ቅድመ ዳሰሳ | ጅማ አባ ጅፋር ከ ኢትዮጵያ ቡና

የ20ኛውን ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታ የተመለከተው ዳሰሳችን እንዲህ ይነበባል።

በተለያየ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የሚገኙት ሁለቱ ቡድኖች ሲገናኙ ጅማ አባ ጅፋር እስትንፋሱን ለማራዘም ኢትዮጵያ ቡና ደግሞ ይበልጥ ወደ ላይ ለመውጣት ይገናኛሉ። የጨዋታው ነጥቦች ከበላዮቹ ጋር ያለውን ልዩነት ለማጥበብ እንጂ ደረጃ ለማሻሻል የማይጠቅሙት ጅማ በሊጉ የመቆየት ተስፋውን ለማለምለም አሁንም ከማሸነፍ ውጪ ሌላ ምርጫ ያለው አይመስልም። ተከታታይ ድሎችን ያሳካው ኢትዮጵያ ቡናም በተመሳሳይ ማሸነፍ ስድስተኛ ደረጃ ላይ እንዲረጋ እና ከላይ ወዳሉት አምስት ቡድኖች እንዲቀርብ ብቻ ያግዘዋል ፤ በትክክል ወደ ላይኛው የፉክክር እርከን መሸጋገሩን ለማወጅ ግን የተከታታይ ድሎቹን ቁጥር መጨመር ያስፈልገዋል።

ጅማ አባ ጅፋር አሁንም መሻሻሉን በውጤት ማጀብ ሳይችል 20ኛው ሳምንት ላይ ደርሷል። ነገ ደግሞ በመጨረሻ ጨዋታው ከገጠመው ድሬዳዋ ከተማ በተለየ መልኩ በኳስ ቁጥጥር ድርሻ የሚፈታተነው ቡድን ይጠብቀዋል። በእርግጥ ድሬዳዋ ባልታሰበ ሁኔታ መልኩን ቀይሮ የመልሶ ማጥቃት ባህሪን ተላብሶ ቢመጣም ወጥ አጨዋወት በሚከተለው ኢትዮጵያ ቡና በኩል ግን መሰል ለውጦች አይጠበቁም። በመሆኑም የቀድሞው ቡድናቸውን በሚገጥሙት የመስዑድ እና ዳዊት ጥምረት የሚመራው የጅማ የአማካይ ክፍል በኳስ ቁጥጥር መነሻነት ጨዋታውን በሚፈልገው አግባብ የማስኬድ ፈተና ይጠብቀዋል። ይህ ካልሆነም ደግሞ እንዳለፈው ሳምንት ድሬዳዋ ከእስካሁኑ የተለየ ያልተገመተ አቀራረብ እና የጨዋታ ዕቅድ ይዞ መምጣት የግድ ይለዋል።

አዲስ ፈራሚ ተጫዋቾቹን ጭምር በየሳምንቱ በሚቀያየር የሜዳ ላይ ኃላፊነት እየተጠቀመ የሚገኘው ጅማ ለማጥቃት ሂደት ወሳኝ የሆነ ወጥ መዋቅር ይዞ አለመቀጠሉ የጎዳው ይመስላል። በቅርብ ሳምንታት ብቻ እንደ እዮብ ፣ አስጨናቂ ፣ ቦና እና ሱራፌል የመሳሰሉ ተጫዋቾች የሚና ለውጥ አድርገው ታይተዋል። ለአብነት ፊት መስመር ላይ ተስፋ ፈንጥቆ የነበረው የመሀመድኑር እና የኢዮብ ጥምረት ይበልጥ እየጎለበተ ይሄዳል ተብሎ ቢጠበቅም በዚሁ የሚና መለዋወጥ ሳቢያ አሁን ላይ መታየት አቁሟል። ነገም በጅማ በኩል መሰል ለውጦች ሊታዩ እንደሚችሉ ሲጠበቅ ቡድኑ ከመጨረሻ ጨዋታው የሚወስደው ብቸኛ መልካም ነገር የዳዊት ፍቃዱ ወደ ግብ አስቆጣሪነት መምጣት ይመስላል።

ያለፉት ሁለት ዘጠና ደቂቃዎች ለኢትዮጵያ ቡና ሁለት የሜዳ ጫፎች ጥሩ ሆነው ያለፉ ነበሩ። ቡድኑ ኳስ መስርቶ ለመውጣት በሚያደርገው ጥረት ውስጥ በራሱ አጋማሽ ከሚሰራቸው ስህተቶች ለተጋጣሚዎች የሚፈጠሩ ዕድሎች ቀንሰዋል። ከፊትም ከራሱ ሜዳ ከወጣ በኋላ ሜዳውን አስፍቶ ወደተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ በቁጥር በርክቶ የሚገኝባቸው አጋጣሚዎች ዳግም መታየት ጀምረዋል። በእርግጥ ቡና ውጤት አጥቶ መሰንበቱ የፈጠረው ተፅዕኖ በሚመስል መልኩ በጨዋታ የተወሰኑ ደቂቃዎች ላይ በተረጋጋ ሁኔታ ኳስ መያዝ እና ጨዋታውን የመቆጣጠር ሂደት ላይ ደከም ብሎ የሚታይባቸው ጊዜያት አይጠፉም።

