በ20ኛ የጨዋታ ሳምንት የተመለከትናቸው ዓበይት ክለብ ነክ ጉዳዮች የመጀመሪያው ፅሁፋችን አካል ናቸው።
👉 ተፈትኖም ቢሆን ያሸነፈው ቅዱስ ጊዮርጊስ
በጨዋታ ሳምንቱ በሰንጠረዡ አናት ለሚደረገው ፉክክር ትልቅ ትርጉም የነበረው እና በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲዳማ ቡናን በጋቶች ፖኖም ብቸኛ ግብ በማሸነፍ ወሳኝ ድልን አስመዝግቧል።
ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ ጥሩ መሻሻል ላይ የሚገኘው ሲዳማ ቡና በ33 ነጥቦች ከመሪው ቅዱስ ጊዮርጊስ በ8 ነጥቦች ርቆ ሦስተኛ ደረጃ ላይ እንደመገኘቱ በመሸናነፍ ውስጥ የሚኖረው ትርጉም የነጥብ ልዩነቱን ወደ 5 ማጥበብ አልያም ወደ 11 ማሳደግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጨዋታው ከፍ ያለ ግምትን ያገኘ ነበር።
በጨዋታው ምናልባት ቅዱስ ጊዮርጊስ በዘንድሮ የውድድር ዘመን በተለይ ዘሪሁን ሸንገታ ወደ ኃላፊነት ከመጣ በኋላ ካደረጓቸው ጨዋታዎች በተጋጣሚ ብልጫ የተወሰደበት ጨዋታ ነው ብለን ማንሳት እንችላለን። በሁለቱም አጋማሾች ሲዳማ ቡናዎች አንፃራዊ የበላይነት በነበራቸው ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊሶች በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ይበልጥ በጥልቀት ወደ ሳጥናቸው እንዲሳቡ ተገደው አመዛኙን ደቂቃ በጥንቃቄ ሲከላከሉ አስተውለናል።
ነገር ግን ምስጋና ቡድኑ በመጀመሪያው አጋማሽ እንተለመደው ከቆመ ኳስ መነሻዋን ካደረገች ኳስ ጋቶች ፖኖም ባስቆጠራት ግብ አሸንፈው መውጣት ችለዋል። ለዋንጫ የሚጫወት ቡድን ሁሌም ተጋጣሚውን በልጦ ያሸንፋል ማለት ባይቻልም የዋንጫ ቡድኖች ጥሩ ባልሆኑባቸው እና ብልጫ በተወሰደባቸው ጨዋታዎችም ጭምር አስፈላጊውን ሦስት ነጥብ ይዘው ሲወጡ እንመለከታለን ታድያ የሲዳማ ቡናው ጨዋታ የቅዱስ ጊዮርጊስ ይህኛውን ጥንካሬ ያሳየን ጨዋታ ነበር።
አሁንም ያለመሸነፍ ግርጋሴውን ያስቀጠለው ቡድኑ ከተፎካካሪዎቹ ሲዳማ ቡና በ11 ከወላይታ ድቻ እና ሀዋሳ ከተማ ደግሞ በ10 ነጥብ ርቆ ሊጉን መምራቱን ቀጥሏል።
👉 ከ561 የጨዋታ ደቂቃዎች በኋላ የተገኘችው የመከላከያ ግብ
ለተጋጣሚዎቹ ከልክ ያለፈ ክብር ይሰጣል በሚል ወቀሳ የሚቀርብበት መከላከያ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ግብ አስቆጥረዋል።
ከባህር ዳሩ ጨዋታ አስቀድሞ ለመጨረሻ ጊዜ ለመጨረሻ ጊዜ ግብ ያስቆጠሩት በ14ኛ የጨዋታ ሳምንት ድሬዳዋ ላይ በሀዋሳ ከተማ 3-2 ሲረቱ ሰመረ ሃፍታይ በ47ኛው ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ ስትሆን ቡድኑ በቀጣዮቹ አምስት ጨዋታዎች ግብ ሳያስቆጥር የቀረ ሲሆን የአዲሱ አቱላ ግብ ከ561 የጨዋታ ደቂቃዎች በኋላ የተገኘች ግብ ናት።
በመሰረታዊነት የተጋጣሚው ደረጃ ምን ሆነ ምን ላለመሸነፍ ቅድሚያ የሰጠው የጨዋታ ዕቅዱ በማጥቃቱ ረገድ በምን ያህል ቡድኑን እየገደቡት እንደሚገኝ ለመመልክት ግብ ማስቆጠር ባልቻላቸው አምስት ጨዋታዎች ያደረጋቸው ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ቁጥር በድምሩ አራት የመሆናቸው ነገር ስለ ቡድኑ የማጥቃት ፍላጎት አለፍ ሲልም አፈፃፀም ጠቋሚ ነው።
