ቅድመ ዳሰሳ | አዲስ አበባ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

በነገው የጨዋታ ቀን ቀዳሚ ግጥሚያ ላይ የሚያተኮረው ዳሰሳችንን እንዲህ አሰናድተናል።

አዲስ አበባ ከተማ ለአንድ ሳምንት ወጥቶ የነበረበት ወራጅ ቀጠና ውስጥ ተመልሶ በመግባቱ ወደ ላይ ከፍ ለማለት አዳማ ከተማ ደግሞ በሂደት ወደዚሁ አደጋ ዞን የቀረበበትን ሂደት ለመለወጥ ይገናኛሉ። በመጨረሻ አምስት ጨዋታዎቹ አንድ ጊዜ ብቻ ድል የቀናው አዲስ አበባ ከተማ በእንቅስቃሴ መጥፎ ሳይሆን ውጤት ሳይዝ የሚወጣበትን ጉዞውን ቀይሮ ነገ ድልን ካሳካ ቀጥሎ ጨዋታውን የሚያደርገው ድሬዳዋ ከተማን ቦታ ቀይሮ ከወራጅ ቀጠናው ቀና ማለት ይችላል። በመቀመጫ ከተማው የመጀመሪያ ድሉን ለማሳካት ነገም ሌላ ሙከራ የሚያደርገው አዳማ ከተማ ድል ካጣጣመ አምስት ጨዋታዎች ያሳለፈ ሲሆን ነገ የዚህን የቅርብ ጊዜ ታሪኩን ቀይሮ ድል ካደረገ ነጥቡን 27 አድርሶ ወደ ሰንጠረዡ አጋማሽ መጠጋት ይችላል።

የውድድር ዓመቱ በፈለጉበት መንገድ እየሄደላቸው ያልሆኑት ሁለቱ ቡድኖች የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር ድክመታቸውን ከጠንካራ ጎናቸው ጋር ማመጣጠን አለመቻላቸው ነው። በጨዋታው ከሚጠበቁ የሜዳ ላይ ፍልሚያዎች ይልቅም ይህንን ነጥብ በዝርዝር መመልከት የነገውን ተጋጣሚዎች ይበልጥ የሚያሳይ ይመስላል።

ግብ በማስቆጠር የማይታማው አዲስ አበባ ከተማ በሪችሞንድ ኦዶንጎ እና ፍፁን ጥላሁን በድምር 15 ጎሎች ያሉት ሲሆን እንደቡድን ያስቆጠራቸው አጠቃላይ ግቦች (22) በሊጉ በአራት ቡድኖች ብቻ የሚበለጥ ነው። ምንም እንኳን የሁለቱ አጥቂዎች አስተዋፅዖ ቢበዛበትም እና ከሌሎች ተሰላፊዎችም ተጨማሪ ግቦችን ማግኘት ቢኖርበትም እንኳን ቡድኑ በወራጅ ቀጠና ውስጥ እንዲገኝ ዋና ምክንያት የሆነው 24 ግቦችን ያስተናገደው የመከላከል መዋቅሩ እንደሆነ መናገር ይቻላል። አዲስ ፈራሚው አዩብ በቀታን ወደ አሰላለፍ በማምጣት ይህንን ድክመቱን ለመቅረፍ ቢሞከርም ጫና በማይፈጥሩ ቅፅበቶች በግለሰብ ስህተቶች ፣ ፈጣን ሽግግሮች ሲሰነዘሩ ደግሞ በተበታተነ መዋቅር አዲስ አበባ ከተማ አሁንም ግብ ማስተናገድ መቀጠሉ በመጨረሻው የፋሲል ከነማ ጨዋታ ላይም ታይቷል።

