የቤትኪንግ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፫) – አሰልጣኞች ትኩረት

በጨዋታ ሳምንቱ በአሰልጣኞች ዙርያ የተዛብናቸውን ሀሳቦች በሦስተኛው ፅሁፋችን ተካተዋል።

👉 ኃላፊነት ለመውሰድ ዝግጁ የሆኑት አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ

በጨዋታ ሳምንቱ የመጀመሪያ በነበረው ጨዋታ ጅማ አባ ጅፋር ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ተጋርተው ወጥተዋል። ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ ሀሳቸውን ለሱፐር ስፖርት የሰጡት የጅማው አለቃ አሸናፊ በቀለ ባልተለመደ መልኩ ከተጫዋች ቅያሬ በተያያዘ የሰሩትን ስህተት አምነው ለነጥብ መጋራታቸው ራሳቸውን ተጠያቂ የሚያደርግ ሀሳብ ሲሰጡ አድምጠናል።

ስለቅያሬዎቻቸወሰ የጠየቁት አሰልጣኝ አሸናፊ ሲመልሱ “መጀመሪያ የቀየርኩት አቀያየር ላይ በተለይ መሀል ላይ በነበረው ክፍተት የሰራሁት ሥራ ራሴንም ይቆጨኛል። ከአንዴም ሁለቴ ልማር ያልቻልኩበት ስለሆነ ይሄ ጥፋት የእኔ ነው። ያንን ባስተካክል ኖሮ ምንአልባት ውጤቱ ይቀየር ነበር ብዬ አስባለሁ።”

“አንዳንዴ አሰልጣኝ የራሱን ስህተት አይቀበልም እንጂ የእኔም ጥፋት ነበር። መቀየር የሌለበትን ሰው ቀይሬ ይጠቅማል ብዬ ያሰብኩት ሰው ባግባቡ ስላልጠቀመኝ ያ ክፍተት በእኔ በኩል ነበር።”

በጨዋታው በጅማ አባ ጅፋር በኩል በድምሩ አራት ለውጦች በጨዋታው ሂደት የተደረጉ ሲሆን በተለይም ደግሞ አሰልጣኙም ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ እንዳመኑት በ58ኛው ደቂቃ ላይ አስጨናቂ ፀጋዬ አስወጥተው በምትኩ ዳዊት እስጢፋኖስን የተኩበት ቅያሬ የታለመለትን አላማ ማሳከት ይቅር እና ቡድኑን ለአደጋ አጋልጦት እንደነበር ተመልክተናል።

ድል ሲገኝ ለመሞገስ መሽቀዳደም በአንፃሩ ደግሞ ውጤቶች በሚፈለገው መልኩ ሳይሄዱ ሲቀር ጣት መቀሳሰር በተለመደበት ሊጋችን አሰልጣኞች በዚህ ደረጃ ደፋር ብለው ስለሰሯቸውን ስህተቶች ኃላፊነት መውሰድ የተለመደ ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ የአሸናፊ በቀለ ድርጊት አድናቆት የሚገባው ነው። ይሁን እንጂ ትናንት በተሰማው ዜና በወራጅ ቀጠና ውስጥ የሚገኘው ክለቡ ከውጤት ማጣቱ እና ሌሎች ጉዳዮች መነሻነት አሰልጣኙን ከሥራ ማገዱን መዘገባችን ይታወሳል።

👉 ግብ ጠባቂዎችን ማፈራረቅ

አንድ ቡድን ከ20 የሚልቁ ተጫዋቾችን በስብስቡ እንደመያዙ የተለያዩ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት ተጫዋቾች እያፈራረቁ መጠቀም የተለመደ አካሄድ ነው።

ታድያ ይህ ሂደት በተለይ በሜዳ ላይ ተጫዋቾች ላይ የተለመደ ሲሆን በግብ ጠባቂዎች ረገድ እንደ እኛ ሀገር ከሊጉ በተጓዳኝ የሚደረጉ ውድድሮች በሌሉበት ሁኔታ ግን ግብ ጠባቂዎችን ማፈራረቅ እምብዛም የተለመደ አይደለም።

ለዚህም ይመስላል በየክለቦቹ ብዙ ደቂቃ የተጫወቱ ተጫዋቾችን ዝርዝር ብንመለከት ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚመደቡ ተጫዋቾች ውስጥ ግብ ጠባቂዎች ይገኙበታል። ወልቂጤ ከተማ ግን ከዚህ ሂደት ባፈነገጠ መልኩ ከሁለተኛው ዙር አንስቶ ግብ ጠባቂዎችን የማፈራረቅ አዝማሚያ እየተመለከትን እንገኛለን።

የውድድር ዘመኑን በአይቮሪኮስታዊው ሲሊቪያን ግቦሆ የጀመሩት ወልቂጤ ከተማዎች ተጫዋቹን ከ8ኛው የጨዋታ ሳምንት አንስቶ መጠቀም ያለመቻላቸውን ተከትሎ እሱን ተክቶ በክረምቱ ቡድኑን የተቀላቀለው ሰዒድ ሀብታሙ የቡድኑን ግብ በቋሚነት ሲጠብቅ ቆይቷል።