ቡና በተለይም ያለአቡበከር ናስር ይህንን ጨዋታን በራስ ቁጥጥር ስር የበላይ ሆኖ የማስኬድ የበላይነትን ከእጁ የሚያጣባቸው ቅፅበቶች ነገም ለጅማ አባ ጅፋር በር ከፋች ቢሆኑም በዚህ ውስጥ የቡድኑ ጠንካራ ጎን እየሆኑ ያሉትን የዊሊያም እና ሮቤልን ወቅታዊ ብቃት ማንሳት ግን አስፈላጊ ነው። ወደ መስመር አጥቂነት የተቀየረው ዊሊያም ኳስ እየገፋ ተጫዋቾችን በማለፍ ሳጥን ውስጥ የሚዘልቅበት አኳኋን ቡና ተደጋጋሚ ጫና እንዲፈጥር ሲያደርግ ይታያል። ነገም በድሬው ጨዋታ ደካማ በነበረው በጅማ ሦስት ተካላካዮች የቀኝ ወገን ይህ ፍልሚያ ይጠበቃል። ተከታታይ ጨዋታዎች ላይ ግብ ያስቆጠረው ሮቤልም የቡድኑን የማጥቃት ፍሰት ተከትሎ ሳጥን ውስጥ የሚገኝበት ጊዜ እና ቦታ ለቡድኑ የወገብ በላይ ገፅታ ሌላ አዎንታዊ መልክ እየሰጠው መገኘቱ በነገውም ጨዋታ የሚፈጥረው ልዩነት ይጠበቃል።

በወቅታዊ አቋም ዙሪያ ይህ ጨዋታ በሁለቱ ግቦች መሀል የሚቆሙ በአሁናዊ ብቃታቸው ዙሪያ ድንቅ የሆኑ ግብ ጠባቂዎችንም ያገናኛል። ያለቀላቸው በተባሉ የአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ከአጥቂዎች ጋር እየተገናኘ በአስደናቂ ሁኔታ በተደጋጋሚ የበላይ ሲሆን የሚታየው አላዛር ማርቆስ ወይስ የመጨረሻ የግብ ዕድሎችን በቅልጥፍና በማዳን ቡናን ደጋግሞ የታደገው እና ቡድኑ በሚፈልገው መንገድ በእግሩ ኳስ የሚያስጀምረው በረከት አማረ ? በነገው ጨዋታ ማን ልዩነት ይፈጥራል የሚለው ጉዳይ ተጠባቂ ነው።

ሙሴ ካበላን በቅጣት የሚያጣው ጅማ አባ ጅፋር ጉዳት ላይ የሰነበተው ኢያሡ ለገሰ ወደ ልምምድ የተመለሰለት ሲሆን ዘንድሮ እምብዛም ግልጋሎት ያልሰጠው ሮባ ወርቁ ጉዳት ላይ ይገኛል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል በቅጣት የሚጣው ተጫዎች ባይኖርም በጉዳት ወንድሜነህ ደረጀ ፣ አቤል እንዳለ ፣ የአብቃል ፈርጃ ፤ ስዩም ተስፋዬ እና አቡበከር ናስር አይኖሩም።

ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት አዳነ ወርቁ ፣ በረዳት ዳኝነት ይበቃል ደሳለኝ እና እሱባለው መብራቴ በአራተኛ ዳኝነት ደግሞ ዓባይነህ ሙላት ይመሩታል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ በሰባት ጨዋታዎች ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና ሦስት ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ ሁለት ድሎችን ሲያስመዘግቡ ሁለት ጊዜ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በጨዋታዎቹ ቡና ሰባት ጅማ ደግሞ ስድስት ግቦችን አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

ጅማ አባ ጅፋር (3-6-1)

አላዛር ማርቆስ

ኢያሱ ለገስ – የአብስራ ሙሉጌታ – ተስፋዬ መላኩ

እዮብ ዓለማየሁ – አድናን ረሻድ – አስጨናቂ ፀጋዬ – ዳዊት እስጢፋኖስ – መስዑድ መሐመድ – ሱራፌል ዐወል

መሐመድኑር ናስር

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

በረከት አማረ

ኃይሌ ገብረትንሳይ – አበበ ጥላሁን – ገዛኸኝ ደሳለኝ – አስራት ቱንጆ

 ታፈሠ ሰለሞን – አማኑኤል ዮሐንስ –  ሮቤል ተክለሚካኤል

ሚኪያስ መኮንን – እንዳለ ደባልቄ – ዊሊያም ሰለሞን

ያጋሩ