ሪፖርት | ሀዲያ ሆሳዕና ተከታታይ ድሉን አሳክቷል

የ20ኛ ሳምንት የመጨረሻው የምሽት ጨዋታ በሀዲያ ሆሳዕና አሸናፊነት ተጠናቋል።

አዳማ ከተማ ላይ ጣፋጭ ድል ካሳኩበት ጨዋታ ሀዲያዎች ባዬ ገዛኸኝ እና ኢያሱ ታምሩን በሳምሶን ጥላሁና እና ሀብታሙ ታደሰ ሲለውጡ በሌላ በኩል ሀዋሳዎች በጠባብ ውጤት ወልቂጤን ካሸነፉበት ስብስብ ግብ ጠባቂውን ዳግም ተፈራን በመሐመድ ሙንታሪ ብቻ በመተካት ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ተመሳሳይ የማጥቃት አጨዋወትን የሚከተሉት ሁለቱ ቡድኖች አንዱ በአንዱ ላይ መሀል ሜዳውን በመቆጣጠር ብልጫ ወስዶ ጎል ለማስቆጠር ያሰቡ ቢመስሉም መስመሮችን ለመጠቀም ሲታትሩ ተመልክተናል። በተለይ ሀዲያዎች የግራ መስመርን መሰረት ያደረገ ፈጣን የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ነበር። ጥቃቱ እስከ 12ኛው ደቂቃ ዘልቆ የሀዋሳው ተከላካይ ፀጋሰው ድማሙ ጉዳት አስተናግዶ ህክምና ለማግኘት ወደ ሜዳ በወጣበት አጋጣሚ የሀዲያው አጥቂ ሀብታሙ ታደሰ በከቀኝ መስመር ሳጥን ውስጥ በመግባት ከእርሱ በተሻለ ቦታ ለሚገኙት አጥቂዎች ለማቀበል ባሰበበት ጊዜ በሀዋሳ ተከላካዮች ተቋርጦ የማዕዘን ምት ሀዲያ አግኝተው ወደ ጎልነት ቀይረውታል። ከማዕዘን ምት የተሻገረውን በ14ኛው ደቂቃ ሀብታሙ ታደሰ በግንባር ኳሱን ከመሬት ጋር አንጥሮ ለሀዲያ የመጀመርያውን ጎል አስቆጥረዋል።

ከጎሉ መቆጠር ከስድስት ደቂቃ በኋላ ሀዋሳዎች ወደ ጨዋታ የሚመልሳቸውን ጎል አግኝተዋል። ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ ከሜዳ ክፍሉ በረጅሙ የላካትን ኳስ ብሩክ በየነ ኳሷን ለመቆጣጠር በሚያደርገው ጥረት ተባረክ ሔፋሞ ከጎሉ ፊት ለፊት ከሳጥን ውጪ ያገኛትን ኳስ በጥሩ ሁኔታ በመምታት የአቻነቱን ጎል ለቡድኑ አስገኝቷል። ከጨዋታው ሦስት ነጥብ የማግኘት ፍላጎት ቢኖራቸውም በተደጋጋሚ በሚሰሩ ጥፋቶች ጨዋታው እየተቆራረጥ እና የተሳካ ቅብብሎሽ ለማድረግ መረጋጋት የማይታይባቸው መሆኑን ተከትሎ ቀሪዎቹን ደቂቃዎች አስቸጋሪ አድርጎታል።

በዚህ ሂደት የቀጠለው ጨዋታ 35ኛው ደቂቃ ሀዲያዎች ሁለተኛ ጎል ማስቆጠር የሚችሉበትን ዕድል ሳጥን ውስጥ በጥሩ ቅብብል በመግባት ወደ ውስጥ ያሻገረውን ጎሉ ቅርበት በሀዋሳ ተከላካዮች ተደርቦ የተመለሰውን ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን በጠንካራ ምት የመታውን ግብጠባቂው መሐመድ በአስደናቂ ሁኔታ ጎል እንዳይሆን አድርጎታል። በ44ኛው ደቂቃ ሳይታሰብ ወደ ማጥቃት ሽግግር የገቡት ሀዋሳዎች ከረጅም ርቀት ዳዊት ታደሰ አክርሮ የመታውን ግብ ጠበቂው ያሬድ ከተቆጣጠረው በኋላ የመጀመርያው አጋማሽ በአንድ አቻ ውጤት ወደ መልበሻ ክፍል አምርቷል።

በአሰልጣኝ ሙሉጌታ የጨዋታ አቀራረብ ለውጥ በማድረግ ከዕረፍት መልስ ወደ ሜዳ የተመለሱት ሀዲያዎች መምራት የሚችሉበትን ጎል በ53ኛው ደቂቃ አግኝተዋል። ከራሳቸው የሜዳ ክፍል አደራጅተው የመጡትን ኳስ በቀኝ መስመር ብርሀኑ ብቀለ ያሻገረውን ሀብታሙ ታደሰ ኳሱን ተቆጣጥሮ ነፃ አቋቋም ላይ ለሚገኘው ፍቅረየሱስ ተክለብርሀን አቀብሎት በግሩም ሁኔታ በመምታት ለቡድኑ ሁለተኛ ጎል አስቆጥሯል። ከጎሉ መቆጠር በኋላ የጨዋታውን መልክ የሚቀይሩ የተለያዩ ክስቶች እያስመለከተን ይቀጥላል ቢባልም እንቅስቃሴው እየተቆራረጠ ቀጥሎ በ77ኛው ደቂቃ የሀዋሳው ተከላካይ በራሱ ላይ ሦስተኛ ጎል ለሀዲያ ማስቆጠር ችሏል።

ተቀይሮ የገባው ባዬ ገዛኸኝ ሀዋሳዎች በራሳቸው የሜዳ ክፍል ተረጋግተው ኳሱን እንዳይጀምሩ ለማድረግ በሚያደርገው ጥረት ተከላካዩ ካሎንጂ ሞንዲያ ለቡድን አጋሩ ግብ ጠባቂው መሐመድ ሙንታሪ ኳሱን ለማቀበል የላከው ኳስ ከእግሩ ሾልካ ወደ ጎልነት ተቀይራለች።

በዚህች ጎል ተሰፋ የቆረጡት ሀዋሳዎች ወደ ጨዋታው ለመመለስ ምንም ዓይነት ፍላጎት ሳይታይባቸው ቆይተው ምን አልባትም በተጨማሪው ደቂቃ አራተኛ ጎል ሊቆጠርባቸው የሚችል ዕድል ባዬ ገዛኸኝ ሳይታሰብ ከቀኝ መስመር ጠርዝ አክሮ የመታውን ግብ ጠባቂው መሐመድ እንደምንም አድኗታል። ጨዋታውም በዚህ መልኩ በሀዲያ 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ውጤቱን ተከትሎ ሀዲያ ሆሳዕናዎች ደረጃቸውን በማሻሻል ስድስተኛ ደረጃ ሲይዙ በአንፃሩ ሀዋሳዎች አንድ ደረጃ ዝቅ ብለው ሦስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።

ያጋሩ