የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት የዛሬ ጨዋታዎች ውሎ

ዛሬ ሦስት ጨዋታዎች ባስተናገደው የሴቶች ፕሪምየር ሊግ ሦስቱ መሪ ቡድኖች ማሸነፍ ችለዋል።

በቶማስ ቦጋለ

አርባምንጭ ከተማ 0-1 ሀዋሳ ከተማ

ረፋድ 03፡00 ላይ አርባምንጭ ከሐዋሳ ሲገናኙ አዞዎቹ በአሥረኛ ሣምንት አዳማ ከተማን 3-0 ከረቱበት አሰላለፍ የአንድ ተጫዋች ቅያሪ ሲያደርጉ ርብቃ ጣሰው በመሠረት ወርቅነህ ተተክታ ገብታለች። ሐዋሳዎችም በበኩላቸው በአሥረኛ ሣምንት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በሰፊ የግብ ልዩነት ከተረቱበት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ፀሐይነሽ ጅላ እና ዙፋን ደፈርሻ በማሕደር ባየ እና እታለም አግኑ ተተክተው ጀምረዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ የተቆራረጡ ኳሶች የበዙበት ፣ ቀዝቀዝ ያለ ፉክክር የታየበት ግን በሁለቱም በኩል ቶሎ ቶሎ ወደግብ የመድረስ ፍላጎት የታየበት አጋማሽ ነበር።

በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ የተሻሉ የነበሩ እና ይበልጥ በተጋጣሚ ክልል በዛ ብለው የተጫወቱት እና የተሻለ የግብ ዕድል የፈጠሩት ሐዋሳዎች ሲሆኑ የመጀመሪያ ሙከራቸውን 4ኛው ደቂቃ ላይ ረድኤት አስረሳኸኝ ከቀኝ መስመር ወደ መሀል ይዛው ገብታ ወደግብ በሞከረችው ኢላማውን ያልጠበቀ ሙከራ አድርገዋል። 8ኛው ደቂቃ ሐዋሳዎች መሪ ያደረጋቸውን ግብ ሲያስቆጥሩ ምሕረት መለሰ ለቱሪስት ለማ ለማቀበል ከረጅም ርቀት ያሻማችውን ኳስ የአርባምንጯ ግብ ጠባቂ ኳሱን ለመያዝ ስትወጣ የጊዜ አጠባበቅ ስህተት በመሥራቷ ኳሱ ነጥሮ መረቡ ላይ አርፏል።

በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት የአርባምንጭ ተከላካዮች በሰሩት ስህተት የግብ ማግባት አጋጣሚ ያገኘችው ቱሪስት ለማ ኃይል ባልነበረው ኳስ ዕድሏን አባክናለች። በተጨማሪም በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት በግራ መስመር ከምሕረት መለሰ የተቀበለችውን ኳስ በቀኝ መስመር የነበረችው ረድኤት አስረሳኸኝ ለማስቆጠር ምቹ ሁኔታ ብታገኝም ሳትጠቀምበት ቀርታ የቡድኗን መሪነት ሊያጠናክር የሚችል ዕድል አባክናለች።

አዞዎቹ የመጀመሪያ ሙከራቸውን ያደረጉት 18ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ወርቅነሽ ሚልሜላ ከረጅም ርቀት በመታችውና ግብ ጠባቂዋ በያዘችው ኳስ ነበር። ከውኃ ዕረፍት መልስ አዞዎቹ በኳስ ቁጥጥሩ ይበልጥ ተሻሽለው ሲቀርቡ 30ኛው ደቂቃ ላይ ትዝታ ኃይለማርያም በጥሩ ሁኔታ አመቻችታ ያቀበለቻትን ኳስ ነፃ ሆና ግብ ለማስቆጠር ምቹ አጋጣሚ ያገኘቸው ሠርክአዲስ ካሣየ ቡድኗን አቻ ሊያደርግ የሚችል ወርቃማ ዕድል አባክናለች። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት አዞዎቹ በወርቅነሽ ሜልሜላ እና በትዝታ ኃይለማርያም የግብ ዕድል ለመፍጠር ቢችሉም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

ሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ ጨዋታ እና የተመጣጠነ ፉክክር የታየበት ሲሆን ጨዋታው በጀመረ በአንድ ደቂቃ ውስጥ መንደሪን ክንድሁን ወደ ግብ በጥሩ ሁኔታ የሞከረችውን የቅጣት ምት ግብ ጠባቂዋ ለመያዝ ብትሞክርም ኃይል ስለነበረው ከሷ አልፎ የላይኛው አግዳሚ መልሶታል። ኳሱ ሲመለስ ነጻ ሆና ያገኘቸው ቅድስት ቴቃ በቀላሉ ግብ ማስቆጠር የምትችልበትን አጋጣሚ ሳትጠቀምበት ቀርታለች። ቀስ በቀስ ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሞከሩት አዞዎቹ የተሻለ ወደተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ ችለዋል። 51ኛው ደቂቃ ላይ ድንቅነሽ በቀለ የሐዋሳ ተከላካዮች ባለመረጋጋት በሰሩት ስህተት ነጻ ሆና ያገኘችውን ኳስ ሳትጠቀምበት ቀርታለች።

70ኛው ደቂቃ ላይ በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው ቱሪስት ለማ በቀኝ መስመር ገፍታ ወደ ግብ የሞከረችውና ግብጠባቂዋ ያዳነችው ኳስ በሐዋሳዎች በኩል የሚያስቆጭ ነበር። ከውኃ ዕረፍት መልስ 72ኛው ደቂቃ ላይ የሐዋሳ ተጫዋቾች ወደቦታቸው ሳይመለሱ ከእጅ ውርወራ ኳሱን በፍጥነት የጀመሩት አዞዎቹ በቁጥር በዛ ብለው ብቻቸውን ከግብ ጠባቂ ጋ ቢገናኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል። ይሄም አዞዎቹን በከፍተኛ ሁኔታ ያስቆጨ አጋጣሚ ነበር። በተደጋጋሚ የማጥቃት አማራጫቸውን የተጠቀሙት አዞዎቹ በጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ሠርክአዲስ ካሣየ አመቻችታ ያቀበለቻትን ኳስ የተከላካዮቹ ስህተት ተጨምሮበት ያገኘችው ድንቅነሽ በቀለ ዘግይታ ኳሱን ለማስቆጠር ብትሞክርም ግብ ጠባቂዋ ይዛዋለች ይሄም ለአርባምንጭ ሌላኛው አስቆጪ አጋጣሚ ነበር። ሐዋሳዎችም ተጨማሪ ግብ ለማስቆጠር በቱሪስት ለማ እና በሲሣይ ገ/ዋህድ የግብ ዕድል መፍጠር ቢችሉም ውጤታማ አልነበሩም። ጨዋታውም በሀዋሳ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-0 አዲስ አበባ ከተማ

08፡00 ላይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እና የአዲስ አበባ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ ንግድ ባንኮች በአሥረኛ ሣምንት ሐዋሳ ከተማን በሰፊ የግብ ልዩነት ካሸነፉበት አሰላለፍ የአራት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ጥሩአንቺ መንገሻ ፣ ብዙዓየሁ ታደሠ ፣ ብርቱካን ገብረክርስቶስ እና ፀጋነሽ ወራና በሎዛ አበራ ፣ ትዝታ ኃይለሚካኤል ፣ አለምነሽ ገረመው እና ትዕግሥት ያደታ ተተክተው ገብተዋል። በአዲስአበባ ከተማዎች በኩል በአሥረኛ ሣምንት በቅዱስ ጊዮርጊስ በቤተልሔም መንተሎ ብቸኛ ግብ ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ቤተልሔም ዮሐንስ ፣ አርያት ኦዶንግ እና ፍቅርተ አስማማው በስርጉት ተስፋዬ ፣ ቤተልሔም ከፍያለው እና ቤተልሔም ሰማኸኝ ተተክተው ገብተዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ የተሻለ ፉክክር የታየበት አጋማሽ ሲሆን ንግድ ባንኮች ከግራ መስመር ከአረጋሽ ካልሳ በሚነሱ ኮሷች የተሻለ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ አዲስ አበባዎች በበኩላቸው ወደ ኋላ ጥቅጥቅ ብለው የሚያገኙትን ኳስ በአርያት ኦዶንግ ላይ በማድረግ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሞክረዋል። 11ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ በጥሩ ሁኔታ ገፍታ ያሻማችውን ኳስ ዝግጁ ያልነበረችው መዲና ዐወል በትክክል ኳሱን ባለማግኘቷ የሞከረችውን ኳስ የግራውን ቋሚ ገጭቶ ወጥቶባታል። አዲስአበባ ከተማዎች የመጀመሪያ ሙከራቸውን ያደረጉት 15ኛው ደቂቃ ላይ አርያት ኦዶንግ በሞከረችውና በንግድ ባንክ ተጫዋቾች ተጨርፎ በወጣው የቅጣት ምት ኳስ ነው። 18ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ ከሰናይት ቦጋለ የተቀበለችውን ኳስ በጥሩ ሁኔታ ብትሞክርም ግብ ጠባቂዋ በጥሩ ብቃት ይዛዋለች። 25ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ ፣ ሰናይት ቦጋለ እና መዲና ዐወል በጥሩ ቅብብል የወሰዱትና ሰናይት ቦጋለ ወደ ግብ የሞከረችው ኳስ የላይኛውን ቋሚ ታክኮ ወጥቶባታል።