ታድያ የሚያስገርመው ነገር ከእነዚህ አምስት ጨዋታዎች ውስጥ በሁለቱ ማለትም ከአርባምንጭ እና አዲስ አበባ ከተማ ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች ምንም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ያለመቻላቸው ጉዳይ ትኩረት የሚስብ ነው።
በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ታድያ ቡድኑ ከባህር ዳር ከተማ ጋር አንድ አቻ ሲለያይ በተሻለ የማጥቃት ፍላጎት የተጫወተውን መከላከያን ተመልክተናል ፤ ቁጥሮችም ይህን ይመሰክራሉ። በ14ኛ የጨዋታ ሳምንት በሀዋሳ 3-2 በተረቱበት ጨዋታ 6 ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ማስመዝገብ የቻለው መከላከያ በባህር ዳሩ ጨዋታ ደግሞ 7 ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን አድርጓል።
ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ከዚህ መነሻነት ጥያቄ የቀረበላቸው አሰልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ ተከታዩን ብለዋል ፤
“ዛሬ በብዛት አጥቅተን እንጫወታለን ብለን ነበር ያሰብነው። ያው ሙከራዎችን ከሌላው ጊዜ በተሻሉ ማድረግ ችለናል። በተለይ ከዕረፍት በኋላ ግን መስጠት የማይገባንን ፍፁም ቅጣት ምት ሰጥተን ዋጋ ከፍለናል። ከዚህ በተረፈ ግን ማጥቃት በፈለግነው መጠን ከሌሎቹ ጊዜ በተሻለ ዛሬ አጥቅተናል። ብዙ ዕድሎች ፈጥረናል። ከዕረፍት በፊትም ዕድሎች አግኝተናል። አሁን ደግሞ መጨረስ የሚለው ላይ መሄድ አለብን።” ሲሉ ተደምጠዋል።
ከከፍተኛ ሊግ እንዳደገ ቡድኑ አለመሸነፍ በራሱ በሊጉ ለመቆየት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ትልቅ ድርሻ እንዳለው ቢጠበቅም የመከላከያ አቀራረብ ግን ይህን እሳቤ ያለ ልክ ወደ አንድ ፅንፍ የወሰደና የቡድኑን ሁሉንተናዊ የጨዋታ መንገድ የገደበ ሆኖ ስንመለከት ብንቆይም ሀስቡን ለማጥቃት ክፍት አድርጎ መታየት መጀመሩ ይበል የሚያሰኝ ሆኖ አግኝተነዋል።
👉 ባህር ዳር ከተማ አሁንም ማሸነፍ ተስኖታል
የሊጉ 2/3 በተገባደደበት በዚህ ወቅት በሰንጠረዡ አናት በሚደረገው ፉክክር የተጠበቀው ባህር ዳር ከተማ በሊጉ ወገብ ላይ ለመዳከር ተገዷል።
የወልቂጤ ከተማ የፎርፌ ውጤት ሳይጨምር ቡድኑ በጨዋታ ተጋጣሚን ካሸነፈ ስምንት ጨዋታዎች ተቆጥረዋል። በጥቅሉ አምስት ጨዋታዎችን ከመጨረሻ ድሉ በኋላ አቻ የተለያየው ቡድኑ በአራቱ አንድ ለአንድ ተለያይቷል። ታድያ ከእነዚህ ጨዋታዎች ውስጥ በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከመከላከያ ጋር አቻ የተለያዩበትን ጨዋታ ጨምሮ በሦስቱ አስቀድመው ግብ ቢያስቆጥሩም የኋላ ኋላ በተቆጠሩባቸው ግቦች አቻ ተለያይተዋል። ይህ ሂደት በኋላ ላይ ፎርፌ ቢያገኙበትም ከወልቂጤ ጋር ሁለት አቻ በተለያዩበት ጨዋታም የተመለከትነው እውነታ ነው።
