ሪፖርት | ዐፄዎቹ ድል አድርገዋል

በሁለተኛው አጋማሽ የተሻለ የተንቀሳቀሱት ፋሲል ከነማዎች አርባምንጭ ከተማን በበዛብህ መለዮ ብቸኛ ግብ በማሸነፍ ለጊዜውም ቢሆን በሰንጠረዡ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ከፍ ብለው ለመቀመጥ በቅተዋል።

አርባምንጭ ከተማዎች በመጨረሻ ጨዋታቸው ባህር ዳር ከተማን ሲረቱ ከተጠቀሙበት የመጀመሪያ 11 ተሰላፊዎች ላይ ሦስት ለውጦችን ያደረጉ ሲሆን በዚህም ሐቢብ ከማል ፣ ፍቃዱ መኮንን እና ኡቸና ማርቲንን አስወጥተው በምትካቸው ኤሪክ ካፓይቶ ፣ በርናርድ ኦቼንግ እና አሸናፊ ፊዳ በመጀመሪያ ተሰላፊነት ያስጀመሩ ሲሆን በፋሲል ከነማዎች በኩል ደግሞ በመጨረሻው ጨዋታ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ሁለት አቻ ከተለያየውን ስብስብ ባደረጉት ብቸኛ ለውጥ ተከላካይ መስመር ላይ ያሬድ ባየህን በአስቻለው ታመነ ብቻ ተክተው ወደ ዛሬው ጨዋታ ቀርበዋል።

ጨዋታው ከመጀመሩ አስቀድሞ በቅርቡ በድንገት ከዚህ ዓለም በሞት ለተለየው የፋሲል ከነማው ደጋፊ ተሾመ ለገሰ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ የጀመረው ጨዋታ እጅግ ቀዝቃዛ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ የተመለከትንበት ነበር።

የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታ ክፍለ ጊዜ ሁለቱ ቡድኖች ፍፁም ተቃራኒ የሆነ የጨዋታ መንገድ ቢከተሉም በመሰረታዊነት ሁለቱም ቡድኖች በኩል የማጥቃት ሀሳብ እጥረትን የታዘብንበት ነበር። bንፅፅር የተሻለ የኳስ ቁጥጥር የነበራቸው ፋሲል ከነማዎች ከኳስ ውጭ ጠቅጠቅ ብለው ለመከላከል የሚሞክሩትን የአርባምንጭ ተጫዋቾችን የመከላከል ውቅር ለማስከፈት የሚረዱ መንገዶችን ለማግኘት ተቸግረው የተመለከትን ሲሆን በዚህም ረጃጅም ኳሶችን ከጥልቀት እና ከመስመር ወደ ሳጥን በመጣል ለማጥቃት ጥረት ቢያደርጉም ይህ ነው የሚባል አጋጣሚ ሳይፈጥሩ ቀርተዋል።

በአንፃሩ አርባምንጭ ከተማዎች ተደራጅቶ ከመከላከል ባለፈ ኳስ በቁጥጥራቸው ስር በምትገባበት ወቅት ወደ ማጥቃት ያደርጉት የነበረው ሽግግር ፍፁም ደካማ ነበር።

በአጋማሹ የተሻሉ የሚባሉት አጋጣሚዎች ከቆመ ኳስ የተገኙ ነበሩ ፤ በአርባምንጭ ከተማዎች በኩል በ6ኛው ደቂቃ ሙና በቀለ ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም ያሻማውን የቅጣት ምት ኳስን በነፃ አቋቋም ውስጥ ሆኖ ያገኛት ፀጋዬ አበራ የገጫት አደገኛ ኳስ ሚኬል ሳማኪ ያዳነበት እንዲሁም በ30ኛው ደቂቃ በፋሲል በኩል ኦኪኪ አፎላቢ ወደ ቀኝ ካደላ አቋቋም በቀጥታ ወደ ግብ የላካትን ኳስ ሳምሶን አሰፋ የተቆጣጠራት ኳስ ተጠቃሾች ነበሩ።

ከሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ አንስቶ ፋሲል ከነማዎች ፈጠን ባሉ የኳስ ቅብብሎች እንዲሁም በቁጥር በርክተው ወደ ተጋጣሚ የሜዳ አጋማሽ በመድረስ ረገድ ቀስ በቀስ ተነቃቅተው ተመልክተናል።

ታድያ ይህ የፋሲሎች መሻሻል በ61ኛው ደቂቃ ፍሬ አፍርቷል ፤ ከቀኝ መስመር ከተሻማ ኳስ የተገኘ ኳስ በረከት ደስታ እና በዛብህ መለዮ ከሳጥኑ ጠርዝ በግሩም አንድ ሁለት ቅብብል ሳጥን ውስጥ ያደረሱትን ኳስ በዛብህ መለዮ በግሩም ሁኔታ አስቆጥሮ ቡድኑን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

በደቂቃዎች ልዩነት ሱራፌል ዳኛቸው ከርቀት በቀጥታ ወደ ግብ አክርሮ የመታው የቅጣት ምት የግቡን አግዳሚ ለትማ ወደ ውጭ ወጣችበት እንጂ ፋሲሎች መሪነታቸውን ለማስፋት ተቃርበው ነበር።

ከግብ ከማስተናገዳቸው አስቀድሞ ማጥቃቱን ሊያሻሽሉ የሚችሉ የግለሰቦችን ለውጥ ማድረግ የጀመሩት አርባምንጮች በሂደት ቅርፃቸውን በመለወጥ በሦስት አጥቂዎች ለመጫወት ሙከራ አድርገዋል።

በዚህ ለውጥ ውስጥ ሦስቱ የአርባምንጭ አጥቂዎች ከተቀረው የቡድን አባላት በቂ የሆነ ድጋፍ ባያገኙም እድሎችን ከምንም ለመፍጠር በተለይ ፍቃዱ መኮንን ያደርግ የነበረው ጥረት የሚደነቅ ነበር።

ፋሲሎች ቀስ በቀስ የነበራቸው የማጥቃት ፍላጎት ተቀዛቅዞ በሂደት ውጤቱን ለማስጠበቅ በሚመስል መልኩ ጥንቃቄን አክለው የተጫወቱ ሲሆን ጥፋቶች የበረከቱበት ጨዋታ ተጨማሪ ግብ ሳያስመለክተን ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ዐፄዎቹ በ34 ነጥብ ሀዋሳ ከተማ እስኪጫወት ድረስ ወደ 2ኛ ደረጃ ከፍ ሲሉ በአንፃሩ አዞዎቹ ደግሞ በ26 ነጥብ 7ኛ ደረጃ ላይ ረግተዋል።