በሀዲያ ሆሳዕና አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የምሽቱ ጨዋታ ፍፃሜን ተከትሎ አሰልጣኞች ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡
አሰልጣኝ ሙሉጌታ ምህረት – ሀዲያ ሆሳዕና
ስለጨዋታው
“የመጣነው ለማሸነፍ ብቻ ነው፡፡ በተግባር እዚሁ አሳይተናል እንቅስቃሴውም ከዕረፍት በኋላ የተሻለ ነበር፡፡ በጎልም በእንቅስቃሴውም ጥሩ ስለነበርን ፤ የነበረው እስከ አሁን ጥሩ ነበር፡፡
ስለ ወሰዱት የኳስ ቁጥጥር ብልጫ
“ከዕረፍት በፊትም ከዕረፍት በኋላም ተመሳሳይ ነገር እንዲሰሩ ነበር፡፡ ግን ከ4-3-3 ወደ 3-5-2 ለውጠን የኳስ ቁጥጥሩ የተሻለ እንዲሆን በብዛት የለመድነው በዛ ነበር እና አድቫንቴጅ የሚኖረን ደግሞ የተሻለ ለማሸነፍም ኳስን የተቆጣጠረ ቡድን አድቫንቴጆች አሉት፡፡ ዛሬ ደግሞ ኳስ ቁጥጥሩ ላይ ትኩረት እንዲያደርጉ የፈለኩት ከመጀመሪያው ጀምሮ ቢሆንም ጥሩ ነበር፡፡ወደ መጨረሻዎቹ እና ከዕረፍት በኋላ ላይ ለመቆጣጠር የሞከሩት፡፡
በአዳማ ስለ ተሻሻለው ሀድያ ሆሳዕና
“ከሀዋሳ ፣ ከድሬዳዋ እዚህ አዳማ ላይ የተሻለ ነው ብዬ የማስበው ልጆቹም እኛ በራሳችንም ብዙ የለወጥናቸው ነገሮች አሉ፡፡ ለዛም ነው የተሻለ የሆነው እዚህ ከተማ ላይ፡፡”
አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ
ስለ ሽንፈቱ
“ስህተቶች ናቸው፡፡ ሆኖም እኔ ዳኝነት ላይ ቅሬታ አለኝ፡፡ ምክንያቱም መጫወት አልቻልንም ተቃራኒ ቡድን በአጠቃላይ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ከኳስ ውጪ የሚደረጉ ንክኪዎች የእኛን ተጫዋቾች ከእንቅስቃሴ ውጪ ነው ያደረጋቸው፡፡ ይሄንን እንዴት ዝም እንዳለ አላውቅም ፤ ከእዛ ውጪ የእኛዎቹ አግሬሲቭ ሆነው ሲሄዱ ደግሞ በተቃራኒው ውሳኔ ሲሰጥ ነው የማየው ተናግሬ ባለውቅም ዛሬ መናገር ስላለብኝ እናገራለሁ፡፡ የጨዋታውን እንቅስቃሴ በአጠቃላይ የቀየረው ዳኝነቱ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ዳኝነት ሊኖርም አይገባም የምንጫወተው ለውጤት ነው፡፡ ስለዚህ የተጫዋቾቼን እንቅስቃሴ በአጠቃላይ ያበላሸብን ዳኝነት ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ የቱም ጋር ስህተት ልንሰራ እንችላለን በተለይ ወደ ፊት ስንሄድ መጫወት አልቻልንም በተቃራኒው ውሳኔው ለተቃራኒ ቡድን የሚደረግ ከሆነ ስሜት ይጎዳል፡፡ ስሜታዊ አድርጓል ተጫዋቾቻችንን፡፡
የቡድኑ ድክመት
“አንዳንዴ ይከሰታል፡፡ መጀመሪያ ጎሉን ባላሰብነው ሰዓት መቆጠሩ ትንሽ እንቅስቃሴውን ቢያወርደውም ተመልሰን ግን ወደ እንቅስቃሴው ገብተናል፡፡ ግን እንዳልኩህ ልጆቻችን ዛሬ በጣም ስሜታዊ ሆነዋል፡፡ መረጋጋት ባለብህ ሰዓት ካልተረጋጋህ አስቸጋሪ ነው፡፡ የሰው ቅያሬም ብናደርግ ተመሳሳይ ነው የነበረው እና ከመስመር እንድንወጣ ያደረገን ይሄ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