ቅድመ ዳሰሳ | አርባምንጭ ከተማ ከ ፋሲል ከነማ

የ20ኛው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ቀዳሚ ፍልሚያ ዙሪያ እነዚህን ነጥቦች አንስተናል።

አምስተኛ እና ሰባተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙት ፋሲል እና አርባምንጭ የደረጃ መሻሻል የሚያስገኝላቸውን ጨዋታ ያደርጋሉ። ባለፉት ዘጠኝ ጨዋታዎች ሽንፈትን ያስወገዱት አርባምንጮች ተከታታይ የሚሆንላቸውን ድል ማሳካት ከቻሉ ነጥባቸውን 29 በማድረስ ወደ ስድስት ከፍ ማለት ይችላሉ። ፋሲል ከነማዎች በበኩላቸው ከአቻ ውጤት መልስ ድል ካደረጉ በ 34 ነጥቦች ሦስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጥ የሚችሉበት ዕድል አለ።

ለአርባምንጭ ከተማ ብቻ ሳይሆን ለሊጉም የማይረሳ ከነበረው ከሀዲያ ሆሳዕናው የ4-4 ውጤት በኋላ አዞዎቹ ሁለተኛ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ። በእርግጥም በአንድ ጨዋታ ከአንድ ጊዜ በላይ መረቡ ተደፍሮ የማያውቀው እና እሱም በተጋጣሚው ላይ ከሁለት በላይ ግብ አስቆጥሮ ለማያውቀው ቡድን ያ አጋጣሚ ህልም ነበር ማለት ይቻላል። በ19ኛው ሳምንት የባህር ዳሩ ጨዋታ ግን አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ የ4-4ቱን ጨዋታ ‘ትምህርት ወስደንበታል’ እንዳሉትም ቡድናቸውን ወደነበረ ገፅታው መልሰው በጠንካራ መከላከል ታጅበው ባህር ዳርን 1-0 በመርታት ሦስት ነጥብ ማሳካት ችለዋል።

ቡድኑ የተለዋዋጭነት መርህ ቢኖረውም ከአቀራረብ አንፃር ግን ነገም ተመሳሳይ አርባምንጭ እንደምናይ ይጠበቃል። ግብ እስኪያገኝ ፋሲል ከነማ ከሜዳው እንደማይወጣ በማፈን የቡድኑ ድከማ ጎን የሆነውን የኋላ መስመር ጥቅም ላይ ማዋል ፤ ግብ ካስቆጠረ ደግሞ በተካነበት ጥልቅ መከላከል የቅብብልም ሆነ የተሻጋሪ ኳሶች ክፍተትን መዝጋት የአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ዋና ዕቅድ የሚሆን ይመስላል።

ከጅማ አባ ጅፋሩ ድል መልስ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋራው ፋሲል ከነማ የአሰልጣኝ ቅያሪ ሰሞን ቡድኖች ላይ የሚታየው ከፍ ያለ ተነሳሽነት ጎልቶ ታይቶበታል ማለት ይከብዳል። በእርግጥ አሰልጣኝ ኃይሉ ነጋሽ ከአዲስ አበባው ጨዋታ በኋላ ቡድኑ ውስጥ ሕብረት እንዳለ ጠቁመው በሥነልቦናው ረገድ ግን ድክመቶች እንዳሉ የጠቆሙበት አስተያየት ሚዛን ይደፋል። ለኳስ ቁጥጥር ቅድሚያ የሚሰጠው ቡድኑ ለረጅም ደቂቃዎች በትዕግስት በቅብብሎች ላይ ዕምነቱን ከማሳደር ይልቅ ችኮላ የሚንፀባረቅባቸው ረጃጅም ኳሶችን ወደ ግብ ሲልክ የሚታይባቸው አጋጣሚዎች ከሁለተኛ ዕቅድነት ይልቅ ግብ ከማስቆጠር ከፍ ያለ ፍላጎት ከሚመነጭ ጥድፊያ ምክንያት የሚታዩ ይመስላሉ።

