በ20ኛው ሳምንት ሁለተኛ ቀን ከቀትር በኋላ የሚደረገውን ጨዋታ የተመለከቱ ነጥቦችን እንደሚከተለው አንስተናል።
በደረጃ ሰንጣረዡ የላይኛው እና የታችኛው ፉክክር ላይ ተፅዕኖ የሚኖሮው ጨዋታ ከውጤት አንፃር ለሁለቱም ዋጋው ከፍ ያለ በመሆኑ ጠንከር ያለ ፉክክር እንደሚያስተናግድ ይጠበቃል። በዋንጫ ፉክክሩ ውስጥ ቢገኝም ሙሉ ነጥብ ካሳካ ሦስት ጨዋታዎች ያለፉት ወላይታ ድቻ ነገ ድልን ካላሳካ ከበላዩ ካሉት ሦስት ክለቦች መራቅ ብቻ ሳይሆን የአራተኝነት ደረጃውንም ሊያጣ ይችላል። ዛሬ የጅማን ነጥብ መጋራት ተከትሎ በዚህ ጨዋታ አንድ ደረጃ የማሻሻል በር የተከፈተለት ሰበታ ከተማም ቢሆን ሽንፈት ከገጠመው የመትረፍ ተስፋውን እያከሰመ ለመሄድ ይገደዳል። በመሆኑም አንዱ ራሱን በዋንጫ ፉክክር ውስጥ ለማቆየት ሌላኛው ደግሞ ራሱን በሊጉ ለማቆየት የሚያደርጉት ፍልሚያ ይሆናል።
ወላይታ ድቻ ከሁለተኛው ዙር መጀመር አንስቶ በጨዋታ አቀራረቡ ላይ ለውጦች እየታዩበት ይገኛል። ሆኖም ማጥቃትን በመቀላቀል ከቀደመው ጊዜ በመጠኑ ለቀቅ ብሎ የሚታየው ቡድኑ አሁንም ቢሆን ነገሮችን ከተጋጣሚዎቹ አንፃር መቃኘቱ እንደቀጠለ ነው። በተለይ በኢትዮጵያ ቡና በተረታበት የመጨረሻው ጨዋታ ከቀደሙት ሁለት ጨዋታዎች ይልቅ ወደ ጥንቃቄው አምዝኖ ነበር። ከነገ ተጋጣሚው ወቅታዊ ደረጃ አንፃር ግን ወላይታ ድቻ ከኳስ ቁጥጥሩም ከፈጣን ጥቃቱም የቀላቀለ አካሄድ እንደሚኖረው ይጠበቃል።
ሰበታ ከተማ አሀንም በኳስ ቁጥጥር ላይ ተመስርቶ የግብ ዕስሎችን ለመፍጠር ከመጣር አልቦዘነም። ነገር ግን ከፍ ያለ የቡድን ውህደት በሚጠይቀው የጨዋታ ምርጫው በሚፈለገው ልክ የግብ ዕድሎችን መፍጠርም ሆነ የተገኙትን የመጨረሽ ችግሩ አብሮት እንደዘለቀ ነው። በመሆኑም ጥሩ ተስፋ ከሰጠበት የመከላከያው ጨዋታ ድል በኋላ በድጋሚ ወደ ተከታታይ ሽንፈት ተመልሷል። ከመጣበት መንገድ አንፃር ስንመለከተው ግን ቡድኑ ነገም በወላይታ ድቻ ላይ ከፍ ያለ የኳስ ቁጥጥር ድርሻን ለማሳከት የሚያልም ይመስላል።
በጨዋታው ወላይታ ድቻም ኳስ መስርቶ የመውጣት አዝማሚያ ሊኖረው ቢችልም በፈጣን ጥቃት ለተጋጣሚው የኳስ ፍሰት ምላሽ መስጠቱ የሚቀር አይመስልም። በዚህም መሀል ለመሀል በሚሰነዘርበት ጥቃት በንጋቱ እና ሙሉጌታ ጥምረት ኳሶችን ማቋረጥ እና ወደ ቀኝ መስመር በያሬድ ዳዊት በኩል አመዝኖ ፈጠን ያሉ የማጥቃት ሽግግሮችን ለመተግበር መጣሩ የቡድኑ ዋነኛ የማጥቃት አማራጭ ሊሆን ይችላል።
በሰበታ ከተማ በኩል በተመሳሳይ አመዛኙ ጥቃት ከግራው ወገን ሊነሳ ይችላል። ቡድኑ በርከት ያሉ ቅብብሎችን በመከወን ወደ ተጋጣሚው ሜዳ የሚቀርብበት አግባብ ቢኖርም በዱሬሳ የሚመራው የግራ ማጥቃት ለመጨረሻ ኳሶች መነሻ ሊሆን ይችላል። በዚህ አኳኋን ወላይታ ድቻ በቦታው ከሚጠቀመው የሜዳ ቁመት ጠንከር ያለ የመከላከል ጥምረት አንፃር ትኩረት ሳቢ ፍልሚያዎችን ልንመለከት እንችላለን።
በጨዋታው ወላይታ ድቻ እንድሪስ ሰዒድን በቅጣት ስንታየሁ መንግሥቱን በጉዳት የማይጠቀም ሲሆን አንተናህ ናደው ከህመም ጌቱ ኃይለማሪይም ከቅጣት የተመለሱለት ሰበታ ከተማ ደግሞ ዘካሪያስ ፍቅሬ እና ዮናስ አቡሌን በጉዳት ምክንያት አያሰልፍም።
ጨዋታው በዓባይነህ ሙላት የመኃል ዳኝነት ሲከናወን ክንፈ ይልማ እና ተስፋዬ ንጉሴ በረዳትነት ዳንኤል ግርማይ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ቡድኖቹ እስካሁን ባደረጓቸው ሦስት ጨዋታዎች በሁለቱ ነጥብ ሲጋሩ ወላይታ ድቻ በዘንድሮው የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ አሸንፏል። በጨዋታዎቹ ወላይታ ድቻ ስድስት ሰበታ ከተማ አራት ግቦችን አስመዝግበዋል።
ወላይታ ድቻ (4-3-3)
ፅዮን መርዕድ
በረከት ወልደዮሐንስ – አንተነህ ጉግሳ – መልካሙ ቦጋለ – አናጋው ባደግ
ሀብታሙ ንጉሴ – ንጋቱ ገብረስላሴ – አበባየሁ አጪሶ
ያሬድ ዳዊት – ምንይሉ ወንድሙ – ቃልኪዳን ዘላለም
ሰበታ ከተማ (4-3-3)
ምንተስኖት አሎ
ጌቱ ኃይለማሪያም – በረከት ሳሙኤል – አንተነህ ተስፋዬ – ኃይለሚካኤል አደፍርስ
ሳሙኤል ሳሊሶ – በኃይሉ ግርማ – አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ
ዴሪክ ኒስባምቢ – ፍፁም ገብረማርያም – ዱሬሳ ሹቢሳ