ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ | የ19ኛ ሳምንት ምርጥ 11

የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የ19ኛ ሳምንት ጨዋታዎችን መሰረት በማድረግ የሳምንቱን ምርጥ ቡድን እንዲህ አሰናድተናል።

አሰላለፍ 4-3-3

ግብ ጠባቂ

ክሌመንት ቦዬ – መከላከያ

ጋናዊው ግብ ጠባቂ ክሌመንት በሳምንቱ ካየናቸው ምርጥ ዘቦች ግንባር ቀደሙ ነው። ለወትሮ የትኩረት ማነስ እና የውሳኔ ችግሮች የነበረበት ተጫዋቹ ቡድኑ ከሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ተጫውቶ ነጥብ ሲጋራ አምስት ዒላማቸውን የጠበቁ እና ለግብነት የቀረቡ ሙከራዎችን ሲያመክን ነበር።

ተከላካዮች

ሄኖክ አዱኛ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

በግራ መስመር የፈረሰኞቹ የተከላካይ መስመር ቦታ ላይ የተሰለፈው ሄኖክን በሁለቱም ኮሪደሮች መጫወት መቻሉን ከግምት በማስገባት ወደ ቀኝ አምጥተነዋል። በመከላከያው ጨዋታ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የጊዮርጊስ የግብ ሙከራዎች ከሄኖክ ጊዜያቸውን የጠበቁ ድንቅ የቆሙ ኳሶች መነሻቸውን ያደረጉ ነበሩ።

ኡቸና ማርቲን – አርባምንጭ ከተማ

በሳምንቱ ከተደረጉ ጨዋታዎች ጥብቅ መከላከል አድርጎ ሙሉ ነጥብ በማሳካት አርባምንጮች ቀዳሚ ነበሩ። በዚህ የቡድኑ አቀራረብ ውስጥ በአንድ ለአንድ ግንኙነት እጅግ ንቁ የነበረው ማርቲን ባህር ዳሮች ወደ ተሻጋሪ ኳሶች ባደሉባቸው የሁለተኛ አጋማሽ ደቂቃዎችም የአየር ላይ ኳሶችን ሲያፀዳ ነበር።

ተስፋዬ መላኩ – ጅማ አባ ጅፋር

ጅማ በድሬዳዋ በተሸነፈበት ጨዋታ 80 ደቂቃዎችን ከሦስቱ የኋላ መስመር ተሰላፊዎች የግራው ወገን ላይ የነበረው ተስፋዬ የድሬዳዋን አጥቂዎች በመልሶ ማጥቃት ወቅት ጥሩ ሲቆጣጠር እና የአደጋ ኳሶችን በአግባቡ ሲያርቅ ነበር። ምንአልባትም ተጫዋቹ በነበረው ዕለታዊ ብቃት ሜዳ ውስጥ ቢኖር ሁለተኛውን ጎል የወለደው የቡድኑ ስህተት ላይፈጠርም በቻለ ነበር።

ዳዊት ማሞ – መከላከያ

ከዚህ ቀደም በመስመር አጥቂነት የሚታወቀው ዳዊት በመከላከያ የግራ መስመር ተከላካይነቱ ቀጥሏል። በዚህ ሳምንት በሜዳው ቁመት ከፊቱ ከነበረው ቢኒያም በላይ ጋር ጥሩ ጥምረት የፈጠረው ዳዊት በቅዱስ ጊዮርጊስ የቀኝ የማጥቃት ክፍል የሚነሱ ጥቃቶችን በማቋረጥ ረገድ ጥሩ የጨዋታ ጊዜ አሳልፏል።

አማካዮች

ዳንኤል ደምሱ – ድሬዳዋ ከተማ

ድሬዳዋ ከ8 ጨዋታዎች በኋላ ድል ሲያገኝ የአምበሉ ዳንኤል ብቃት ጥሩ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ ለመከላለል ባሰበው እንዲሁም በሁለተኛው አጋማሽ ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ጠጋ ለማለት በሞከረው ቡድን ውስጥ ተጫዋቹ ከኳስ ጋር በማደራጀቱ ረገድ ከኳስ ውጪ ደግሞ በማጨናገፍ የነበረው ተሳትፎ በምርጥ ቡድናችን እንዲገባ አድርጎታል።

