የአሰልጣኞች አስተያየት | መከላከያ 1-1 ባህር ዳር ከተማ

የመከላከያና ባህር ዳር ከተማ ጨዋታ በአንድ አቻ ከተጠናቀቀ በኋላ አሰልጣኞቹ ተከታዩን አስተያየት ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ – መከላከያ

ከረጅም ደቂቃ በኋላ ጎል ስለማስቆጠራቸው

“ሦስት ነጥብ የሚያስገኝ ጎል ነው የምንፈልገው። ዛሬ በብዛት አጥቅተን እንጫወታለን ብለን ነበር ያሰብነው። ያው ሙከራዎችን ከሌላው ጊዜ በተሻሉ ማድረግ ችለናል። በተለይ ከዕረፍት በኋላ ግን መስጠት የማይገባንን ፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተን ዋጋ ከፍለናል። ከዚህ በተረፈ ግን ማጥቃት በፈለግነው መጠን ከሌሎቹ ጊዜ በተሻለ ዛሬ አጥቅተናል ፤ ብዙ ዕድሎች ፈጥረናል። ከዕረፍት በፊትም ዕድሎች አግኝተናል። አሁን ደግሞ መጨረስ የሚለው ላይ መሄድ አለብን።

አንዱ ጎሉ መልካም ነገር ይዞ ስለመምጣቱ

“አዎ አንደኛ ወደ ጎል መድረሱ ፣ ሁለተኛ ብዙ ዕድሎችን መፍጠሩ፣ ሦስተኛ ከማፈግፈግ ይልቅ በፍላጎት ወደ ፊት መሄዱ እነዚህ ሁሉ መልካሞች ናቸው። ፍፁም ቅጣት ምቱ ባይገባብን ሦስት ነጥብ ይዘን እንወጣ ነበር።

ስለተጫዋች ቅያሪ

“ነባር የሆኑ ሁለት ተጫዋቾችን ቀይረናል። በብዛት የምንጠቀመው አራት አምስት ልጆች በልዩ መለያ ካርድ በማስገባት ነው። ብሩክ ፣ ግሩም ፣ ተሾመም በልዩ ካርድ የሚጫወቱ ናቸው። ያለን ስኳድ ጠባብ በመሆኑ ከቦታ ቦታ ነው ልጆቹን እየቀያየርን የምናጫውተው። ወጣቶቹን የመያዝ ጥቅሙ የትም ቦታ የመጫወቱ ፍላጎት ስላላቸው ነው። በዚህ ላይ የሥራ ችግር የለባቸውም ወጣቶች ናቸው። በዚህ ምክንያት ቅያሪው ይህን ጥቅም ሰጥቶናል። ግሩም ፣ አዲስ በሙሉ አቅማቸው አይደሉም ጉዳት አለባቸው ግን እንደዛም ሆኖ ወጣቶቹ እንደዚህ ያለ ዕድል ስትሰጣቸው ከተጠቀሙበት ጥሩ ነው ብዬ አስባለው።”

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ

ሙሉ ነጥብ ሳላለማሳካታቸው

” በሙሉ ዘጠና ደቂቃ ውስጥ ሦስት ነጥብ ይዘን እንዳንወጣ የሆነበት ምክንያት ጎል ካስቆጠርን በኋላ ለማስጠበቅ ወደ ኋላ በማፍግፈጋችን ነው። ተጫዋቾቻችን ያገኘናትን ጎል አስጠብቆ ለመውጣት ከነበራቸው ፍላጎት ፣ ከጭንቀት ለመውጣት ስለፈለጉ ወደ ኋላ ማፈግፈጋቸው ስህተት ነው። ሁለተኛው እንደሌላው ጊዜ የቆሙ ኳሶች ላይ በሳጥን ውስጥ ያለን ሰው በሰው የመቆጣጠር ሥራ በአግባቡ ስላልተሰራ ከቆመ ኳስ ጎል ተቆጥሮብን ዛሬም ዋጋ አስከፍሎናል። በተረፈ ግን መሐል ላይ ያሉ ተጫዋቾችን ማብዛታችን ኳሱን ፣ ጨዋታውን እንድንቆጣጠር ዕረድቶናል።

የመጨረሻው ደቂቃ ላይ ቡድኑ ስለሚቸገርበት ምክንያት

“አንዳንድ ጊዜ የተጋጣሚ ቡድን የገባበትን ግብ ለማስጠበቅ ነቅለው በሚመጡበት ጊዜ የእነርሱን ክፍት ቦታ ለመጠቀም የምናደርገው ጥረት ትክክል አለመሆን ወይም ያደረግነው ጥረት አናሳ በመሆኑ ጎድቶናል። ሌላው እኛ ጋር ያለው ችግር የተጋጣሚ ቡድን በመስመር በሚመጣበት ጊዜ ከግራ ወደ ቀኝ ወይም ከቀኝ ወደ ግራ የሚለወጡ ኳሶችን ለመቆጣጠር የትኩረት ችግር እንዳለብን ተመልክቼያለሁ። ይሄንን በተቻለ መጠን በሚቀጥለው ጨዋታ ደግሞ እናስተካክላለን ብዬ ተስፋ አደርጋለው።”

ያጋሩ