ወደ አዳማ ከተማ ስንመጣ ደግሞ በርካታ አቻ ውጤቶችን በማስመዝገብ የሚታማው ቡድን በመከላከል ቁጥሩ ግን አሁንም ከቅዱስ ጊዮርጊስ ቀጥሎ ጥቂት ጎል ያስተናገደ ቡድን እንደሆነ እንዲቀጥል አድርጓል። ነገር ግን በዋናነት ከዳዋ ሆቴሳ ፣ አሜ መሀመድ እና አብዲሳ ጀማል ጥምረት 11 ግቦችን ያስቆጠረው የፊት መስመሩ በበቂ ደረጃ አዳማ ጨዋታዎችን እያሸነፈ እንዲወጣ የሚያደርጉ ግቦችን ማምረት ሲሳነው ከሌሎች የቡድኑ ተሰላፊዎችም በግል ከአንድ በላይ ግብ የሚያስቆጥርለት ተጫዋች አላገኘም። ይህንን ለማስተካከል ቡድኑ ቅርፁን እየቀያየረ ወደ ሜዳ ቢገባም እንደ ሀዲያ ሆሳዕናው ጨዋታ አዳማን በማይገልፀው መልኩ የመከላከልም ክፍተት ሲታይበት እንጂ ከፊት መሻሻል ሲያመጣ አልታየም። ቡድኑ በሜዳውም ጨዋታዎችን እያሸነፈ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ አጥቂዎችም ሆኑ ሌሎች ተሰላፊዎች ሳጥን ውስጥ ተገኝተው በደካማ ውሳኔ አሰጣጥ የሚያመክኗቸው ዕድሎች ከሥነ ልቦና ጋር የተያያዙ መሆናቸው ቢታመንም በአምስት ጨዋታዎች ከሦስት በላይ ግቦች ላላገኘው ቡድን ግን እስካሁን መፍትሄ የተገኘ አይመስልም።

በመሆኑም ነገ በኦዶንጎ የሚመራው የአዲስ አበባ ከተማ የፊት መስመር ጠንካራውን የአዳማን መከላከል ሰብሮ ልዩነት ፈጣሪ ግቦችን ያስቆጥራል ወይስ በወጥነት ግቦችን ማምረት ያልሆነለት የአዳማ ከተማ የአጥቂ ክፍል በቀላሉ ግቦች የሚቆጠሩበት የአዲስ አበባ ከተማን የኋላ ክፍል ድክመት ይጠቀማል የሚለው ተጠባቂ ይሆናል። በጨዋታው በሁለቱም ቡድኖች በኩል የጉዳት እና የቅጣት ዜና ያልተሰማ ሲሆን ለአዳማ ከተማ ከላይ የተጠቀሰውን ድክመት ለማሻሻል በሚረዳ መልኩ አቡበከር ወንድሙን ከጉዳት መልስ የሚያገኝ መሆኑ መልካም ዜና ሆኖለታል።

ጨዋታውን ሄኖክ አክሊሉ በመሀል ዳኝነት ፣ ይበቃል ደሳለኝ እና እሱባለው መብራቴ በረዳትነት ኃይለየሱስ ባዘዘው ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ይመሩታል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ በድኖች እስካሁን ሦስት የሊግ ጨዋታዎች ያደረጉ ሲሆን በ2009 ጨዋታዎች አዳማ በ3-1 እና 2-1 ውጤቶች ሲያሸንፍ ዘንድሮ አዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ድሉን በ1-0 ውጤት ለማግኘት ቢቃረብም አዳማዎች በጭማሪ ደቂቃ አንድ ግብ አስቆጥረው የእርስ በእርስ ውጤቶች የበላይነታቸውን አስጠብቀዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል ተሾመ

አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ቴዎድሮስ ሀሙ – አዩብ በቀታ – ሮቤል ግርማ

ሙሉቀን አዲሱ – ቻርለስ ሩባኑ – ኤሊያስ አህመድ

እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን

አዳማ ከተማ (4-3-3)

ጀማል ጣሰው

ጀሚል ያዕቆብ – ቶማስ ስምረቱ – አዲስ ተስፋዬ – ሚሊዮን ሰለሞን

አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዮናስ ገረመው

አቡበከር ወንድሙ – ዳዋ ሆቴሳ – አሜ መሀመድ