ሮቤል ተክለሚካኤል – ኢትዮጵያ ቡና

ከሳጥን ሳጥን ከኳስ ጋር እና ውጪ በመሮጥ፣ የአማካይ መስመሩን ከአጥቂው ጋር በማገናኘት እንዲሁም የዘገዩ የሳጥን ውስጥ ሩጫዎችን በማድረግ አስደናቂ የሆነው ሮቤል ባሳለፍነውም ሳምንት በዚህ ሚና ደምቆ አምሽቷል። ተጫዋቹ ዋና ሀላፊነቶቹ የሆኑትን ተግባራት በሜዳ ላይ ከመከወኑ በተጨማሪ የአሸናፊነት ጎሉን በማስቆጠሩ በምርጥ ቡድናችን ቦታ አግኝቷል።

ዊሊያም ሰለሞን – ኢትዮጵያ ቡና

በቡና የቀኝ መስመር አጥቂ ቦታ ላይ የዚህንም ሳምንት ጨዋታ ያደረገው ዊሊያም ቦታው የተመቸው ይመስላል ፤ ሆኖም በምርጥ ቡድናችን ውስጥ የቀደመው የስምንት ቁጥር ቦታው ላይ ሰይመነዋል። ዊሊያም ከኳስ ጋር ከመስመር በመነሳት ኳስ እየገፋ ተጫዋቾችን ይቀንስ የነበረበት መንገድ ትኩረት የሚስብ ሲሆን ድንገተኛ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳሶቹም ለቡድኑ የማጥቃት አማራጭ ፈጥረዋል ፤ የሮቤል ብቸኛ ጎል ሲቆጠር እንቅስቃሴው የጀመረውም ከዊሊያም እግር ነበር።

አጥቂዎች

ዑመድ ኡኩሪ – ሀዲያ ሆሳዕና

2006 ላይ የሊጉ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የነበረው ዑመድ ከግብፅ ቆይታ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝቷል። ቡድኑ ሀዲያ አዳማን በረታበት ጨዋታ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ድንቅ የነበረው ተጫዋቹ የቀደመ ፍጥነት እና ስልነቱን ያገኘ መስሎ በአጥቂዎቹ ወጥ ብቃት ለተቸገረው ቡድን አለው ብሏል።

ኦኪኪ አፎላቢ – ፋሲል ከነማ

በርካታ አጥቂዎች ጎልተው በወጡበት ሳምንት ሁለት ኳሶችን ከመረብ ያገናኘው ተጫዋች ኦኪኪ አንዱ ነው። ምንም እንኳን ቡድኑ ፋሲል ከአዲስ አበባ ጋር አቻ ቢለያይም ወደ ጨዋታ የመለሳቸውን እና መሪ ያረጋቸውን ጎል የተከላካዮችን ስህተት እንዲሁም ድንቅ የቦታ እና ጊዜ አጠባበቁን ተጠቅሞ አስቆጥሯል።

ሳላዲን ሰዒድ – ሲዳማ ቡና

በይገዙ ቦጋለ የተንጠለጠለው የሲዳማ የግብ ምንጭ ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ አማራጭ ያገኘ መስሏል። በውድድር አጋማሹ የዝውውር መስኮት ቡድኑን የተቀላቀለው ሳላዲን በሰበታው ጨዋታ ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ ለተከላካዮች የራስ ምታት በመሆን ሐት-ሪክ በመስራት የሳጥን ውስጥ አንበሳነቱን ያስመሰከረበትን ድንቅ ምሽት አሳልፏል።

አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ – አርባምንጭ ከተማ

ባሳለፍነው ሳምንት 4-1 እየመራ ነጥብ የተጋራው አርባምንጭ ከተማ በ19ኛው ሳምንት ከባህር ዳር ሙሉ ነጥብ መውሰድ ችሏል። አሰልጣኝ መሳይ በሚታወቁበት ጥብቅ መከላከል ከስህተቱ ተምሮ የወትሮው አደረጃጀቱ ላይ የተገኘው አርባምንጭ ከባህር ዳር በሁሉም መስመሮች የተወረወረበትን ጥቃት በአግባቡ አምክኖ የ1-0 ውጤቱን በማስጠበቅ አሸንፎ ወጥቷል። ቡድኑን በአንድ ሳምንት ልዩነት ወደ ቀደመ ጥንካሬው በመመለሳቸውም አሰልጣኙን የሳምንቱ ምርጥ ብለናቸዋል።

ተጠባባቂዎች

ሳምሶን አሰፋ – አርባምንጭ ከተማ
ግርማ በቀለ – ሀዲያ ሆሳዕና
አማኑኤል እንዳለ – ሲዳማ ቡና
አቤል ከበደ – ድሬዳዋ ከተማ
ሀቢብ ከማል – አርባምንጭ ከተማ
ብሩክ በየነ – ሀዋሳ ከተማ
ፍቃዱ መኮንን – አርባምንጭ ከተማ

ያጋሩ