28ኛው ደቂቃ ላይ አረጋሽ ካልሳ በጥሩ ሁኔታ ገፍታ ከግራ መስመር ያሻማችውን ኳስ ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረችው ፀጋነሽ ወራና በአግባቡ በመጠቀም ቡድኗን መሪ አድርጋለች። በአራት ደቂቃዎች ልዩነት አረጋሽ ካልሳ በተመሳሳይ ሁኔታ ከግራ መስመር ያሻማችውን ኳስ መዲና ዐወል በጥሩ ሁኔታ ብትሞክርም ግብ ጠባቂዋ በጥሩ ብቃት ይዛዋለች። አዲስአበባ ከተማዎች በጨዋታው ሁለተኛ ሙከራቸውን ያደረጉት አርያት ኦዶንግ ከዘይነባ ሰይድ የተቀበለችውና ገፍታ ወስዳ ባደረገችው ኢላማውን ባልጠበቀ ሙከራ ነበር። በጨዋታው ጥሩ ስትንቀሳቀስ የነበረችው መዲና ዐወል በቀኝ መስመር ከዕፀገነት ብዙነህ የተቀበችውን ኳስ ወደግብ ብትሞክርም ግብ ጠባቂዋ ይዛዋለች።

ከዕረፍት መልስ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፍጹም የበላይነት የታየ ሲሆን የመጀመሪያው የግብ ሙከራ የታየውም 55ኛው ደቂቃ ላይ ተቀይራ የገባቸው ሎዛ አበራ ከሳጥን ውጪ ወደ ግብ በሞከረችው እና ግብ ጠባቂዋ በቀላሉ በያዘችው ኳስ ነበር። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ሎዛ አበራ ለመዲና ዐወል የሰጠቻትና መዲናም በግሩም ሁኔታ ሞክራው ግብ ጠባቂዋ በአስደናቂ ብቃት በላይኛው አግዳሚ ያወጣችው ኳስ ንግድ ባንኮችን ያስቆጨ አጋጣሚ ነበር። 65ኛው ደቂቃ ላይ መዲና ዐወል ወደግብ ሞክራው ከግብ ጠባቂዋ ቢያልፍም ትክክለኛ ቦታ ላይ የነበረችው ዮርዳኖስ ፍስሃ በፍጥነት አጽድታዋለች።

በሁለት ደቂቃ ልዩነት እፀገነት ብዙነህ ከቀኝ መስመር ያሻማችውን ኳስ መዲና ዐወል በግሩም ሁኔታ በግንባሯ ገጭታ ብትሞክርም በጨዋታው አስደናቂ ብቃት ያሳየችው ግብ ጠባቂዋ ቤተልሔም ዮሐንስ በድንቅ ብቃት አድናዋለች። የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃዎች ላይ ሎዛ አበራ ለአረጋሽ አመቻችታ ያቀበለቻትን ኳስ አረጋሽም ወደኋላ መልሳ ለሰናይት ቦጋለ አመቻችታ ስታቀብል ሰናይት ኃይል ባልነበረው ሙከራ ዕድሏን አባክናለች። ጨዋታው ሊጠናቀቅ ጥቂት ደቂቃዎች ሲቀሩ አረጋሽ ካልሳ በግራ መስመር ይዛው የገባችውን ኳስ ለሎዛ አመቻችታ ስታቀብል ለማስቆጠር ምቹ ቦታ ላይ የነበረችው ሎዛ አበራም በቀላሉ ስታስቆጥር አዲስ አበባ ከተማዎች ከዕረፍት መልስ አንድም ሙከራ ሳያደርጉ ጨዋታው በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ኢትዮ ኤሌክትሪክ 2-0 አዳማ ከተማ