ከዚህ አንፃር ስንመለከተው የነገው ጨዋታ ለፋሲል ቀላል ይሆናል ብሎ ማሰብ ከባድ ነው። በቀላሉ ክፍተት የማይሰጠውን የአርባምንጭን የኳስ ውጪ አደረጃጀት ፋሲሎች ጥራታቸውን በጠበቁ እና ትዕግስትን በተላበሱ ቅብብሎች አልፈው የግብ ዕድሎችን የመፍጠር ወቅታዊ ብቃታቸው እስከምን ነው የሚለው አጠያያቂ ነው። ረዣዥም ኳሶችንም መጠቀም ለአዞዎቹ ይበልጥ ምቹ ከመሆኑ አንፃርም በዋነኝነት ከሱራፌል ዳኛቸው የሚላኩት መሰል ኳሶች ስኬት አጠራጣሪ የሚባል ነው።

የተጋጣሚዎቹ ያለፉ ጨዋታዎች በዚህ ጨዋታ ዳሰሳችን ውስጥ ግለሰባዊ አበርክቶዎችን እንድናነሳ ያደርገናል። በአርባምንጭ በኩል ከፊት አህመድ ሁሴን እና ኤሪክ ካፓይቶን ማጣቱን ባለፈው ጨዋታ የሸፈነበት መንገድ ትኩረት ሳቢ ነበር። ለዚህም የፍቃዱ መኮንን ረጅም ቅብብሎችን ለሁለተኛ ኳስ በማመቻቸት እንዲሁም ከኳስ ውጪ የተጋጣሚን የቅብብል መስመሮች በማፈን የነበረው ድርሻ ለነገው ጨዋታም ለቡድኑ ስንቅ የሚሆን ነው። የተጨዋቹ እንቅስቃሴ ሳምንት ግብ ላስቆጠረው ሀቢብ ከማል እና ለሌሎቹም ተሰላፊዎች የሚሰጠው ክፍተትም መረሳት አይኖርበትም።

በተመሳሳይ በፋሲል ከነማ በኩል ዘግይተው ሳጥን ውስጥ ለሚደርሱ አማካዮች በጥሩ ጊዜ እና ቦታ ከኳስ ጋር እንዲገናኙ የሚያደርገው የኦኪኪ አፎላቢ እንቅስቃሴ ብዙ ክፍተት በማይገኝበት በነገው ጨዋታ ለፋሲል ወሳኝ ነው። በሁለት ጨዋታዎች ሦስት ግቦች አስቆጥሮ አጠቃላይ የግብ ድምሩን ስድስት ያደረሰው ኦኪኪ በአዲሱ መለያው ያለው ተፅዕኖ መጨመር ለቡድኑ የነገ ግጥምያ ትልቅ ተስፋ የሚሰጥ ነው።

አርባምንጭ ከተማዎች ከአህመድ ሁሴን እና ኤሪክ ካፓይቶ በተጨማሪ ማርቲን ኦኮሮን በጉዳት ሲያጡ በፋሲል በኩል ጉዳት ላይ የሚገኘው ሙጂብ ቃሲም ብቻ ጨዋታው ያልፈዋል።

ጨዋታው በተካልኝ ለማ የመሀል ዳኝነት ሲደረግ አስቻለው ወርቁ እና ተስፋዬ ንጉስ ረዳቶች ተፈሪ አለባቸው ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

የእርስ በእርስ ግንኙነት

– ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በሊጉ በአምስት ጨዋታዎች የመገናኛት ታሪክ ሲኖራቸው ፋሲል ከነማ ሁለቴ ፣ አርባምንጭ ከተማ ደግሞ አንድ ጊዜ አሸንፈው የዘንድሮውን ጨምሮ ሁለት ጊዜ ነጥብ ተጋርተዋል። በጨዋታዎቹ ፋሲል አራት አርባምንጭ ሁለት ጎሎችን አስመዝግበዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ወርቅይታደስ አበበ – አሸናፊ ፊዳ – ፀጋዬ አበራ – ተካልኝ ደጀኔ

ሙና በቀለ – አቡበከር ሸሚል – እንዳልካቸው መስፍን – ሀቢብ ከማል

ፍቃዱ መኮንን – በላይ ገዛኸኝ

ፋሲል ከነማ (4-1-4-1)

ሚኬል ሳማኬ

ዓለምብርሃን ይግዛው – ከድር ኩሊባሊ – ያሬድ ባየህ – አምሳሉ ጥላሁን

ይሁን እንዳሻው

ሽመክት ጉግሳ – በዛብህ መለዮ – ሱራፌል ዳኛቸው – በረከት ደስታ

ኦኪኪ አፎላቢ