ሪፖርት | የምሽቱ ጨዋታም በአቻ ውጤት ተጠናቋል

መከላከያ እና ባህር ዳር ከተማን ያገናኘው የዕለቱ ሁለተኛ ጨዋታ በ1-1 ውጤት ተቋጭቷል።

ጨዋታው በ1950’ዎቹ ለመቻል በመጫወት ያሳለፉት የጌታቸው ገላሼን ህልፈት በህሊና ፀሎት በማሰብ የተጀመረ ነበር።

መከላከያ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ነጥብ ከተጋራበት ጨዋታ ባደረገው ለውጥ አሚን ነስሩን በግሩም ሀጎስ ምትክ ተጠቅሟል። በባህር ዳር በኩል በአርባምንጩ ሽንፈት ተሰልፈው የነበሩት መናፍ ዐወል ፣ አህመድ ረሺድ እና አብዱልከሪም ኒኪማ በሳለአምላክ ተገኘ ፣ ሄኖክ ኢሳይያስ እና አለለኝ አዘነ ተተክተዋል።

ጨዋታው በጀመረባቸው ደቂቃዎች ፍፁም ዓለሙ ከግራ መስመር ባሻማው ኳስ እና በተከታታይ ከቆሙ ኳሶች ባህር ዳር ከተማዎች ዕድል በመፍጠር ከፍ ባለ ግለት ጀምረዋል። ሆኖም ቀስ በቀስ ይህንን ጫና ያበረዱት መከላከያዎች ነገሮችን በቁጥጥራቸው ስር በማድረግ በንፅፅር በተሻለ ሁኔታ በማጥቃት ግማሽ የሚባሉ ዕድሎችን ፈጥረዋል። ከእነዚህም ውስጥ በቀዳሚው የቡድኑ ጥረት 12ኛው ደቂቃ ላይ ቢኒያም በላይ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ የላከውን ኳስ ፋሲል ገብረሚካኤል ብዙም ሳይቸገር አድኖበታል።


በአመዛኙ ቢኒያም ከተሰለፈበት የግራ ወገን በሚነሱ ኳሶች ወደ ግብ ለመድረስ የሚጥሩት መከላከያዎች ቢኒያም ከዚሁ አቅጣጫ በቀጥታ በማሻገር በመቀጠል ደግሞ እየገፋ የባህር ዳር ተከላካዮችን አልፎ በመሰንጠቅ ባድራ ሲይላ አጋጣሚዎችን ቢፈጥርም አጥቂው በአግባቡ ሳይጠቀምባቸው ቅርቷል።
ባህር ዳር ከተማዎች እምብዛም ቦታውን ትቶ የማይወጣውን የጦሩን የኋላ ክፍል ማስለከፈት ከብዳቸው ሲታይ አልፎ አልፎ ወደ ሳጥኑ ቢቃረቡም ከጨዋታ ውጪ በሆነ አቋቋም ከሽፎባቸዋል። 

መከላከያዎችም የመጨረሻ የቅብብል ጥራታቸው መውረድ ይበልጥ ጫና ከመፍጠር ሲያግዳቸው የአጋማሹን የተሻለ ሙከራ ያደረጉት 29ኛው ደቂቃ ላይ ነበር። በዚህም ልደቱ ጌታቸው ከዳዊት ሞሞ ወደ ግራ ያደላ ቅጣት ምት ጥሩ ዕድል አግኝቶ ከቅርብ ርቀት ያደረገው ሙከራ ወደላይ ተነስቷል።
ከዕረፍት መልስ ገናናው ረጋሳ ባደረጋቸው ቀጥተኛ ሩጫዎች ከቀኝ መስመር ሁለት ጥሩ ኳሶችን ባደረሰባቸው ሂደቶች መከላከያ በጥሩ ንቃት ጀምሯል። ሆኖም ቢኒያም በላይ እና ተሾመ በላቸው አጋጣሚዎቹን ወደ ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች መቀየር ሳይችሉ ቀርተዋል። 

ባህር ዳሮች እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ ከጦሩ የተሻለ ጫና ቢደርስባቸውም 54ኛው ደቂቃ ላይ በፍፁም እና አለልኝ አዘነ ቅብብሎች ተሳክቶላቸው መግባት ችለው የፍፁም ሙከራ ወደ ውጪ የወጣ ነበር። ሆኖም ከአምስት ደቂቃዎች በኋላ አማካዩ ቡድኑ መከላከያን በቁጥር በልጦ ሳጥን ውስጥ በገባበት ቅፅበት በኢብራሂም ሁሴን ጥፋት ተሰርቶበት የፍፁም ቅጣት ምት ሲያገኝ ራሱ በመምታት ማስቆጠር ችሏል።

ጥረታቸውን የቀጠሉት መከላከያዎች ምላሽ ለመስጠት አስር ደቂቃ ብቻ አስፈልጓቸዋል። ቢኒያም በላይ ከግራ መስመር ያሻማውን የቅጣት ምት ኳስ ልደቱ ጌታቸው በግንባር ሲያመቻችለት ተቀይሮ ከገባ ሰከንዶች ያስቆጠሩት አዲሱ አቱላም በግንባሩ ጎል አድርጎታል። 

ጨዋታው በጥሩ ምልልስ የቀጠለ ሲሆን መከላከያዎች የተሻለ የማጥቃት የበላይነት ነበራቸው። በተለይም 77ኛው ደቂቃ ላይ ሌላው ተቀያሪ ግሩም ሀጎስ ከቀኝ ከኢማኑኤል ላሪያ የደረሰውን ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ መትቶ ፋሲል በአስገራሚ ቅልጥፍና ያቋረጠበት ለግብ የቀረበ ሙከራ ነበር።

ጨዋታው ወደ መጨረሻው ምዕራፍ ሲሸጋገር ከባህር ዳር የኳስ ቁጥጥር ይልቅ ጦሩ ኳስ አስጥሎ ወደ ፊት በፍጥነት ለመሄድ የሚሞክርበት ፍጥነት የተሻለ አስፈሪነት ነበረው። ከዚህም ውስጥ 85ኛው ደቂቃ ላይ በጥሩ መልሶ ማጥቃት ባህር ዳር ደጃፍ ደርሰው ተሾመ በላቸው ጥሩ ኳስ ቢያድረስም የአዲሱ የግንባር ኳስ ሙከራ ደካማ ሆኖ አልፏል። ቀሪው የጨዋታ ደቂቃዎችም በሁለቱም በኩል የሚደረጉ ጥረቶችን ከማሳየት በቀር ኢላማውን የጠበቀ ከባድ ሙከራ ሳይስተናገድበት በ1-1 ውጤት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ባህር ዳር በ 25 ነጥቦች አንድ ደረጃ አሻሽሎ 8ኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጥ መከላከያ በነበረበት 12ኛነት ላይ ለመርጋት ተገዷል።