እጅግ ቀዝቃዛ በነበረው እና ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች እምብዛም በነበሩበት ጨዋታ ወላይታ ድቻ እና ሰበታ ከተማ ጨዋታቸውን በአቻ ውጤት ፈፅመዋል።
የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያሙ ወላይታ ድቻ በኢትዮጵያ ቡና የተረታውን ስብስብ ሳይለውጥ በዛሬው ጨዋታ የተጠቀመ ሲሆን በአንፃሩ በአሰልጣኝ ብርሃኑ ደበሌ የሚመሩት ሰበታ ከተማዎች ደግሞ በመጨረሻው ጨዋታ በሲዳማ ሽንፈት ሲያስተናግዱ ከተጠቀሙት ስብስብ ሦስት ለውጦችን አድርገዋል በዚህም ዓለማየሁ ሙለታ ፣ ቢያድግልኝ ኤልያስ እና ፍፁም ገብረማርያምን አስወጥተው ጌቱ ኃይለማርያም ፣ ጋብርኤል አህመድ እና ሳሙኤል ሳሊሶን በመተካት አስገብተዋል።
በእንቅስቃሴ ረገድ ሰበታ ከተማዎች የበላይ በነበሩት የሁለቱ ቡድኖች የመጀመሪያ አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ አመዛኙ የጨዋታ ክፍለ ጊዜን በወላይታ ድቻ አጋማሽ ያሳለፉት ሰበታ ከተማዎች የጠሩ የግብ አጋጣሚዎችን መፍጠር ግን ሳይችሉ ቀርተዋል።
በአጋማሹ ከቆሙ ኳሶች እና ከመስመር ከሚሻገሩ ኳሶች ጥቃት መሰንዘር የጀመሩት ሰበታዎች በ17ኛው ደቂቃ ሳሙኤል ሳሊሶ ከመስመር ያሻማውን ኳስ አብዱልሀፊዝ ቶውፊቅ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ የላካት እና ለጥቂት ወደ ውጭ የወጣችበት ኳስ አስቆጭ አጋጣሚ ነበረች።
በአጋማሹ ከመከላከል ባለፈ ይህ ነው የሚባል የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ ለመፍጠር የተቸገሩት ድቻዎች በ21ኛው ደቂቃ በቀጥተኛ ቅብብል አበባየሁ አጪሶ በግሩም ሁኔታ ያደረሰውን ኳስ ምንይሉ ወንድሙ ከሳጥን ጠርዝ አስቆጠረ ተብሎ ሲጠበቅ ያመከናት ኳስ እንዲሁም በ30ኛው ደቂቃ አበባየሁ አጪሶ ከሳጥን ውጭ በቀጥታ ሞክሮ ለጥቂት ከግቡ አናት በላይ የወጣችበት ኳስ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ።
ከውሃ እረፍት መልስ በተወሰነ መልኩ ሰበታ ከተማዎች የተቀዛቀዙ ሲሆን በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች በሰበታ ከተማ ተጫዋቾች መካከል በሚደረጉ ፈጣን ቅብብሎች ወደ ግብ ለመሄድ በመሞከር ረገድ ተሻሽለው ተመልክተናል ፤ በመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ በፈጣን መልሶ ማጥቃት ቃልኪዳን ዘላለም ከግራ የሳጥን ጠርዝ ወደ ውስጥ ያሳለፈለትን ኳስ ምንይሉ ወንድሙ ተንሸራቶ ለጥቂት ሳይደርሳባት በቀረችው አጋጣሚ አጋማሹ ያለ ግብ ተጠናቋል።
በሁለተኛው አጋማሽ እንደ መጀመሪያው ሁሉ ሰበታ ከተማዎች የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ሲሆን በአንፃሩ ወላይታ ድቻዎች ደግሞ አመዛኙን ጊዜ ከኳስ ውጭ ቢያሳልፉም በመልሶ ማጥቃት ግን እድል በመፍጠር ረገድ ደካማ ነበሩ።
የጨዋታ ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ግን ወላይታ ድቻዎች በመልሶ ማጥቃት ፍላጎት ረገድ ፍፁም መሻሻልን በማሳየት ወደ ማጥቃት በሚደረጉ ሽግግሮች ወቅት በቁጥር በርከት ብለው ወደ ሰበታ ሳጥን መጠጋት ጀምረዋል ፤ በተለይ የአጥቂ ተሰላፊዎች የውሳኔ አሰጣጥ ሆነ እንጂ በጣት የሚቆጠሩ አደገኛ የነበሩ አጋጣሚዎችን አግኝተው ነበር።
በጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ጫናቸው ያየለው ወላይታ ድቻዎች በመጨረሻዎቹ 10 ደቂቃዎች አደገኛ አጋጣሚዎችን የፈጠሩ ሲሆን በጨዋታው በሁለቱም አጋማሽ የተሻሉ ይመስሉ የነበሩት ሰበታዎች በመጨረሻዎቹ ደቂቃዎች ይበልጥ በመከላከሉ አተኩረው ጨዋታውን አገባደዋል።
በ82ኛው ደቂቄ አበባየሁ አጅሶ ከሳጥን ውጭ መሬት ለመሬት የመታውን ኳስ ምንተስኖት አሎ ሲያድንበት በ87ኛው ደቂቃ ደግሞ ከመስመር የተሻማን ኳስ ምንይሉ ወንድሙ ሳጥን ውስጥ ተቆጣጥሮ ወደ ግብ የላካትን ኳስ ምንተስኖት ሊያድንበት ችሏል።
ጨዋታው ያለ ግብ መጠናቀቁን ተከትሎ ወላይታ ድቻ በ34 ነጥብ ወደ ሦስተኛ ደረጃ ከፍ ሲሎ በአንፃሩ ሰበታ ከተማ ደግሞ በ13 ነጥብ አሁንም በሊጉ ግርጌ ላይ ይገኛሉ።