ድሬዳዋ ከተማ ለሊጉ አክስዮን ማኀበር ቅሬታ አስገብቷል

በትናንት በስትያው ጨዋታ ዙርያ ድሬዳዋ ከተማዎች ቅሬታ አለን በማለት ለሊጉ አክስዮን ማኀበር ደብዳቤ አስገብተዋል።

የ20ኛ ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታዎች ትናንት ሲገባደዱ በሦስተኛው ቀን የምሽት መርሐ-ግብር ወልቂጤ ከተማን ከድሬዳዋ ከተማ ያገናኘው ጨዋታ አንድ አቻ በሆነ ውጤት መጠናቀቁ ይታወሳል። ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኋላ ደግሞ ድሬዳዋ ከተማዎች ቅሬታ አለን በማለት ለሊጉ የበላይ አካል አክስዮን ማኀበር ደብዳቤ ማስገባታቸውን አውቀናል።

እንደ ክለቡ ገለፃ ከሆነ የቅሬታው መነሻ የተሰጠባቸውን የፍፁም ቅጣት ምት በመንተራስ እንደሆነና በጨዋታው ዝናብ ከመዝነቡ ጋር ተያይዞ ሜዳው እርጥበታማ ስለሆነ ሁለቱም ተጫዋቾች ተንሸራተው የወደቁ በመሆናቸው የተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት ያለአግባብ የተሰጠ በመሆኑ ቡድናችን አንድ አቻ እንዲወጣ ተገዷል ካሉ በኋላ የውድድር ስነ ሥርዓት ኮሚቴ የጨዋታውን ሁኔታ መርምሮ የእርምት እርምጃ ይስጠን ብለዋል። የተሰጠው ፍፁም ቅጣት ምት ፍትሐዊ አይደለም በማለት ቅሬታ ያቀረበው አንበሉ ዳንኤል ደምሱ የተመለከተው የቢጫ ማስጠንቀቂያም እንዲነሳልን እንጠይቃለን በማለት በደብዳቤያቸው ጥያቄ አቅርበዋል።