በተለይም ቡድኑ ግቦችን ካስቆጠረ በኋላ የሚያደርጋቸው የተጫዋቾች ለውጥ አውንታዊ ሆኑ አሉታዊ ቡድን እንደ ቡድን ማጥቃቱን በማስቀጠል ተጨማሪ ግብ ከማስቆጠር ይልቅ እንደ ቡድን ወደ ኋላ ተስበው በጥንቃቄ ለመጫወት የሚያደርጉት ጥረት በስተመጨረሻም ዋጋ ሲያስከፍላቸው ተመልክተናል።
አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ በመጨረሻው ደቂቃ ስለሚቆጠርባቸው ግቦች ምክንያት ሲጠየቁ ማጥቃቶችን ማስቀጠል ያለመቻላቸው እንዲሁም በመከላከል ወቅት ያሉባቸውን የትኩረት ችግሮች በምክንያትነት አቅርበዋል።
በሌላ ጎኑ ምንም እንኳን ሙሉ ሦስት ነጥብ ለመያዝ ይቸገር እንጂ ቡድኑ ሜዳ ላይ የሚያሳየው እንቅስቃሴ መጥፎ የሚባል አይደለም። ኳሱን ለመቆጣጠር ጥረት የሚያደርገው ባህር ዳር በስብስቡ እንዳሉት የማጥቃት ባህሪ ያላቸው አማካዮች በመጨረሻው የማጥቃት ሲሶ ያለው አፈፃፀም ጥሩ የሚባል አለመሆኑ እንጂ የተሻለ ነጥቦችን ማስመዝገብ በቻለ ነበር።
የጣና ሞገዶቹ ከቀጣዩ የጨዋታ ሳምንት አንስቶ ውድድሩ ወደ መቀመጫ ከተማቸው ማምራቱን ተከትሎ የመጨረሻውን የባህር ዳር ቆይታ በሁለት ስሜት ውስጥ ሆነው የሚያደርጉት ይሆናል። አንደኛው ከዚህ ውጤት አልባ ጉዞ ተላቀው በደጋፊዎቻቸው እየታገዙ የውድድር ዘመናቸውን ዳግም ወደ መስመር ያስገቡ ይሆን አልያም ደግሞ ብዙ በመቀመጫ ከተማዎች ውድድርን ያደረጉ ቡድኖች እንደሚያጋጥማቸው ባለው ከፍተኛ ጥበቃ ውስጥ ይፈተኑ ይሆን የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።
ሙሉ ሦስት ነጥብ እያሰሰ የሚገኘው ባህር ዳር በቀጣይ ሁለት የጨዋታ ሳምንት ፍፁም ተቃራኒ በሆነ በአውንታዊ እና አሉታዊ መንገድ የሚጫወቱትን ጅማ አባ ጅፋርን እና ወላይታ ድቻን ይገጥማል።
👉 የወራጅነት ስጋት የተደቀነባቸው ቡድኖች
ከሳምንታት በፊት በተጠናቀቀው የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ፣ ለገጣፎ ለገዳዲ እና ኢትዮጵያ መድን በቀጣይ ዓመት የሊጉ ተሳትፏቸውን አረጋግጠዋል። ታድያ ለእነዚህ ክለቦች ቦታቸውን የሚለቁት ክለቦች ጉዳይ ግን ትኩረት የሚስብ ነው።
ከ20ኛ የጨዋታ ሳምንት መጠናቀቅ በኋላ ባለው የደረጃ ሰንጠረዥ ሰበታ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር በእኩል 13 ነጥቦች በሊጉ 15ኛ እና 16ኛ ደረጃ ላይ ሲገኙ አዲስ አበባ ከተማ ደግሞ በ20 ነጥብ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።
አሁን ባለው ሁኔታ ሰበታ ከተማ እና ጅማ አባ ጅፋር ላለመውረድ በሚደረገው ትግል ከአናታቸው ከሚገኙት ክለቦች በተወሰነ መልኩ የራቁ ቢመስሉም 30 ነጥቦች ገና በሚቀሩት ውድድር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት በሂሳባዊ ስሌት ብዙም ሩቅ የሚባል ግን አይደለም።
በአንፃሩ አዲስ አበባ ከተማዎች ደግሞ በሰንጠረዡ አሁናዊ ሁኔታ የሌሎች ቡድኖችን ውጤት ወደ ጎን ትተን የአንድ ጨዋታ ድል ወደ 12ኛ ደረጃ ሊያመጣቸው የሚችል ሲሆን የሁለት ጨዋታ ድል ደግሞ እስከ 8ኛ ደረጃ ያለውን ቦታ እንዲቆናጠጡ ያስችላቸዋል።
በወራጅ ቀጠና ቀጥተኛ ስጋት የተደቀነባቸው ሦስቱም ቡድኖች የሚያመሳስላቸው ነገር ቢኖር ሁሉም ሜዳ ላይ ያላቸው እንቅስቃሴ አስከፊ ያለመሆኑ ጉዳይ ነው። ተጋጣሚ ላይ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን የመውሰድ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖቹ ይህን የኳስ ቁጥጥር አደጋ ለመፍጠር በሚያስችል ሁናቴ የጠሩ የግብ አጋጣሚዎችን ለመፍጠር የመጠቀም እንዲሁም በመከላከሉ ወቅት የሚሰሯቸው ቀላል የሚመስሉ ነገር ግን ከፍተኛ ዋጋ የሚያስከፍሉ ስህተቶችን መቀነስ ቢችሉ ኖሮ እንዳላቸው የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ በሰንጠረዡ ወገብ መገኘት በተገባቸው ነበር።
በመሆኑም የውድድር ዘመኑ መቋጫ እየተቃረበ እንደመሆኑ በውድድር ዘመኑ መጨረሻ ላይ በሊጉ የሚያቆያቸው ያስመዘገቡት ውጤት እንጂ በእንቅስቃሴ ጥሩ የመሆናቸው ጉዳይ አለመሆኑን ተገንዝበው በቀሩት ጨዋታዎች በሊጉ ለመሰንበት የሞት ሽረት ትግል ማድረግ ይጠበቅባቸዋል።
👉 የተፎካካሪዎቹ ጉዳይ
ቅዱስ ጊዮርጊስ በ44 ነጥብ ከተከታዮቹ በአስር ነጥብ ርቆ እየመራው በሚገኘው የሊግ ውድድር ተፎካካሪዎቹ ቡድኖች ጫና ለማሳደር እየተቸገሩ ይገኛል።
በዋንጫ ፉክክር ውስጥ በአሁኑ ሰዓት በሊጉ ከአንድ እስከ አምስተኛ ደረጃ የሚገኙት ቡድኖች በሁለተኛው ዙር ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች የሰበሰቡት ነጥብ ስለተፎካካሪነታቸው አንዳች ነገር ይጠቁመናል።
በዚህ ሂደት ቅዱስ ጊዮርጊስ ማግኘት ከሚገባው አስራ አምስት ነጥቦች ውስጥ አስራ ሦስቱን ማሳካት ሲችል በተከታይነት የተሻለ ነጥብ ማሳካት የቻሉት ፋሲል ከነማ እና ሲዳማ ቡና ስምንት ነጥብ አስመዝግበዋል። ሀዋሳ ከተማ በሰባት ወላይታ ድቻ ደግሞ ስድስት ነጥቦችን ብቻ ማሳካት ችለዋል።
እነዚህን ጨዋታዎች ብቻ ነጥለን ከተመለከትን እንኳን የተቀሩት ተፎካካሪ ቡድኖች እንዴት ከመሪው ቡድን ጋር እየተነጠሉ እንደመጡ ማሳያ ነው። እርግጥ በሁለተኛው ዙር ቀላል የሚባል ጨዋታ ባይኖርም ቅዱስ ጊዮርጊስን እየተፎካከሩ የሚገኙት ቡድኖች በዚህን ያህል መጠን ነጥብ የጣሉባቸው ጨዋታዎች በንፅፅር ማሸነፍ ከሚችሏቸው ተጋጣሚዎች ጋር በተደረጉ ጨዋታዎች የመሆኑ ጉዳይ ሌላው ልብ ሊባል የሚገባ ጉዳይ ነው።
በመሆኑም መፎካከር በራሱ የሚፈልገው የተለየ የአዕምሮ ዝግጁነት እንዳለ የሚታመን ሲሆን በፉክክር ውስጥ በሚገኙት አንዳንድ ክለቦች ውስጥ ይህ ለመፎካከር የሚበያበቃ የአዕምሮ ዝግጁነት መኖሩ አጠያያቂ ነው።
ከጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ከአንዳንድ የተፎካካሪ ቡድኖች አሰልጣኞች አስተያየት መረዳት እንደምንችለው አሁን ላይ ከዋንጫው ፉክክር ይልቅ ሁለተኝነት ስለማለም የጀመሩ ክለቦች መኖራቸው በራሱ ስለተፎካካሪ ቡድኖች የፉክክር ደረጃ ምስል ይሰጠናል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ከዋንጫው ፉክክር ባለፈ ካለው የክለቦች የነጥብ መቀራረብ አንፃር ሁለተኛው የአፍሪካ ተሳትፎ ትኬትን ለሚያስገኘው የሁለተኝነት ደረጃ የሚደረገው ፉክክር ግን ከወዲሁ ትኩረት የሚስብ ነው።