የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ 11ኛ ሳምንት የሁለተኛ ቀን ጨዋታዎች ውሎ

ዛሬም በመሸናነፍ በተጠናቀቁ ሦስት ጨዋታዎች በቀጠለው የኢትዮጵያ ሴቶች ፕሪምየር ሊግ መከላከያ በሰፊ ልዩነት ሲያሸንፍ ቦሌ ክፍለ ከተማ እና ጌዲዮ ዲላም ድል አጣጥመዋል።

በቶማስ ቦጋለ

አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ 0-6 መከላከያ

ረፋድ 03:00 ላይ አቃቂ ክፍለከተማ ከ መከላከያ ሲገናኙ በአሥረኛ ሣምንት አራፊ የነበሩት አቃቂዎች በዘጠነኛ ሣምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር ሁለት አቻ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ምንም ዓይነት ለውጥ ሳያደርጉ ሲገቡ በመከላከያዎች በኩል በአስረኛ ሣምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር አንድ አቻ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የ ሦስት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል። በዚህም መስከረም ካንኮ ፣ ዙሪያሽወርቅ መልኬ እና ሥራ ይርዳው በዓይናለም አደራ ፣ ማዕድን ሣህሉ እና ረሂማ ዘርጋው ተተክተው ገብተዋል።

የመከላከያ ፍፁም የበላይነት በታየበት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታው 4ኛ ደቂቃ ላይ ቤዛዊት ተስፋዬ ከግራ መስመር ወደ ግብ በጥሩ ሁኔታ በሞከረችውና የላይኛውን አግዳሚ ታክኮ በወጣው ኳስ የግብ ሙከራ ማድረግ የጀመሩት መከላከያዎች 18ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ ተመስገን በቀኝ መስመር ከማዕዘን ያሻማችውን ኳስ ሥራ ይርዳው በግሩም ሁኔታ በግንባሯ በመግጨት ባስቆጠረችው ግብ መሪ መሆን ችለዋል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ሴናፍ ዋቁማ በቀኝ መስመር ከሥራ ይርዳው የተቀበለችውን ኳስ ተጠቅማ በጥሩ አጨራረስ ለጦሩ ሁለተኛ ግብ ማስቆጠር ችላለች።
መከላከያዎች በቁጥር በዛ ብለው በተጋጣሚ የግብ ክልል በመገኘት የተለያዩ የግብ ዕድሎች ሲፈጥሩ 26ኛው ደቂቃ ላይ መሳይ ተመስገን ብቻዋን ያገኘችውን ኳስ ከጨዋታ ውጪ ነኝ ብላ በመዘናጋት ከተወችው በኋላ የመስመር ዳኛዋ ምንም አለማለቷን ስታይ ዘግይታ ኳሱን ለመግፋት በመሞከር እና ብቻዋን ለነበረችው ሴናፍ ዋቁማ ከሩጫዋ የዘገየ ኳስ በማቀበል ወርቃማ ዕድል አባክናለች። በአንጻሩ ከራሳቸው የሜዳ ክልል ለመውጣት የተቸገሩት አቃቂዎች የመጀመሪያውን ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ያደረጉት 28ኛው ደቂቃ ላይ ሲሆን ከውሃ ዕረፍት መልስ መከላከያዎች ተረጋግተው ወደቦታቸው ባልተመለሱበት ሁኔታ በፍጥነት የጀመሩትን ኳስ ዓይናለም መኮንን ለበሬዱ በቀለ አመቻችታ ብታቀብልም በሬዱ ያደረገችውን የግብ ሙከራ ግብጠባቂዋ መልሳዋለች።

በተደጋጋሚ በቀላሉ ወደተጋጣሚ ክልል መግባት የቻሉት መከላከያዎች በሥራ ይርዳው በሴናፍ ዋቁማ እና በመሳይ ተመስገን የተለያዩ የግብ ዕድሎች መፍጠር ሲችሉ በተለይም 36ኛው ደቂቃ ላይ ሥራ ይርዳው እና ሴናፍ ዋቁማ ብቻቸውን ግብ ጠባቂ ጋ ሲገናኙ ሥራ ለሴናፍ አመቻችታ ብታቀብልም ሴናፍ ቀድማ ገብታ ስለነበር ከጨዋታ ውጪ በመሆኗ ትልቅ የግብ ዕድል አባክነዋል። በጨዋታው ከራሳቸው የግብ ክልል ለመውጣት የተቸገሩት አቃቂዎች በጨዋታው ሁለተኛ የግብ ሙከራቸውን 40ኛው ደቂቃ ላይ ወለላ ባልቻ ከረጅም ርቀት በሞከረችውና ግብ ጠባቂዋ በያዘችው የቅጣት ምት አድርገዋል። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት መሳይ ተመስገን በግሩም ሁኔታ ገፍታ ወደተጋጣሚ ሳጥን ይዛው ገብታ ለሥራ ይርዳው አመቻችታ ብታቀብልም ሥራ ይርዳው መከላከያዎች ተጨማሪ ግብ ሊያስቆጥሩ የሚችሉበትን ዕድል አባክናለች።

