የ20ኛ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብሮች የማሳረጊያ ፍልሚያ እንዲህ ተዳሷል።
ያለፉትን አራት ጨዋታዎች ሽንፈት ያላስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና ባሳለፍነው ሳምንት በመቀመጫ ከተማው የሚጫወተው አዳማ ከተማ ላይ ያገኘውን ድል በመድገም ደረጃውን ለማሻሻል እንደሚጥር ሲጠበቅ በዋንጫ ፉክክር ውስጥ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ ካስተናገደው ሽንፈት ያገገመበትን ድል ደግሞ በፉክክሩ ለመዝለቅ እንደሚጫወት ይታመናል።
በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም እስካሁን ሽንፈት ያላስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና በጥሩ መሻሻል ላይ ያለ ይመስላል። በውጤት ብቻ ሳይሆን በእንቅስቃሴም መጠነኛ እድገት አሳይቶ በአንፃራዊነት ከበድ ያሉትን ፍልሚያዎች ተወቷል። በተለይ በአዳማው ጨዋታ 19 ጊዜ የግብ ሙከራዎችን በማድረግ የተጋጣሚን የግብ ክልል ደጋግሞ ጎብኝቷል። ከወገብ በላይ የሚጫወቱት ተጫዋቾች የወረደ የውሳኔ አሰጣጥ ችግር እና ስል አለመሆን ለበርካታ ጨዋታዎች ዋጋ ሲያስከፍሉት ቆይቶ ያለፉትን ሁለት ጨዋታዎች ብቻ በቀደሙ ሰባት ጨዋታዎች ያስቆጠረውን ስድስት ጎል አግኝቷል። በነገው ጨዋታ ግን ቡድኑ የሚገጥመው ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ካላቸው ቡድኖች መካከል አንዱን ስለሆነ ዕድሎች ተደጋግመው ላይገኙ ስለሚችሉ የማጥቃት እንቅስቃሴውን ማሳደግ እና የሚገኙ ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል።
ባሳለፍነው ሳምንት ወልቂጤ ከተማን ሲረታ የቀደመ ብቃቱ ላይ ሳይገኝ የነበረው ሀዋሳ ከሽንፈት መልስ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ በመፈለግ እንደሆነ በሚያሳብቅ ሁኔታ በ38ኛው ደቂቃ መሪ ከሆነ በኋላ ውጤት ማስጠበቅ ላይ ተጠምዶ ጊዜውን አሳልፏል። በኳስ ቁጥጥርም ሆነ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ተዳክሞ ጫናዎችን መመከት ተያይዞ ጨዋታውን ፈፅሟል። በሀሳብ ደረጃ ይህ ሂደት ጥሩ ቢሆንም በአንዳንድ ቅፅበቶች አደጋን በራሱ ላይ እንዲጋብዝ አድርጎት ነበር። በነገው ጨዋታም የወልቂጤው ጨዋታን አይሁን እንጂ ኳሱን ለሀዲያዎች በመተው የሚታወቁበትን የሽግግር አጨዋወት ለመተግበር መንቀሳቀሳቸው የማይቀር ነው። በዋናነትም የመስመር ተጫዋቾቹ እና የፊት አጥቂዎቹን ፍጥነት ያማከለ አጨዋወት በመተግበር ሦስት ነጥብ ለማግኘት እንደሚጥርም ይጠበቃል።
ከግብ ጠባቂ ውጪ በሁሉም የሜዳ ክፍሎች የሚጫወቱ ተጫዋቾች ከግብ ጋር የሚገናኙለት ሀዲያ ሆሳዕና ነገም በቅይጥ አጨዋወቱ (ቀጥተኛ እና ኳስ በማንሸራሸር) በአብዛኛው ጊዜ በሦስት የመሐል ተከላካዮች የሚጫወተውን የሀዋሳ የኋላ መስመር በመፈተን በግልባጩ የደረጃ ሰንጠረዥ ለመገኘት ይጥራል ተብሎ ይጠበቃል። ከብሩክ በየነ ጋር በጣምራ የክለቡ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ተጫዋች የሆነው መስፍን ታፈሰ በነገው ጨዋታ መመለስ ደግሞ ለሀዋሳ የፊት መስመር የሚሰጠው ጥቅም ከፍተኛ ነው። ከኳስ ጋር እና ውጪ የመታተር ችግር የሌለበት ተጫዋቹ ከተከላካይ ጀርባ የሚገኘውን ቦታ በማነፍነፍ ቡድኑን ለመጥቀም መንቀሳቀሱ ስለማይቀር ሀዲያዎች ትኩረይ መስጠት አለባቸው። ሀዋሳም በቀጣይ ከጊዮርጊስ ጋር ለሚያደርገው ጨዋታ የሚሆነው ስንቅ ለመያዝ ጨዋታውን እንደሚፈልገው ይታመናል።
በሀድያ ሆሳዕና በኩል ከግብ ጠባቂው ሶሆሆ ሜንሳ ውጭ ሁሉም የቡድኑ አባላት ለነገው ጨዋታ ዝግጁ መሆናቸው ሲገለፅ ሀዋሳ ከተማም ቅጣት ላይ ከሚገኘው ተከላካዩ አዲስዓለም ተስፋዬ በስተቀር ሁሉንም ተጫዋች እንደሚያገኝ ተጠቁሟል።
የሳምንቱ የማሳረጊያ ጨዋታ በኃይለየሱስ ባዘዘው የመሐል ፋሲካ የኋላሸት እና ታምሩ አደም ረዳት እንዲሁም ማኑኤ ወልደፃዲቅ አራተኛ ዳኝነት ይመራል።
እርስ በርስ ግንኙነት
– ቡድኖቹ አምስት ጊዜ ተገናኝተው ሀዋሳ ከተማ ሁለቱ ሲረታ ቀሪውን ሦስት ጨዋታ ደግሞ በአቻ ውጤት ፈፅመዋል። በጨዋታዎቹም ሀዋሳ 9 ሀዲያ 5 ጎሎች አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ሀዋሳ ከተማ (3-4-3)
መሀመድ ሙንታሪ
ካሎንጂ ሞንዲያ – ላውረንስ ላርቴ – ፀጋሰው ድማሙ
ዳንኤል ደርቤ – ወንድምአገኝ ኃይሉ – በቃሉ ገነነ – መድሃኔ ብርሃኔ
ኤፍሬም አሻሞ – ብሩክ በየነ – መስፍን ታፈሰ
ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)
ያሬድ በቀለ
ፍሬዘር ካሳ – ቃለአብ ውብሸት – ግርማ በቀለ
ብርሃኑ በቀለ – አበባየሁ ዮሐንስ – ተስፋዬ አለባቸው – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – ሄኖክ አርፌጮ
ዑመድ ኡኩሪ – ባዬ ገዛኸኝ