ሪፖርት | አዲስ አበባ እና አዳማ ነጥብ ተጋርተዋል

በዝናባማ የአየር ሁኔታ ውስጥ በተደረገው የዕለቱ የመጀመሪያ ጨዋታ አዳማ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ያለግብ ተለያይተዋል።

አዲስ አበባ ከተማዎች ከፋሲል ከነማ ጋር ሁለት አቻ ከተለያዩበት ጨዋታ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ፍፁም ጥላሁንን በመሀመድ አበራ ብቻ ሲለውጡ በአንፃሩ አዳማ ከተማዎች በኩል ደግሞ በሀዲያ ሆሳዕና ከተረታው ስብስብ ሦስት ለውጦች ተደርገው አሜ መሀመድ ፣ ዮሴፍ ዮሀንስ እና ዮናስ ገረመው በጀሚል ያዕቆብ ፣ ፀጋአብ ዮሴፍ እና ዘካርያስ ከበደ ምትክ በዛሬው ጨዋታ በመጀመሪያ ተሰላፊነት ተካተዋል።

ገና ከጅምሩ ጨዋታውን ለማሸነፍ ከፍ ባለ ፍላጎት ጫና ፈጥረው መጫወት የጀመሩት አዳማዎች በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች በከፍተኛ የማጥቃት ማዕበል አዲስ አበባ ከተማን ሲፈትኑ አስተውለናል። በተለይ ደግሞ በ3ኛው ደቂቃ ዳዋ ሆቴሳ ከአዲስ አበባ ሳጥን ትይዩ ያገኘውን የቅጣት ምት ኳስ በቀጥታ ወደ ግብ የላካት እና ዳንኤል ተሾመ በግሩም ቅልጥፍና ያዳነበት አዳማዎችን ገና በማለዳው ቀዳሚ ለማድረግ የቀረበች አጋጣሚ ነበረች።

በጨዋታው ቀስ በቀስ የአዳማ ተጫዋቾች መሀል ሜዳ ላይ ጫና ውስጥ በመክተት በሚነጠቁ ኳሶች የመልሶ ማጥቃት የመሰንዘር ፍላጎት የነበራቸው አዲስ አበባዎች በ8ኛው ደቂቃ ዮሴፍ ዮሐንስ የተሳሳተውን የኳስ ማቀበል ሂደት ተጠቅሞ ሪችሞንድ አዶንጎ ግሩም የማግባት አጋጣሚ ቢያገኝም ኳሷን ከግቡ አናት በላይ ለቋታል። አዳማ ከተማዎች እንደነበራቸው አጀማመር ተደጋጋሚ የጠሩ ዕድሎችን መፍጠር ሳይችሉ የቀሩ ሲሆን ይህም ቀስ በቀስ አዲስ አበባዎች ወደ ጨዋታው እንዲገቡ ፈቅደውላቸዋል።

አዳማ ከተማዎች በአጋማሹ በተለይ ከማዕዘን ምቶች መነሻነት ተደጋጋሚ ዕድሎችን ለመፍጠር ጥረት ያደረጉ ሲሆን በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማዎች በአጋማሹ የመጨረሻ 20 ደቂቃዎች ይበልጥ በጨዋታው የተሻለ ቁጥጥር ነበራቸው በዚህም በ36ኛው ደቂቃ በቀጥተኛ አጨዋወት ያገኘውን ኳስ እንዳለ ከበደ ከቀኝ መስመር ሲያሻማ ሪችምንድ አዶንጎ ተቆጣጥሮ ከሳጥን ጠርዝ ወደ ግብ ልኮት ጀማል ጣሰው አድኖበታል።

ተለዋዋጭ መልክ በነበረው በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ መሐመድ አበራን አስወጥተው በምትኩ ፍፁም ጥላሁንን ቀይረው ያስገቡት አዲስ አበባ ከተማዎች አሰጋኸኝ ጴጥሮስ ከቆመ ኳስ በቀጥታ ባደረጋት ሙከራ የጀመሩ ሲሆን ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያ በተሻለ ነቃ ያለ አጀማመር ማድረግ ችለው ነበር።

ነገር ግን አዳማ ከተማዎች በተለይ ከአዲስ አበባ ተከላካዮች ጀርባ የሚኖረውን ክፍተት ለመጠቀም ተደጋጋሚ ጥረት ማድረግ የጀመሩ ሲሆን በዚህም በሁለት አጋጣሚዎች ግብ ማስቆጠር ቢችሉም ኳሶቹ ከጨዋታ ውጪ በሚል ሳይፀድቁ ቀርተዋል።

በጨዋታው ምንም እንኳን የጠሩ ዕድሎችን መፍጠር ያልቻሉት አዳማ ከተማዎች አንፃራዊ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ወስደው ግቦችን ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። በ63ኛው ደቂቃ ደስታ ዮሐንስ በቀጥታ ከቆመ ኳስ ወደ ግብ ልኳት ዳንኤል ካዳነበት ኳስ ውጪ ይባስ ብሎ ደቂቃዎች እየገፉ መሄዳቸውን ተከትሎ በጥድፊያ ለማጥቃት ያደረጉት ጥረት ፍሬያማ አልነበረም። በአንፃሩ ፍፁም ጥላሁን በተሰለፈበት የግራ መስመር በኩል የተሻለ የመልሶ ማጥቃቶችን ለመሰንዘር ጥረት ያደረጉት አዲስ አበባዎች በውሳኔዎች መዘግየት ያሰቡትን ማሳካት ሳይችሉ ቀርተዋል።

ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቁን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማዎች በ20 ነጥብ ለጊዜውም ቢሆን ወደ 13ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ በተመሳሳይ አዳማ ከተማም እንዲሁ በ25 ነጥብ ወደ 9ኛ ከፍ ብለዋል።

ያጋሩ