ሁለተኛው አጋማሽ በጀመረ በሁለት ደቂቃ ውስጥ ሴናፍ ዋቁማ በተረጋጋ እና ጥሩ በሆነ አጨራረስ ለቡድኗ ሦስተኛ ግብ አስቆጥራ የመከላከያን መሪነት ማጠናከር ችላለች። 61ኛው ደቂቃ ላይ አሶሬ ኃይሶ ከግራ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ነፃ ሆና ያገኘቸው ፍሬህይወት በድሉ አቃቂዎችን ወደ ጨዋታው ለመመለስ የሚያስችል አጋጣሚን አባክናለች። ከዕረፍት መልስም ፍጹም የበላይነቱን የወሰዱት መከላከያዎች ሲሆኑ ቤዛዊት ተስፋዬ ያቀበለቻትን ኳስ ሴናፍ ዋቁማ በምርጥ አጨራረስ አስቆጥራ ሐት-ትሪክ መሥራት ችላለች።

በተወሰነ መልኩ ከተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ በቻሉት አቃቂዎች በኩል 76ኛው ደቂቃ ላይ አሶሬ ኃይሶ ከረጅም ርቀት የሞከረችውና የላይኛውን አግዳሚ ታክኮ የወጣው ኳስ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። ዓይናለም መኮንን በቀኝ መስመር ላይ የሞከረችውና ግብ ጠባቂዋ የያዘችው ኳስም ሌላኛው አቃቂዎች የፈጠሩት የግብ ዕድል ነበር። 82ኛው ደቂቃ ላይ ህድአት ካሱ በግራ መስመር ገፍታ የወሰደችውን ኳስ ለሥራ ይርዳው ስታቀብል ሥራ ያደረገችውን የግብ ማግባት ሙከራ ትዕግስት ሽኩር በድንቅ ሁኔታ ስትመልሰው በድጋሚ ኳሱን ያገኘችው ሥራ ወደግብ ብትሞክርም የላይኛውን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶባታል። በአንድ ደቂቃ ልዩነት ሴናፍ ዋቁማ ከቤዛዊት ተስፋዬ የተቀበለችውን ኳስ ከሳጥን ውጪ በግሩም ሁኔታ ብትሞክርም የላይኛውን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶባታል። 90 ኛው ደቂቃ ላይ ከ ማዕድን ሣህሉ የተቀበለችውን ኳስ ሴናፍ ዋቁማ በድንቅ አጨራረስ ለራሷ አራተኛ ለቡድኗ አምሥተኛ ግብ ስታስቆጥር የጨዋታው የመጨረሻ ደቂቃ ላይ ህድአት ካሱ ከግራ መስመር ያሻማችውን ኳስ ጤናየ ዘርጋው በራሷ ላይ አስቆጥራ ጨዋታው በመከላከያ 6-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ባህር ዳር ከተማ 0-2 ቦሌ ክፍለ ከተማ

ቀን 8፡00 ላይ ባህርዳር ከተማ ከቦሌ ክፍለ ከተማ ሲገናኙ ባህር ዳር ከተማዎች በአሥረኛ ሳምንት በጌዴኦ ዲላ 2-0 ከተሸነፉበት አሰላለፍ የሦስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ ባንቺዓየሁ ደመላሽ ፣ ቤዛዊት መንግሥቴ እና ሜላት ደመቀ በሽብሬ ኮንቦ ፣ ቅድስት ዓባይነህ እና ትዕግሥት ወርቄ ተተክተው ሲገቡ ቦሌዎች በበኩላቸው በአሥረኛ ሣምንት በኢትዮ ኤሌክትሪክ 2-0 ከተረቱበት ጨዋታ የአምስት ተጫዋቾች ለውጥ ሲያደርጉ የምሥራች ሞገስ ፣ ይዲዲያ አሜ ፣ ሜላት ጌታቸው ፣ ምርጥነሽ ዮሐንስ ፣ እና ሲፈን ተስፋየ በስንታየሁ ኢርኮ ፣ ብዙነሽ እሸቱ ፣ ሒሩት ተስፋዬ ፣ መዐዛ አብደላ እና ትዕግሥት ሙሉዓለም ተተክተው ገብተዋል።

