በወራጅ ቀጠናው የሚገኘው ሰበታ ከተማ በምክትል አሠልጣኝነት እና የቴክኒክ አማካሪ ሀላፊነት የቀድሞ አሠልጣኙን ሾሟል።
በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ የደረጃ ሰንጠረዥ 16ኛ ቦታይ ይዞ የሚገኘው ሰበታ ከተማ ከወራት በፊት ዋና አሠልጣኙ ዘላለም ሽፈራውን ካገደ በኋላ የቀድሞ ምክትል አሠልጣኙ ብርሃን ደበሌን በጊዜያዊ አሠልጣኝነት ኃላፊነት በመሾም ውድድሩን እያከናወነ እንደሚገኝ ይታወቃል። አሠልጣኝ ብርሃን ደበሌም ያለ ረዳት አሠልጣኝ 7 ጨዋታዎችን ከመሩ በኋላ በዛሬው ዕለት ረዳት ማግኘታቸውን ሶከር ኢትዮጵያ ከክለቡ ሥራ-አስኪያጅ አቶ አለማየሁ ምንዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።
እስከ ውድድር ዓመቱ መጨረሻ ረዳት አሠልጣኝ ሆነው የተሾሙት በ2001 ክለቡን ወደ ፕሪምየር ሊግ ያሳደጉት አሠልጣኝ ደረጄ በላይ ናቸው። የቀድሞ የምድር ጦር ተጫዋች የነበሩት አሠልጣኝ ደረጄ ከሰበታ በተጨማሪ ጅማ አባ ቡና እና ወልቂጤ ከተማንም ወደ ፕሪምየር ሊጉ ማሳደጋቸው አይዘነጋም። ሰበታ ከተማ በቀጣይ ዓመት በሊጉ እንዲዘልቅ የማድረግ ሀላፊነትም ከአሠልጣኝ ብርሃን ደበሌ ጋር በመሆን ተሰጥቷቸው ወደ ስራ ገብተዋል።
አሠልጣኝ ደረጄ ከምክትል አሠልጣኝነት በተጨማሪ የቴክኒክ አማካሪነት ሀላፊነት እንደተሰጣቸውም ለማወቅ ተችሏል። አሠልጣኝ ብርሃን እና ደረጄ በተመሳሳይ የምክትል አሠልጣኝነት እርከን ሀላፊነት ቢቀጥሉም እንደ ጊዜያዊ ዋና አሠልጣኝ ብርሃን እንደሚቀጥሉ እና የዋና አሠልጣኝነት ጉዳይ እስካሁን እንዳልታወቀ ተነግሮናል።