ትናንት በተገባደደው የ20ኛ ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር አንድ አቻ የተለያየው መከላከያ ለአክሲዮን ማኅበሩ ቅሬታውን አሰምቷል።
የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ውድድር በአዳማ ከተማ እየተከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል። የአቻ ውጤት በበዙበት የ20ኛ ሳምንት ከባህር ዳር ከተማ ጋር ነጥብ የተጋራው መከላከያ በጨዋታው ተፈፅመዋል ባላቸው ሁለት ጉዳዮች ላይ ለኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር የቅሬታ ደብዳቤ ማስገባቱን አውቀናል።
የመጀመሪያው ቅሬታ ያስነሳው ጉዳይ ‘በጨዋታው 72ኛው ደቂቃ ላይ በተገኘው የመዓዘን ምት ኢብራሒም ሁሴን እና አሚን ነስሩ ላይ ፍፁም ቅጣት ምት የሚያሰጥ ጥፋት ተሰርቶባቸው ዋናው እና ረዳት ዳኞቹ በዝምታ ማለፋቸው የጨዋታው ውጤት እንዲቀየር አድርጎታል የሚል እምነት አለን።’ የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ‘ጨዋታው ሊጠናቀቅ ባለበት ሰዓት (92ኛው ደቂቃ) በቅጣት ምት ምክንያት በቆመበት ወቅት ምንም አይነት እንቅስቃሴ ሳይኖር የባህር ዳሩ አጥቂ ኦሴ ማውሊ የተከላካዩ ኢብራሒም ሁሴን የእግር ኳስ ህይወቱን እንዲጨርስ የሚያደርግ ምት በቆመበት ከፍተኛ ሀይል በተቀላቀለበት እግሩ ላይ የመርገጥ ሥራ ሲሰራ የመሐል ዳኛው እና ረዳት ዳኛው በዝምታ ያለፉ ከመሆኑ በተጨማሪ አሁንም በግልፅ በቪዲዮ ምስሉ ላይ እንደታየው ይሄው ተጫዋች ጨዋታው ካለቀ በኋላ የኢብራሒምን አንገት እንዳነቀው ያሳያል’ በማለት ቅሬታ ካቀረቡ በኋላ ከዚህ ቀደም በቪዲዮ ምልከታ ውሳኔ በተላለፈባቸው ክስተቶች ላይ እርምጃ እንደተወሰደ በማስታወስ ይሄም ሂደት እርምጃ እንዲሰጥበት በደብዳቤ ጠይቀዋል።