የጨዋታው የመጀመሪያው አጋማሽ ተመጣጣኝ ፉክክር የታየበት ሲሆን የጣና ሞገደኞቹ ተረጋግቶ ኳስ ይዞ ለመጫወት እና ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ቢሞክሩም ከተከላካይ እና ከአጥቂ መሀል ሆኖ የግብ ዕድል ለመፍጠር የሚሞክር ተጫዋች ባለመኖሩ አብዛኞቹ ኳሶች የተቆራረጡ ነበሩ። ቦሌዎች በበኩላቸው መሃል ላይ በቁጥር በመብዛት በፍጥነት ወደተጋጣሚ የግብ ክልል ለመድረስ ሲሞክሩ ብዙ ውጤታማ ቅብብሎችም አድርገዋል።
በጨዋታው የመጀመሪያ ደቂቃዎች ባህር ዳሮች ተደጋጋሚ የግብ ዕድል ሲፈጥሩ 7ኛው ደቂቃ ላይ አዳነች ጌታቸው ከረጅም ርቀት በሞከረችው እና ግብ ጠባቂዋ በያዘችው ኳስ የመጀመሪያ ኢላማውን የጠበቀ ሙከራቸውን አድርገዋል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ቤዛዊት መንግሥቴ ከግራ መስመር ወደ ግብ ያሻማችውን እና ትልቅ የግብ ዕድል የፈጠረውን ኳስ የቦሌ ተከላካዮች በፍጥነት አፅድተውታል። 15ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም ግዛቸው ግሩም የቅጣት ምት ብትመታም የላዩን አግዳሚ ገጭቶ ተመልሶባታል ይሄም በባህር ዳር በኩል በጣም ያስቆጨ አጋጣሚ ነበር። ቦሌዎች 16ኛው ደቂቃ ላይ ሲፈን ተስፋየ ከግራ መስመር አክራራ በመታችውና ግብ ጠባቂዋ በድንቅ ብቃት በመለሰችው ኳስ የመጀመሪያውን የተሻለ ሙከራቸውን አድርገዋል።

በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ንግሥት በቀለ ከቀኝ መስመር ጥሩ አድርጋ የሞከረችና ግብ ጠባቂዋ የያዘችው ኳስ በቦሌዎች በኩል አስቆጪ አጋጣሚ ነበር። 41ኛው ደቂቃ ላይ መንደሪን ታደሠ በግራ መስመር ከሜላት ደመቀ የተሻገረላትን ኳስ በጥሩ ሁኔታ በግንባሯ ብትገጭም የላይኛውን አግዳሚ ታክኮ ወጥባታል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት የቦሌዋ ጤናየ ለታሞ ከግራ መስመር ያሻገረችውን ኳስ ንግሥት በቀለ የግል ብቃቷን ባስመሠከረ እና ሁሉንም ተመልካች ባስገረመ ሁኔታ በአስደናቂ አጨራረስ አስደናቂ ግብ አስቆጥራ ቦሌ የመጀመሪያውን አጋማሽ መርቶ እንዲወጣ አስችላለች።

በሁለተኛው አጋማሽ ቦሌዎች በጋለ የጨዋታ ስሜት ሲቀርቡ የጣና ሞገደቹ በበኩላቸው ይበልጥ ተቀዛቅዘው ቀርበዋል። በቦሌዎች በኩል በግራ መስመር በባለፈው ጨዋታ ያልነበረችው እና ዛሬ ወደ ጨዋታው የተመለሰችው የምሥራች ሞገስ በግሏ እንደሌሎቹ የቡድን አጋሮቿ ጥሩ ቀን ስታሳልፍ ለቡድኗ የተከላካይ መስመሩን በማጠናከር እና አደገኛ ኳሶችን በማቋረጥ በኩል ተከላካይ ክፍሉን በማረጋጋት ቦሌ ይበልጥ ወደፊት ተጭኖ እንዲጫወት ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጋለች። በሲፈን ተስፋየ ፣ በጤናየ ለታሞ እና በንግሥት የተለያዩ የግብ ዕድሎች መፍጠር የቻሉት ቦሌዎች ተሳክቶላቸው 58ኛው ደቂቃ ላይ ንግሥት በቀለ ከግራ መስመር ያሻገረችላትን ኳስ ጤናየ ለታሞ በአግባቡ ተጠቅማ በማስቆጠር የቦሌን መሪነት አጠናክራለች።

