ቅድመ ዳሰሳ | መከላከያ ከ ኢትዮጵያ ቡና

በ21ኛው ሳምንት ቀዳሚ የጨዋታ ዕለት ምሽት ላይ የሚደረገውን ጨዋታ እንዲህ ዳሰነዋል።

ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከአቻ ውጤት የመጡት መከላከያ እና ቡና ወደ ሦስት ነጥብ የሚመልሳቸውን ጨዋታ ያደርጋሉ። ከሁለቱ ውጤቱን አጥብቆ የሚያፈልገው መከላከያ ከወራጅ ቀጠናው በአንድ ነጥብ ብቻ ከፍ ብሎ የሚገኝ ሲሆን ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ድልን ማጣጣም ከቻለ በመጠነኛ እፎይታ ወደ ባህር ዳሩ ውድድር የማምራት ዕድል ይኖረዋል። ሰባተኛ ደረጃ ላይ በተቀመጠው ