ቅድመ ዳሰሳ | ወልቂጤ ከተማ ከ ድሬዳዋ ከተማ

ነገ አመሻሽ በሚደረገው ጨዋታ ዙሪያ ተከታዩ ዳሰሳ ተዘጋጅቷል።

የወቅቱ የሊጉ ዋንጫ ባለ ባለቤት ፋሲል ከነማን አሸንፎ በተከታታይ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ድል ማድረግ የተሳነው ወልቂጤ ከተማ ከድል ጋር ታርቆ ደረጃውን ለማሻሻል ወደ ሜዳ ይገባል። ድሬዳዋ ከተማ በበኩሉ ከስምንት ጨዋታዎች በኋላ ያገኘውን ሦስት ነጥብ ደግሞ ከአስጊው ቀጠና መላቀቅን በማሰብ ጨዋታውን ይቀርባል።

ባሳለፍነው ሳምንት በዋንጫ ፉክክር ውስጥ በሚገኘው ሀዋሳ ከተማ ሽንፈት ያስተናገደው ወልቂጤ ከተማ በጨዋታው ያሳየውን አንፃራዊ የእንቅስቃሴ ብልጫ ፍሬያማ ማድረግ ተስኖት ወጥቷል። በተለይ ቡድኑ በኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ የነበረ ቢሆንም ጨዋታውን በመቆጣጠር ግን ስል አልነበረም። የግብ ዕድሎችንም በመፍጠር ረገድ ተዳክሞ ነበር። ለዚህም ከዚህ ቀደም ጥሩ የነበረው የጌታነህ እና ጫላ ጥምረት ቀዝቀዝ ማለቱ ለሀዋሳ ተከላካዮች እምብዛም ፈተና አላበዛም ነበር። አሠልጣኙም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ እንዳሉት ጌታነህ በተጋጣሚ ተከላካዮች ትኩረት ሲደረግ ክፍተቶችን ሲጠቀም የነበረው ጫላ ከጤና ጋር ተያይዞ ብርቱ አለመሆኑ የፊት መስመሩን አዶልዱሞታል። በነገው ጨዋታ ግን ይህ የፊት መስመር በቀደመ ብቃቱ ላይ ከተገኘ ድሬዎች መቸገራቸው የማይቀር ነው።

የወልቂጤ ፍጥነት የተቀላቀለበት አጨዋወት በወጥነት አለመቀጠሉ ቡድኑ ላይ የሚነሳ ድክመት ነው። እርግጥ ከጨዋታ ጨዋታ ሙሉ 90 ደቂቃ ከኳስ ጋር እና ውጪ ፍጥነት የተቀላቀለበት አጨዋወት ማድረግ ከባድ ቢሆንም ብልጠት በተሞላበት የጊዜ እና የሁኔታ አጠባበቅ አጨዋወቱን ተግባራዊ ቢያደርግ ተጠቃሚ ሊሆን ይችል ነበር። ካለፉት 12 ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ መረቡን ያላስደፈረው ወልቂጤ የኋላ መስመሩን አደረጃጀት ማስተካከል ይገባዋል። በተለይ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ ትግል ላይ ያለው ድሬዳዋ ከተማ ድሎችን ለማግኘት አጥቅቶ መጫወቱ ስለማይቀር እንዳይቸገር ያሰጋል።

የናፈቀውን ድል ባሳለፍነው ሳምንት ጅማ አባ ጅፋር ላይ ያሳካው ድሬዳዋ ከተማ በአዲሱ አሠልጣኙ ስር መጠነኛ መሻሻል ቢያሳይም ካለበት አደገኛ ቀጠና አንፃር ከዚህ በላይ መሻሻል ይገባዋል። በጅማውም ጨዋታ በኳስ ቁጥጥር እና ግልፅ የግብ ማግባት ዕድሎችን በመፍጠር መጠነኛ ብልጫ ቢወሰድበትም በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች የነበረውን ክፍተት ለመድፈን የጣረበት መንገድ ዋጋ አስገኝቶታል። በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በ4-4-2 የተጫዋች አደራደር ቅርፅ ለመከላከል ቅድሚያ በመስጠት ግቡን መጠበቅ ላይ ተጠምዶ የነበረ ሲሆን በሁለተኛው አጋማሽ ደግሞ በ3-5-2 የተወሰደበትን የመሐል ሜዳ ብልጫ መልሶ ለማግኘት በመሞከር ሚዛናዊ ሆኖ ጨዋታውን ረቷል። የነገው ተጋጣሚው እንደ ጅማ ኳሱን ለመያዝ የሚሻ ስለሆነም መሐል ሜዳ ላይ የቁጥር ብልጫ በመውሰድ የሀይል ሚዛኑን ለማመጣጠን እንደሚውተረተር ይገመታል።

ከ429 ደቂቃዎች በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት ኳስ እና መረብን ያገናኘው ድሬዳዋ ከተማ ከወገብ በላይ የነበረውን እጅግ የከፋ የሚመስል ቁስል ሙሉ ለሙሉ መዳኛ መድሃኒት ባያገኝም በጅማው ጨዋታ በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ አሻሽሽሎ ታይቷል። ከስድስት ጨዋታዎች በኋላም ከፍተኛ ሙከራዎችን (17) ያደረገበት የጨዋታ ቀን አሳልፎ የግቡን መረብ ሁለት ጊዜ አግኝቷል። በተቃራኒው የሊጉ ሦስተኛው ብዙ ግብ ያስተናገደ የኋላ መስመር የሆነው ቡድኑም የተከላካዮቹን መዋቅራዊ ስህተቶች መቅረፍ ካልቻለ እንደ ቅፅል ስማቸው ሰራተኛ በሆኑት ወልቂጤዎች ሊቸገር ይችላል።

ወልቂጤ ከተማ ሀብታሙ ሸዋለምን በጉዳት ምክንያት የሚያጣ ሲሆን የአጥቂው ጫላ መጠነኛ ጉዳትም የተጫዋቹን የመሰለፍ ጉዳይ አጠራጣሪ አድርጎታል። ድሬዳዋ ከተማ ግን በጉዳትም ሆነ በቅጣት ምክንያት የሚያጣው ተጫዋች የለም።

ዳንኤል ግርማይ የጨዋታው ዋና አልቢትር ሲሆኑ ክንፈ ይልማ እና ፋንታሁን አድማሱ ረዳት ሀብታሙ መንግስቴ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው በጨዋታው መመደባቸውን አውቀናል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– በሦስት ጊዜ የቡድኖቹ የቀደመ ግንኙነት ወልቂጤ ከተማ ሁለት ጊዜ ሲረታ አንዷን ደግሞ ድሬዳዋ አሸንፏል። በሦስቱ ጨዋታዎች ከተቆጠሩት ስምንት ጎሎችም ወልቂጤ አምስት ድሬ ሦስት ግብ በስማቸው አግኝተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ


ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ሮበርት ኦዶንካራ

ተስፋዬ ነጋሽ – ዳግም ንጉሴ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ

በኃይሉ ተሻገር – አክሊሉ ዋለልኝ – አብዱልከሪም ወርቁ

ያሬድ ታደሠ – ጌታነህ ከበደ – ጫላ ተሺታ

ድሬዳዋ ከተማ (4-2-3-1)

ፍሬው ጌታሁን

እንየው ካሳሁን – መሳይ ጳውሎስ – አውዱ ናፊዩ – አማረ በቀለ

ዳንኤል ኃይሉ – ዳንኤል ደምሴ

ጋዲሳ መብራቴ – ሙኸዲን ሙሳ – አብዱርሀማን ሙባረክ

ማማዱ ሲዲቤ