የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 20ኛ ሳምንት ዓበይት ጉዳዮች (፬) – ሌሎች ጉዳዮች

በመጨረሻው ፅሁፋችን ደግሞ ሌሎች ትኩረት የሳቡ ጉዳዮችን ተዳሰውበታል።

👉 ተቀጣጣይ ቁሶች ለድጋፍ መስጫነት…

ከሰሞኑ እየተደረጉ በሚገኙ የሊጉ ጨዋታዎች የተለያዩ ክለቦች ደጋፊዎች የቡድናቸው መገለጫ ቀለም የሆኑ ተቀጣጣይ የሆኑ እና ከውስጣቸው ጭስ የሚተፉ ቁሶችን በመጠቀም በስታዲየም ቡድናቸውን ለማበረታታት ጥቅም ላይ እየዋሉ ተመልክተናል።

በቀደመው ጊዜ ለመርከበኞች መልዕክት መለዋወጫ በመሆን ሲያገለግል የነበረው ይህ ቁስ አሁን ላይ በተለይ ከቤት ውጪ በሚደረጉ የተለያዩ ሁነቶች ላይ እንደ ማድመቅያ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።

በቀደሙት ጊዜያት በተለይ በምስራቅ አውሮፓ እንዲሁም በደቡብ አሜሪካ ሀገራት የደጋፊዎች የድጋፍ ባህል(Fan Culture) አካል ተደርገው ይወሰዱ የነበሩት እነዚህ የታመቁ ጭሶች (Flair) አሁን ግን በዓለምአቀፍ ደረጃ በተለያዩ ሀገራት ደጋፊዎች ዘንድ እየተለመዱ መጥተዋል።

ለስታዲየሞች የተለየ ድባብን የማላበሳቸው ነገር የሚያጠያይቅ ባይሆንም ከደህንነት እና ከጤና ዐውድ ግን መሰል ቁሶች በተለይ በአንዳንድ ሀገራት ስታዲየሞች ውስጥ ጥቅም የመዋላቸው ነገር ይሁንታ የተቸረው አይደለም። በሀገራችን መሰል ሂደቶችን አሁን በስፋት እያስተዋልን የሚገኝ ሲሆን በስታዲየሞች ውስጥ መሰል ቁሶችን ይዞ መገኘት ለቅጣት የሚዳርግ ሲሆን ሊጋችንም ከወዲሁ በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባዋል።

👉 አቻ የበዙበት ግቦች የጠፉበት የጨዋታ ሳምንት

አምስት አቻ ፤ 12 ግቦች በ20ኛ የጨዋታ ሳምንት የተመዘገቡ ውጤቶች ናቸው።

ከሌሎች የጨዋታ ሳምንታት አንፃር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ ግብ የተቆጠረበት የጨዋታ ሳምንቱ የማሳረጊያ ዕለት መርሐግብር በነበረው የሀዲያ ሆሳዕና እና ሀዋሳ ከተማ ጨዋታ አራት ግቦች መቆጠራቸው የግቦቹን መጠን ሁለት አሀዝ አደረሰው እንጂ ምናልባት በጨዋታ ሳምንቱ እንደተመለከትነው አዝማሚያ የውድድር ዘመኑ ዝቅተኛ ግብ የቆጠረበት በሆነ ነበር።

ሌላኛው በጨዋታ ሳምንቱ ከተደረጉ ስምንት ጨዋታዎች አምስቱ በአቻ ውጤት የተጠናቀቁበትም ነበር። ሁለት ጨዋታዎች ያለ ግብ ሲጠናቀቁ የተቀሩት ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ አንድ አቻ በሆነ ውጤት የተጠናቀቁ ጨዋታዎች ነበሩ።

👉 እግር ኳስ እና ቱሪዝም

የእግርኳስን በጎ ተፅዕኖ ለመጠቀም በሀገራችን ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ እዚህም እዚያም ጥረቶች ሲደረጉ እያስተዋልን እንገኛለን በተለይ ወድድሩ የቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት ማግኘቱን ተከትሎ ጥረቶቹ ተጠናክረው ቀጥለዋል።

በዚህ የጨዋታ ሳምንት ደግሞ ዛሬ በድምቀት እየተከበረ የሚገኘውን የ2013/14 የሲዳማ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ ክብረ በዓል የሆነው “ፊቼ ጫምበላላ”ን የሚያስተዋውቁ መልዕክቶች የክልሉ ተወካይ በሆኑት ሀዋሳ ከተማ እና ሲዳማ ቡና ተጫዋቾች ሲተዋወቁ ተመልክተናል።

በርካታ ባህሎች እና መስህቦችን የታደለችው ሀገራችን እነዚህን በማስተዋወቁ ረገድ ግን አሁንም ሰፊ ሥራዎች ይቀሩናል።

👉 ደጋፊያቸውን የዘከሩት ፋሲል ከነማዎች

ፋሲል ከነማ አርባምንጭ ከተማን በረታበት በዚህኛው የጨዋታ ሳምንት መርሃግብር የፋሲል ከነማ ደጋፊዎች በጎ ምግባርን ያስተዋልንበት ነበር።

ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ መላው የፋሲል ከነማውያን በቅርቡ ከዚህ ዓለም በድንገተኝ የተለየውን ተሾመ ለገሰን የሚዘክር መልዕክት ይዘው ወደ ሜዳ በመግባት እንዲሁም ከጨዋታው መጀመር አስቀድሞ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት እንዲደረግ በማድረግ አጋርነታቸውን አሳይተዋል።