ትኩረት የሚስብ ነው።

እርግጥ በመለያው ጀርባ ላይ የሰፈረው ቁጥርም ቢሆንም በመጠኑም ገዘፍ ያለ መጠን ያለው ሲሆን በቁምጣው ላይ የሰፈረው ደግሞ ከተለመደው መጠን እጅግ የገዘፈፈው ሆኖ ተመልክተናል።

በመጠናቸው ያነሱ የመለያ ላይ ፅሁፎች አሁን ደግሞ ከመጠን ያለፉ የመለያ ፅሁፎችን እያስተዋልን የምንገኝ ሲሆን ይህን ለመቅረፍ የሊጉ አክሲዮን ማህበር ወጥ የሆነ የአፃፃፍ መጠን እና ዓይነትን የሚደነግጉ ደንቦችን ቢያወጣ ተመራጭ ይሆናል።

ያጋሩ