በአዳማ ከተማ የሚደረገው የመጨረሻ ሳምንት የሊጉ መርሐ-ግብሮች የመክፈቻ ፍልሚያ እንደሚከተለው ተዳሷል።
ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ሦስቱንም የጨዋታ ውጤት ያገኘው ባህር ዳር ከተማ (ድሉ በፎርፌ ውጤት የተገኘ ነው) ወደ መቀመጫ ከተማው በቀጣይ ሲያመራ ጥሩ ስንቅ ለመያዝ እና ከግልባጩ የደረጃ ሰንጠረዥ ወደ ፊተኛው ለመጓዝ ጠንክሮ እንደሚጫወት ይጠበቃል። በተቃራኒው በወራጅ ቀጠናው እየዳከረ የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ የናፈቀውን ድል አግኝቶ ከወራጅ ቀጠናው ለመራቅ የሚያደርገውን ሩጫ ለማፋጠን ተግቶ እንደሚንቀሳቀስ ይታመናል።
ካለው የተጫዋች ስብስብ እና የአሠልጣኝ ጥራት አንፃር አሁን ካስመዘገበው ውጤት በላይ የሚጠበቅበት ባህር ዳር ከተማ በወጥነት ወጥ ያልሆነ ቡድን መሆኑን ቀጥሎበታል። ባሳለፍነው ሳምንትም የመውረድ ስጋት ካለበት መከላከያ ጋር ተጫውቶ መጠነኛ ብልጫ ተወስዶበት አቻ ተለያይቷል። በተለይ ቡድኑ በ59ኛው ደቂቃ በፍፁም ቅጣት ምት መሪ ከሆነ በኋላ ጨዋታውን ለመቆጣጠር የጣረበት መንገድ በከፍተኛ ተነሳሽነት ሲጫወቱ ለነበሩት መከላከያዎች እጅግ የተመቸ ነበር። በዚህም ከመስመር በሚነሱ ኳሶች ጥቃቶች በርክተውበት ጫና ውስጥ ገብቶ ነበር። እንዳልነው ጨዋታን የመቆጣጠር (Game management) ክፍተት መታረም የሚገባው ሲሆን በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ግን የታየው የማጥቃት እንቅስቃሴ መልካም ነበር። በነገው ጨዋታም ቡድኑ ሌላ የመውረድ ስጋት ያለበት ክለብ እንደመግጠሙ ጫናዎችን ተቆጣጥሮ በተጋጣሚ ተጫዋቾች ጀርባ (ጅማ ጨዋታዎችን ለማሸነፍ ነቅሎ ይወጣል ተብሎ ስለሚጠበቅ) የሚገኘውን ቦታ በመጠቀም ጨዋታዎችን ለመወሰን ያለበትን ውስንንት አስተካክሎ ከቀረበ ፍሬያማ ሊሆን ይችላል።
ዋና አሠልጣኙ አሸናፊ በቀለን አግዶ በምክትል አሠልጣኙ የሱፍ ዓሊ እየተመራ ውድድሩን ለማገባደድ ውሳኔ ያስተላለፈው ጅማ አባ ጅፋር በበኩሉ ቀሪ 10 ጨዋታዎችን እንደ ፍፃሜ እየተመለከተ የማይቀርብ ከሆነ በቀጣዩ ዓመት በከፍተኛው የሊግ እርከን መክረሙ አጠራጣሪ ነው። በእንቅስቃሴ ደረጃ ያለፉትን ጨዋታዎች እንደ ቡድን እድገት እያሳየ የሚገኘው ጅማ በድሬዳዋው እና በፋሲሉ ጨዋታ ባለቀ ሰዓት ግብ አስተናግዶ አሳዛኝ ተሸናፊ ሆነ እንጂ ቢያንስ በጨዋታዎቹ አንድ አንድ ነጥብ ቢያገኝ ከአስጊው ቀጠና ለመውጣት የሚያደርገውን ሩጫ ያፋጥን ነበር። የሆነው ሆኖ በቡናውም ጨዋታ የተጋጣሚን አጨዋወት በማምከን እና የግብ ዕድሎችን በመፍጠር ጥሩ ነበር። በተለይ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ቡና ግብ ካስጠበቀ በኋላ ወደ ኋላ ለማፈግፈግ ያሳየውን ፍላጎት ለመጠቀም በመጣር ጫናዎችን ሲያሳድሩ ታይቷል። ኳስን በማንሸራሸርም ሆነ በቀጥተኛ አጨዋወት ሲንቀሳቀስ የሚታየው ቡድኑ ነገም በፈጣኖቹ አጥቂዎቹ ባለፉት ሰባት ጨዋታዎች (የፎርፌውን ጨምሮ) ግቦችን ላስተናገደው የባህር ዳር የኋላ መስመር ፈተና እንደሚሰጥ ይገመታል።