በአራት ደቂቃዎች ልዩነት ትርሲት ወንድወሠን በጥሩ ሁኔታ የሞከረችው እና ግብ ጠባቂዋ ስትመልሰው ከላይኛው አግዳሚ ገጭቶ የተመለሰውን ኳስ ንግሥት በቀለ ብታስቆጥርም ከጨዋታ ውጪ በሚል ተሽሮባታል። ሞገደኞቹ ወደ ጨዋታው ለመመለስ ተቀይራ ገብታ ጥሩ በተንቀሳቀሰችው ሳባ ኃ/ሚካኤል ፣ በቤተልሔም ግዛቸው እና በምስር ኢብራሂም የተለያዩ የግብ ዕድሎች መፍጠር ቢችሉም ሳይሳካላቸው ቀርቷል። በተለይም ሳባ ኃ/ሚካኤል ከረጅም ርቀት የሞከረችውና የግብ ጠባቂዋ ስህተት ተጨምሮበት ወደማዕዘን የወጣው ኳሶ በባህር ዳሮች በኩል ከዕረፍት መልስ የተሻለው ሙከራ ነበር። 87ኛው ደቂቃ ላይ የቦሌዋ ምርጥነሽ ዮሐንስ ከቀኝ መስመር ያደረገችውን ሙከራ ግብ ጠባቂዋ በጥሩ ብቃት አድናዋለች። የጨዋታው መጨረሻ የዳኛ ፊሽካ ሲጠበቅ ከተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ነፃ ኳስ ያገኘቸው የባህር ዳር ከተማዋ ምስር ኢብራሂም ኃይል ባልነበረው ሙከራ ትልቅ ዕድል አባክናለች። ይሄም የጨዋታው የመጨረሻ ትዕይንት ሆኖ ጨዋታው በቦሌ ክፍለከተማ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።

ድሬዳዋ ከተማ 0-1 ጌዲዮ ዲላ

10:00 ሰዓት ላይ የ11ኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ በድሬዳዋ ከተማ እና በ ጌዴኦ ዲላ መካከል ሲደረግ ድሬዎች በ10ኛ ሳምንት ከመከላከያ ጋር አንድ አቻ ሲለያዩ ከተጠቀሙት አሰላለፍ ምንም ለውጥ ሳያደርጉ ሲገቡ ጌዴኦ ዲላዎች በበኩላቸው በአሥረኛ ሣምንት ባህርዳር ከተማ ጋር 2 – 1 በሆነ ውጤት ወሳኝ ድል ሲቀዳጁ ከተጠቀሙት አሰላለፍ የሁለት ተጫዋቾች ለውጥ አድርገዋል በዚህም ግብ ጠባቂ ላይ መኪያ ከድር በሣራ ብርሃኑ ስትተካ ጤናየ ወመሴ በፅዮን ማንጁራ ተተክተው ጀምረዋል።

ጨዋታው በመጠኑም ቢሆን የተቀዛቀዘ የነበር ሲሆን ጌዴኦ ዲላዎች ካለፉት ጨዋታዎች በብዙ መልኩ ተሽለው ሲቀርቡ ድሬዳዋ ከተማዎች በበኩላቸው የተሻለ የኳስ ቁጥጥር እና የጨዋታ ብልጫ ቢኖራቸውም የተሳኩ የግብ ዕድሎችን በመፍጠር በኩል ግን ካለፉት ጨዋታዎች ተዳክመው ቀርበዋል። የጨዋታውን የመጀመሪያ ሙከራ ያደረጉት ድሬዎች ሲሆኑ 6ኛው ደቂቃ ላይ ሰርካለም ባሳ ከቤተልሔም ታምሩ የተቀበለችውና ወደ ግብ የሞከረችው ኳስ የላዩን አግዳሚ ታክኮ ወጥቶባታል። በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት ባንቺይርጋ ተስፋየ ከግራ መስመር ወደግብ የሞከረችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ ይዛባታለች። 13ኛው ደቂቃ ላይ እንዲሁ ቤተልሔም ታምሩ ከግራ መስመር የሞከረችውና ግብ ጠባቂዋ የያዘችው ኳስ ሌላኛው በድሬዎች በኩል የተሻለው ሙከራ ነበር። 15ኛው ደቂቃ ላይ ባንቺይርጋ ተስፋይዬ ኳስ በእጅ በመንካቷ የተሰጠውን የፍጹም ቅጣት ምት በተከታታይ ጨዋታዎች ምርጥ እንቅስቃሴ ያሳየችው አዲስ ንጉሤ አስቆጥራ ጌዴኦ ዲላዎችን መሪ አድርጋለች። ከግቧ መቆጠር በኋላ ጌዴኦ ዲላዎች ወደራሳቸው የግብ ክልል በጣም በመጠጋት በሚያገኙት ኳሱም በመልሶ ማጥቃት የግብ ዕድል ለመፍጠር በመሞከር በተረጋጋ ሁኔታ ውጤታቸውን አስጠብቀው ለመውጣት ሲጥሩ ታይተዋል።

