የአሰልጣኞች አስተያየት | አዲስ አበባ ከተማ 0-0 አዳማ ከተማ

የአዲስ አበባ እና አዳማ ጨዋታ ያለ ግብ መጠናቀቁን ተከትሎ አሰልጣኞች ተከታዩን ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡

አሰልጣኝ ደምሰው በፍቃዱ – አዲስ አበባ ከተማ

ስለጨዋታው

“ጨወታው ትንሽ ጠንካራ ነበር፡ ፤ ፈታኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም አዳማም ተጭኖ ነው የተጫወቱት እኛ ደግሞ ወደ ኋላ የማፈግፈግ ነገር ስለነበር ትንሽ አስቸጋሪ ነበር፡፡

ስለጨዋታ ዕቅዳቸው

“እኛም መጀመሪያም እንደገለፅኩት ማሸነፍ የግድ ያስፈልገናል፡፡ ልክ አዳማ እንደሚፈልገው ሁሉ እኛም ማሸነፍ እንፈልጋለን እንጂ አቻነቱን አንፈልገውም ፤ ግን ደግሞ ከመጣ ትቀበላለህ፡፡

ስለአጨራረስ ችግር

“ምክንያቱን እንግዲህ ቀስ እያልን እናየዋለን፡፡በእርግጥ እኛም ያወቅነው ነገር አለ። በኦዶንጎ አካባቢ በእርግጥ ላይሳካ ይችላል አንዳንድ ጊዜ። እሱ ጎበዝ ጎል አስቆጣሪያችን ነው አንዳንድ ቀን ደግሞ ያው በእግር ኳስ ይከሰታል፡፡ ሌሎች አካባቢ ያሉ ክፍተቶችን ግን እናስተካክላለን፡፡

የኤልያስ ማሞ ወደ ቡድኑ መምጣት ስለሚሰጠው ጥቅም

“ኤልያስ ማሞ ትልቅ ልምድ ያለው ተጫዋች ነው፡፡ በጊዜ ሂደት ደግሞ እየተስተካከለ እየተስተካከለ ሲመጣ ለቡድናችን ትልቅ ይጠቅማል ለልጆቹም ትልቅ መነሳሳትን ይፈጥርልናል፡፡

ስለውጤቱ

“ይሄ የተሸናፊ መንፈስ የሚለውን ነገር አንደኛ ያስቀርልናል፡፡ እስከ አሁን ድረስ የመጣንበት ጥሩ ነው፡፡ የማሸነፍን መንፈስን ደግሞ ከፍ እያደረገልን ስለሚሄድ ለሚቀጥሉት ጨዋታዎች ስንቅ ይሆንልናል፡፡”

አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ – አዳማ ከተማ

ስለሁለተኛው አጋማሽ

“የሁለተኛው አርባ አምስት ብዙ ችኮላ የበዛበት እና ጥድፊያ የበዛበት ነበር፡፡ በምናስበው መልኩ ተጫውተናል ብዬ አላስብም፡፡በመጀመሪያው አርባ አምስት አጀማመር ሁሉ ነገር ጥሩ ነበር፡፡ ግን ያው መጨረሻ የሜዳ ክፍል ላይ ጨዋታውን ለማሸነፍ ስለምንፈልግ ብዙ ችኮላዎች ይታዩ ነበር፡፡ ጨዋታዎችን ማሸነፍ ፈልገን ነበር፡፡ ልጆቻችን በጫና ውስጥ እንደሆኑ ይሰማኛል አልተሳካልኝም፡፡

ጎል ስልማስቆጠር እክል

“በእርግጥ በጣም ከኋላ አራት የማይሄዱ ልጆች ከአንድ የተከላካይ አማካይ ጋር አምስት ሆነው በጣም ጎላቸውን በጥንቃቄ እየጠበቁ እንደነበር ሜዳ ላይ አይቻለሁ፡፡ ያንን ነው መስበር ያልቻልነው አንዳንድ ኳሶች ትክክል አይደሉም። ከችኮላ ጋር ተያይዞ የምናጠቃበት መንገድ ስህተት ነው፡፡ ወደ በኋላ ደግሞ ሰዓቱ እያለቀ ሲሄድ የበለጠ ችኮላ ውስጥ ገባን የምንፈልገውን ነገር ማግኘት አልቻልንም፡፡

ተከያያይ ነጥብ መጣላቸው

“ምንም ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር የለም፡፡ እግር ኳስ ነው ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ናቸው እኔ በምፈልገው መንገድ ቡድኑ ያልተጫወተው ተስፋ የሚያስቆጥር ነገር የለውም፡፡ የሚሻሻል እና የመጀመሪያውን ጨዋታ ማሸነፍ ከቻልን ጎሎችን ማግኘት ከቻልን ልጆቻችን ወደ ሚፈለገው ሥነ ልቦና ይመለሳሉ ብለን እናስባለን፡፡”