በወራጅ ቀጠናው ቅርቃር የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለን ማገዱን ሶከር ኢትዮጵያ አረጋግጣለች።
የ2010 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ባለቤቱ ጅማ አባ ጅፋር ያለፉትን ዓመታት በሜዳ እና ከሜዳ ውጪ ባሉ ችግሮች ተተብትቦ ላለመውረድ ሲጫወት ቆይቷል። ዘንድሮም አሠልጣኝ አሸናፊ በቀለን በመቅጠር ሊጉን ቢጀምርም በ20 ጨዋታዎች 13 ነጥቦችን ብቻ ሰብስቦ 15ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የክለቡ አመራር ቦርድ ከትናንት በስትያ ግምገማ አከናወንኩ ካለ በኋላ ትናንት ምሽት ዋና አሠልጣኙ አሸናፊ በቀለ በልምምድ እና ቀሪ ጨዋታዎች ቡድኑን እንዳይመሩ የእግድ ውሳኔ አስተላልፏል። ከውጤት መጥፋቱ ጉዳይ ውጪ ለእግዱ እንደ ምክንያትነት የቀረበው ደግሞ ያልተገባ ከተጫዋች ጋር ግንኙነት መፍጠር፣ በጋራ በመወያየት እና በመተጋገዝ እንዲሁም ተጫዋቾቹን በአግባቡ በመከታተል ለውጥ ለማምጣት እምብዛም ፍላጎት እንደሌለ ከክለቡ አባላት ጋር (ተጫዋቾች እና አመራሮች) ከትናንት በስትያ በተደረገ ግምገማ መታወቁን ተከትሎ እንደሆነ በእግዱ ደብዳቤ ተገልጿል። በደብዳቤው ላይ እንደተገለፀው ግን ከትናንት በስትያ ከተጫዋቾች ጋር በጋራ ግምገማ እንዳልተደረገ ያረጋገጥን ሲሆን በተናጥል ብቻ የተወሰኑ ተጫዋቾችን የክለቡ አመራሮች አነጋግረው ውሳኔው እንደተወሰነ ሰምተናል።
ከወራት በፊት ምክትል አሠልጣኙ ኢያሱ መርሐፅድቅን ከዋናው ቡድን አግዶ አሁን ዋና አሠልጣኙ አሸናፊ በቀለን ያገደው ክለቡ ቀሪ ጨዋታዎችን በምክትል አሠልጣኙ የሱፍ ዓሊ እየተመራ እንደሚቀጥል ታውቋል።