10 ሰዓት ላይ የኢትዮ ኤሌክትሪክ እና የአዳማ ከተማ ጨዋታ ሲደረግ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በአሥረኛ ሣምንት ቦሌ ክፍለከተማን 2-0 በረቱበት ጨዋታ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ምንም የተጫዋች ለውጥ ሳያደርጉ ሲገቡ አዳማዎች በበኩላቸው በአሥረኛ ሣምንት በአርባምንጭ ከተማ 3-0 ሲረቱ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የ አምሥት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ኢየሩሳሌም ሎሬቶ ፣ ናርዶስ ጌትነት ፣ ሠብለ ቶጋ ፣ ማሕሌት ታደሠ እና ስመኝ ተስፋየ በ እምወድሽ ይርጋሸዋ ፣ መሠሉ አበራ ፣ ሣምራዊት ኃይሉ ፣ ሠርካአዲስ ጉታ እና ቅድስት ቦጋለ ተተክተው ገብተዋል።

ቀዝቀዝ ያለና ብዙም የተሳኩ ሙከራዎች ያልታዩበት ጨዋታ ሲሆን በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጉት አዳማዎች ሲሆኑ ትዕግሥት ዘውዴ ከቀኝ መስመር የተሻገረላትን ኳስ ወደ ግብ የሞከረችውና እና ግብ ጠባቂዋ ማርታ በቀለ በፍጥነት የመለሰችው ኳስ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ጎል ሊያስቆጥሩበት የሚችሉበት አጋጣሚ ነበር። 30ኛው ደቂቃ ላይ ሰላማዊት ጎሣየ ከዙሌይካ ጁሀር የተቀበለችውና ወደ ግብ በጥሩ ሁኔታ ሞክራው ግብጠባቂዋ ያስወጣችባት ኳስ በኤሌክትሪኮች በኩል የመጀመሪያው የተሻለ ሙከራ ነበር። በተደጋጋሚ በ ዙሌይካ ጁሀር ፣ ዓይናለም አሳምነው እና ኝቦኝ የን የግብ እድል ለመፍጠር ሲሞክሩ የነበሩት ኤሌክትሪኮች ተሳክቶላቸው 42ኛው ደቂቃ ላይ ኝቦኝ የን ግብ አስቆጥራ ኤሌክትሪክ የመጀመሪያውን አጋማሽ መርቶ እንዲወጣ አስችላለች።

ሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ የተቀዛቀዘ እና ለተመልካች የማይስብ አሰልቺ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ነበር። አዳማዎች መሠሉ አበራን ቀይረው በማስገባት የተከላካይ መስመራቸውን በማረጋጋት ወደፊት ተጠግተው ለመጫወት ሲሞክሩ ኤሌክትሪኮችም ከንቦኝ የን እና ከዙሌይካ ጁሀር በሚነሱና የመጨረሻ ኳሳቸውን በሦስቱም አጥቂዎች ዓይናለም አሳምነው ሰላማዊት ጎሣየ እና ምንትዋብ ዮሐንስ ላይ በማድረግ የግብ ዕድል ለመፍጠር ሞክረዋል።

68ኛው ደቂቃ ላይ ኝቦኝ የን ከቀኝ መስመር ያሻማችውን ኳስ ምንትዋብ ዮሐንስ አስቆጥራ ቡድኗን መሪነት አጠናክራለች። 77ኛው ደቂቃ ላይ ስመኝ ተስፋዬ የኤሌክትሪክ ተከላካዮች ባለመግባባት የሰሩት ስህተት ተጨምሮበት ብቻዋን ግብ ጠባቂ ጋር ተገናኝታ ኃይል ባልነበረው ኳስ ቡድኗን ወደ ጨዋታው ለመመለስ ወርቃማ ዕድል አምክናለች። ይሄም የጨዋታው የተሻለው የመጨረሻ ሙከራ ሆኖ በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ያጋሩ