ቅድመ ዳሰሳ | መከላከያ ከ ባህር ዳር ከተማ

በግልባጩ የደረጃ ሰንጠረዥ የሚገኙት መከላከያ እና ባህር ዳር ከተማ የሚያደርጉት ጨዋታ እንዲህ ተቃኝቷል።

ድል ካደረገ ስድስት ጨዋታዎች ያለፉት መከላከያ የናፈቀውን ሦስት ነጥብ አግኝቶ ካለበት የወራጅነት ስጋት በመጠኑም ቢሆን ለመላቀቅ እንደሚጥር ሲጠበቅ ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች ወልቂጤ ላይ ካገኘው የፎርፌ ውጤት ውጪ በእንቅስቃሴ አንድም ጨዋታ ያላሸነፈው ባህር ዳር ከተማም ድልን እያሰላሰለ ደረጃ እና ነጥቡን ለማሻሻል ጠንክሮ እንደሚጫወት ይጠበቃል።

ለተጋጣሚ ቡድኖች ከልክ ያለፈ አክብሮት በመስጠት ለመከላከል ቅድሚያ ሲሰጥ የምንመለከተው መከላከያ ባሳለፍነው ሳምንት የሊጉን መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ገጥሞ ያለ ግብ አቻ መውጣቱ የሚደነቅ ነው። በጨዋታው አብዛኛውን ክፍለ ጊዜ ዝቅ ብሎ ለመከላከል የጣረው ቡድኑም ወደ ጎንም ሆነ ወደ ፊት ችምችም ብሎ መሮጫ ቦታ የሚፈልጉትን የአሠልጣኝ ዘሪሁን ተጫዋቾች ምቾት ነፍጎ ነበር። ከተከላካዮቹ አልፈው የሚገኙ ዕድሎችንም በጨዋታው ድንቅ የነበረው የግብ ዘብ ክሌመንት ቦዬ በማዳን ጥሩ የጨዋታ ቀን አሳልፈው ነበር። የነገው ተጋጣሚያቸው ባህር ዳርም የጊዮርጊስን ያህል አይሁን እንጂ ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ተጠግቶ መጫወት የሚፈልግ ስለሆነ በተመሳሳይ አቀራረብ ወደ ሜዳ እንደሚገቡ ይጠበቃል። በተለይ ከወራጅ ቀጠናው ክለቦች ውጪ ብዙ የተረታ ክለብ (ከድሬዳዋ ጋር በጣምራ) ስለሆነም ተቀዳሚ ዓላማው አለመሸነፍን አድርጎ ሊንቀሳቀስ ይችላል።

ባህር ዳር ከተማ በበኩሉ ድባቴ ውስጥ ያለ ክለብ ይመስላል። ባሳለፍነው ሳምንትም ወልቂጤ ላይ ያገኘውን የፎርፌ ውጤት በእቅስቃሴ ድል ያስቀጥላል ተብሎ ቢጠበቅም በአርባ ምንጭ ከተማ ሽንፈት አስተናግዷል። እርግጥ አርባ ምንጭ በጨዋታው ያን ያህል ባህር ዳርን አስጨንቆ ባይጫወትም በጥቂት አጋጣሚዎች ብቻ ወደ ግብ በመድረስ ኳስ እና መረብን በማገናኘት በእጁ የገባውን ሦስት ነጥብ ማስታመም ላይ ተጠምዶ ጨዋታውን አገባዷል። በተለይ በራሱ ሜዳ አጥቦ በመከላከል ባህር ዳር የግብ ማስቆጠሪያ አማራጭ እንዳይኖረው አድርጓል። የባህር ዳር የነገው ተጋጣሚም ባሳለፍነው ሳምንት አርባ ምንጭ በተከተለው የጨዋታ መንገድ መቅረብ የሚፈልግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ደግሞ ነገም የአሠልጣኝ አብርሃም ተጫዋቾች እንዳይቸገሩ አስግቷል።