ድሬዎች በበኩላቸው በኳስ ቁጥጥሩ በጣም የተሻሉ የነበሩ ሲሆን ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ቢደርሱም በከፍተኛ የግብ ማስቆጠር ጉጉት የተነሳ ባለመረጋጋት ብዙ የግብ ዕድሎችን አባክነዋል። 39ኛው ደቂቃ ላይ ቤተልሔም ታምሩ ከግራ መስመር ያገኘችውን የቅጣት ምት ወደ ግብ በጥሩ ሁኔታ ብትሞክርም ግብ ጠባቂዋ አድናዋለች። የመጀመሪያው አጋማሽ ከመጠናቀቁ በፊት ማርያም ታደሠ ከቅጣት ምት ወደጎል ያሻማችውን ኳስ ነፃ ሆና ያገኘችው ዝናቧ ሽፈራው ኃይል ባልነበረው ኳስ የጌዴኦ ዲላዎችን መሪነት ማጠናከር የሚችል ትልቅ የግብ ዕድል አባክናለች።

ከዕረፍት መልስ የተቆራረጡ ቅብብሎች የበዙበት ክፍለጊዜ የነበረ ሲሆን 53ኛው ደቂቃ ላይ የድሬዋ ብርቄ አማረ ከቅጣት ምት ወደግብ የሞከረችውን ኳስ ግብ ጠባቂዋ ስትመልሰው ነጻ ሆና ያገኘችው ሰርካለም ባሳ ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ ብታደርግም ኳሱ ከግብ ጠባቂዋ ሲያልፍ ሙሉ ትኩረቷ ከኳሱ የነበረው ኢየሩስ ኤልያስ በግሩም ሁኔታ አፅድታ የማዕዘን ምት አድርጋዋለች። በሦስት ደቂቃዎች ልዩነት የድሬዋ ቤተልሔም ታምሩ ከግራ መስመር የተገኘውን የቅጣት ምት ተጠቅማ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ ብትሞክርም ራሄል መሰሉ በአስደናቂ ሁኔታ በግንባሯ ገጭታ አስወጥታዋለች። 63ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ ንጉሤ በግራ መስመር ከቅጣት ምት ያሻማችውና ዝናቧ ሽፈራው ያባከነችው በቀላሉ በግንባር ተገጭቶ ግብ የሚሆን ኳስ ወደኋላ ተስበው እየተጫወቱ ከቆሙ ኳሶች የግብ ዕድል ለመፍጠር የፈለጉትን ጌዴኦ ዲላዎች ያስቆጨ አጋጣሚ ነበር።

በሁለት ደቂቃዎች ልዩነት የድሬዋ ታደለች አብርሃም ከግራ መስመር ያደረገችው ጥሩ የግብ ማግባት ሙከራ በግብ ጠባቂዋ ጥሩ ብቃት ግብ ከመሆን ቀርቷል። በጥቂት ደቂቃዎች ልዩነት ብርቄ አማረ ከቀኝ መስመር ያሻማችውና ሠርካለም ባሳ ያባከነችው ትልቅ የግብ ማግባት ዕድል በድሬዎች በኩል እጅግ አስቆጪ አጋጣሚ ነበር። ከዚህ ሙከራ በኋላ የዳኛ ፊሽካ የበዛበት እና እጅግ የተቀዛቀዘ የጨዋታ ስሜት አስተናግዶ ብዙም የተሳኩ ሙከራዎች ሳይደረጉ ጨዋታው በጌዴኦ ዲላ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።