በሁለቱ የፍፁም ቅጣት ምት ክልሎች ችግር ያለበት ባህር ዳር ከተማ በላይኛው ሳጥን መሳሳት የሚያመጣበት ውሳኔ ትናንት ተወስኖበታል። በዚህም ኦሴ ማውሊ በመከላከያው ጨዋታ ኢብራሒም ሁሴን ላይ ከኳስ ውጪ በሰራው ጥፋት አራት ጨዋታዎችን በመታገዱ የቡድኑን የፊት መስመር ሊያዶሎዱመው ይችላል። እርግጥ ማውሊ ባይኖርም ሌሎች ቦታውን ተክተው የሚጫወቱ ተጫዋቾች ያሉ ቢሆንም እነሱ ያለባቸውን የውሳኔ አሰጣት ችግር ቀርፈው መቅረብ ይገባቸዋል። ከዚህ ውጪ ቡድኑ ላይ የሚታየው የቆመ ኳስ አጠቃቀም ችግርም በድጋሜ ዋጋ እንዳያስከፍለው ያሰጋል። ጅማ በበኩሉ እንደ አብዛኞቹ ቡድኖች የአሠልጣኝ ሽግሽግ (ለውጥ) ሲደረግ የሚኖረው ተነሳሽነት ከመጣ ጨዋታውን ወደ ራሱ ሊያመጣ ይችላል። በተለይ በፍላጎት በመጫወት ጥያቄ የሚነሳባቸው የባህር ዳር ተጫዋቾችን በልጦ መገኘት ከጨዋታው አንዳች ነገር ሊያስገኝ ይችላል። በዋናነት ደግሞ ሽግግሮችን በአግባቡ መከወን እና በቡናው ጨዋታ የታየውን የአጨራረስ ክፍተት ማስተካከል ወደ ሦስት ነጥብ ሊወስዳቸው ይችላል።
ባህር ዳር ከተማ በጉዳት የሚያጣው ተጫዋች ባይኖርም ከላይ እንደገለፅነው ጋናዊው አጥቂ ኦሴ ማውሊ ግን የአራት ጨዋታዎች ቅጣት ስለተላለፈበት ግልጋሎት አይሰጥም። ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ በቅጣት ምክንያት ሙሴ ከቤላን እንዲሁም በጉዳት ምክንያት ዳዊት እስጢፋኖስን አያገኝም።
ተፈሪ አለባቸው የጨዋታው የመሔል አልቢትር ሲሆኑ ክንፈ ይልማ እና ፋንታሁን አድማሱ ረዳት ቢኒያም ወርቅአገኘሁ ደግሞ አራተኛ ዳኛ ሆነው ጨዋታውን ይመራሉ።
እርስ በርስ ግንኙነት
– ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም 5 ጊዜ ተገናኝተው አንድ አንድ ጊዜ ሲሸናነፉ በሦስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል። በአምስቱ ግንኙነት ደግሞ ባህር ዳር 5 ጅማ 4 ጎሎችን አስቆጥረዋል።
ግምታዊ አሰላለፍ
ባህር ዳር ከተማ (4-3-3)
ፋሲል ገብረሚካኤል
መሳይ አገኘሁ – ፈቱዲን ጀማል – ሰለሞን ወዴሳ – ሔኖክ ኢሳይያስ
ፍፁም ዓለሙ – ፍቅረሚካኤል ዓለሙ – ፉዐድ ፈረጃ
ተመስገን ደረሰ – ዓሊ ሱሌይማን – ግርማ ዲሳሳ
ጅማ አባ ጅፋር (3-5-2)
አላዛር ማርቆስ
ኢያሱ ለገስ – የአብስራ ሙሉጌታ – ተስፋዬ መላኩ
እዮብ ዓለማየሁ – አድናን ረሻድ – አስጨናቂ ፀጋዬ – መስዑድ መሐመድ – ሱራፌል ዐወል
መሐመድኑር ናስር – ዳዊት ፍቃዱ