ተጋጣሚ ላይ ግብ ካስቆጠረ 492 ደቂቃዎች ያለፉት መከላከያ ባለፉት ጨዋታዎች ግብ ለማስቆጠር በተደጋጋሚ የመጨረሻው የማጥቃት ሲሶ ላይ ለመድረስ ሀሳብ ባይኖረውም ቀጥተኝነትን ግን እንደ ዋነኛ የግብ ምንጭነት ለመጠቀም ይሞክራል። ይህ አጨዋወት ነገም እንደሚደገም ሲጠበቅ በተጨማሪም ግለሰባዊ የውሳኔ እና አቋቋም ህፀፆች የማይጠፉበት የባህር ዳር ተከላካዮችን ዒላማ ያደረገ የመልሶ ማጥቃትንም ሊሰነዝሩ ይችላሉ። በዚህም ቁመታሙ አጥቂ ባዳራ ሲይላን ያማከሉ አንደኛ እና ሁለተኛ ኳሶችን እያሸነፉ ለባህር ዳር ፈተና ሊሰጡ ይችላሉ። በተቃራኒው ባህር ዳርም ፈጣኖቹን አጥቂዎች በመጠቀም ውጤት ለማግኘት ይጥራል። በዋናነት የሜዳውን ስፋት ለመጠቀም በመሞከር ግጥግጥ ብሎ እንደ ስሙ የሚከላከለውን የመከላከያ የኋላ መስመር ለመዘርዘር የመስመር ላይ ሩጫዎችን ማዘውተሩ አይቀርም። ይህ ቢሆንም ግን እንደ አርባ ምንጩ ጨዋታ ዕድሎችን የሚያመክኑ ከሆነ ዋጋ ሊከፍሉ ይችላሉ።

መከላከያ በነገው ጨዋታ ሰመረ ሀፍታይን እና አሌክስ ተሰማን በጉዳት ምክንያት የማያገኝ ሲሆን በጊዮርጊሱ ጨዋታ ባለቀ ሰዓት ቁርጭምጭሚቱ ላይ ጉዳት አስተናግዶ የነበረው አሚን ነስሩ ግን ለጨዋታው ዝግጁ ሆኗል። ባህር ዳር ከተማ በበኩል በጉዳትም ሆነ በቅጣት ምክንያት የሚያጣው ተጫዋች የለም።

ይህንን ጨዋታ ማኑኤ ወልደፃዲቅ በመሐል አልቢትርነት ሲመሩት ሙስጠፋ መኪ እና ፋንታሁን አድማሱ ረዳት ሔኖክ አክሊሉ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው የሚመሩት ይሆናል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– መከላከያ እና ባህር ዳር ከተማ ነገ ለአራተኛ ጊዜ በሊጉ ይገናኛሉ። ከዚህ ቀደም በነበረው የሦስት ጊዜ ግንኙነት ባህር ዳር ያላሸነፈ ሲሆን መከላከያ ሁለት ጊዜ አሸንፎ አንዱን ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በሦስቱ ጨዋታዎች ከተቆጠሩት አምስት ጎሎች ደግሞ መከላከያ አራቱን ባህር ዳር ቀሪዋን አንድ ግብ አስቆጥረዋል።

ግምታዊ አሠላለፍ


መከላከያ (4-4-2)

ክሌመንት ቦዬ

ገናናው ረጋሳ – ኢብራሂም ሁሴን – አሚኑ ነስሩ – ዳዊት ማሞ

ግሩም ሀጎስ – ኢማኑኤል ላርዬ – ምንተስኖት አዳነ – ቢኒያም በላይ

ተሾመ በላቸው – ባዳራ ናቢ ሲላ

ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)

ፋሲል ገብረሚካኤል

መሳይ አገኘሁ – ፈቱዲን ጀማል – መናፍ ዐወል – ሔኖክ ኢሳይያስ

ፍፁም ዓለሙ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ፉዐድ ፈረጃ

ዓሊ ሱሌይማን – ኦሴ ማውሊ – ግርማ ዲሳሳ