የአሰልጣኞች አስተያየት | ወላይታ ድቻ 0-0 ሰበታ ከተማ

ያለግብ ከተጠናቀቀው የዛሬው የመጀመሪያ ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማሪያም – ወላይታ ድቻ

ስለጨዋታው ፉክክር

“ትናንትም ጅማ ምን ያህል ፈታኝ እንደነበር አይተናል ለኢትዮጵያ ቡና። አሁን ላቻምፒዮና መሄዱ አይደለም ዋናው ችግር ሊጉ ላለመውሩድም አቅምህን አውጥተህ የምትጫወትበት ስለሆነ በአንዴ ሦስት ነጥብ የተሻለ ደረጃ ሊያስኬድም ስለሚችል ጠንካራ ፉክክር እንደሚኖር እናውቃለን። ሰበታ ከተማም ሜዳ ላይ የሚያሳየው እንቅስቃሴ እና ያለበት ደረጃ የሚገናኝ አይደለም። ጥሩ ቡድን ነው ፤ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች በየቦታ የያዘ ቡድን ነው። በዛ ላይ የወጪ ተጫዋቾችም አሏቸው እና ጠንካራ ፉክክር እንደሚገጥመን እናውቅ ነበር የታየውም እሱ ነው። በጣም ጥሩ ጨዋታ ታይቷል ብዬ ነው የማስበው። ትልቁ ችግራችን የነበረው የመጨረስ ችግር ነው እንጂ አሸንፈን መውጣት የምንችልባቸው አጋጣሚዎች ነበሩ። ያ አለመሆኑ ዋጋ አስከፍሎናል ማለት ይቻላል፤ ባተረፈ ግን ጥሩ ፉክክር ታይቷል ብዬ አስባለሁ።

ስለቡድኑ የማጥቃት ሽግግር

“የመጨረስ ችግር ነው። ዞሮ ዞሮ ሦስተኛው የሜዳ ክፍል ላይ በምንደርስበት ጊዜ ተረጋግቶ የማስቆጠር ፣ ከተከላካይ ራስን ነፃ ያለማድሩግ ፣ ከራስ የተሻለ ሌላ በጥሩ አቋቋም ላይ ላለ ሰው ኳስ ያለማዘጋጀት ፣ ችኮላዎች ፣ ያለቁ ኳሶች አለማዘጋጀት ፣ የኳሱን እና የአጥቂውን ፍጥነት ግምት ውስጥ አለማስገባት ዓይነት ችግሮች ነበሩብን። እነዚህ ናቸው ሽግግሩ ላይ የነበሩ ዕክሎች።

ስለዋንጫ ፉክክሩ

“ግልፅ ለመናገር የዋንጫ ቡድን ማለት ስህተት ቀንሶ የሚመጣ ቡድን ነው። ቅዱስ ጊዮርጊስ በሁሉም መስመሮች ላይ ስህተት ቀንሶ ይመጣል። ለዚህም ነው እያሸነፈ እና ነጥቦች እያያዘ የሚሄደው። ሌሎቻችን ጋር ግን የአጨራረስ ችግር ፣ አንዳንዴ የተከላካዮች ስህተት ይኖራል። እነዚህን በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አታገኝም። እኛ ሳምንት ከቡና ጋር ስንጫወት የሰራነው ስህተት ዋጋ አስከፍሎናል ፤ ግን ቀላል ስህተቶች ነበሩ። እኛ በራሳችን እንቅስቃሴ ብዙ ስህተቶች እየቀነስን አይደለም። የምናገኛቸውን ዕድሎች ካልተጠቀምን እና ስህተቶች ካልቀነስን ልንቸገር እንችላለን። አሁንም ካለን የሰው ኃይል አኳያ እየሞከርን ነው ያለነው። ይህንን ለማስቀጠል እንሞክራለን።”

አሰልጣኝ ብርሀን ደበሌ – ሰበታ ከተማ

ስለውጤቱ

“ሦስት ነጥብ በጣም እንደምፈልግ ተናግሬ ነበር። ይህንን ለማድረግ ደግሞ በመጀመሪያው አጋማሽ በርካታ ኳሶችን ስተናል። የአጨራረስ ችግር ነበር ልጆቼ ጋር። ሙሉ ዘጠና ደቂቃውን ለማጥቃት አልፎ አልፎ ሙከራ እያደረግን ነበር።

ስለአማካይ ክፍል ጥምረታቸው

“የድቻ አጨዋወት በጣም ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ስለሆነ ጂብሪል ቀረት እያለ በኃይሉ ደግሞ ወደ ፊት እየሄደ እንዲጫወት ነው ያደረግነው እንጂ ሁለት ሲኪመር ይመስላል። ነገር ግን በኃይሉ ወደ አብዱልሀቪዝ ተጠግቶ ማጥቃቱን እንዲያፋጥን ነው የተደረገው።

ከመስመር ሰብረው መግባት ስላለመቻላቸው

“በመስመር ላይ ያሉን ተጫዋቾች ባላቸው ተሰጥኦ አልፎ አልፎ ፈጥሮ የመግባት አቅም አላቸው። ነገር ግን ድቻዎች ተጠቅጥቀው ስለነበር ያንን ማድረግ አልቻሉም። ሁለተኛ ከፊት ሦስት ነው ያሰለፍነው ተደራቢ አጥቂዎቻችን እንደልብ መግባት ስላልቻሉ ያንን ነገር ሊገታው ችሏል።

ስለቡድኑ በሊጉ የመቆየት ዕድል

“እንደኔ ሀሳብ ይቆያል። ከጥረታችን ጋር ተያይዞ ፈጣሪ ከፈቀደ እንቆያለን የሚል ዕምነት አለኝ ፤ ቀሪውን ጨዋታ በማሸነፍ።”