በአጋማሹ የዝውውር መስኮት በሲልቪያን ምትክ ሌላ ግብ ጠባቂ ፍለጋን ወደ ገበያ የወጡት ወልቂጤ ከተማዎች የቀድሞውን የቅዱስ ጊዮርጊስ እና አዳማ ከተማ የግብ ዘብ የነበረውን ሮበርት ኦዶንካራን ማስፈረማቸው አይዘነጋም።

ታድያ በግብ ጠባቂ ስፍራ ላይ የፉክክር መንፈስ በመፍጠር የሻለውን ግብ ጠባቂ የማሰለፍ ፍላጎት እንዳላቸው ሲናገሩ የተደመጡት አሰልጣኝ ተመስገን ዳና በሁለተኛው ዙር ከፋሲል እና አዳማ ከተማ ጋር በነበሩት ጨዋታዎች ተጠባባቂ በመሆን የወልቂጤ ቆይታውን የጀመረውን ሮበርት ኦዶንካራን ከባህር ዳር ከተማ ጋር 2-2 (በኋላ በፎርሬ 3-0 በተሸነፉበት) እንዲሁም በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት ከድሬዳዋ ጋር አቻ ሲለያዩ ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን ሰዒድ ሀብታሙም እንዲሁ በባለፈው የጨዋታ ሳምንት በሀዋሳ ከተማ ሲረቱ ተሰልፎ ተጫውቷል።

የአሰልጣኝ ተመስገን ይህ ውሳኔ የሚፈለገውን የፉክክር መንፈስ በመፍጠር ቡድኑን ተጠቃሚ ያደርገዋል ወይንስ ከተጠበቀው በተቃራኒ አለመረጋጋትን በመፍጠር ቡድኑ ላይ አደጋን ይደቅን ይሆን የሚለው ጉዳይ ይጠበቃል።

👉 ዳኝነቱን የተቸው አሠልጣኝ

የጨዋታ አመራሮች ሆነ ዳኞችን ለሽንፈት ተጠያቂ ማድረግ በእግርኳሳችን ጥቂት ዓመታትን ወደ ኋላ ብንጓዝ እጅጉን የተለመደ ምግባር ነበር።

ነገርግን በተለይ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት መጀመሩን ተከትሎ አሰልጣኞች ይበልጥ ስለ ንግግራቸው መጨነቅ መጀመራቸው እና መሰል አስተያየቶችን በመስጠታቸው ሊደርስባቸው የሚችለውን ውግዘት በመፍራት በዳኝነቱ ደስተኛ ባይሆኑም ስሜታቸውን ውጠው አጋጣሚዎቹን ለማሳለፍ ሲጥሩ እንመለከታለን።

በዚህም ዳኝነቱን በተመለከተ ለሚቀርብላቸው ጥያቄ “ዳኝነቱን በተመለከተ የሚመለከተው አካል አለ……” የሚል ሀሳብን ደጋግመው ሲሰጡ መደመጥ ጀምራል። ነገርግን በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት በሀዲያ ሆሳዕና ሽንፈት ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ አሰልጣኝ የሆኑት ዘርዓይ ሙሉ በከፍተኛ ምሬት ሀሳብ ሲሰጡ አድምጠናል።

“እኔ ዳኝነት ላይ ቅሬታ አለኝ፡፡ ምክንያቱም መጫወት አልቻልንም ተቃራኒ ቡድን በአጠቃላይ እያንዳንዱ እንቅስቃሴ ከኳስ ውጪ የሚደረጉ ንክኪዎች የእኛን ተጫዋቾች ከእንቅስቃሴ ውጪ ነው ያደረጋቸው፡፡ ይሄንን እንዴት ዝም እንዳለ አላውቅም ከእዛ ውጪ የእኛዎቹ አግሬሲቭ ሆነው ሲሄዱ ደግሞ በተቃራኒው ውሳኔ ሲሰጥ ነው የማየው ተናግሬ ባለውቅም ዛሬ መናገር ስላለብኝ እናገራለሁ፡፡ የጨዋታውን እንቅስቃሴ በአጠቃላይ የቀየረው ዳኝነቱ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ዳኝነት ሊኖርም አይገባም የምንጫወተው ለውጤት ነው፡፡ ስለዚህ የተጫዋቾቼን እንቅስቃሴ በአጠቃላይ ያበላሸብን ዳኝነት ነው ብዬ የማምነው፡፡ የቱም ጋር ስህተት ልንሰራ እንችላለን በተለይ ወደ ፊት ስንሄድ መጫወት አልቻልንም በተቃራኒው ውሳኔው ለተቃራኒ ቡድን የሚደረግ ከሆነ ስሜት ይጎዳል፡፡ ስሜታዊ አድርጓል ተጫዋቾቻችንን፡፡” የሚልን ሀሳብ ስለ ሽንፈታቸው መንስኤ በተጠየቁበት ወቅት አንስተዋል።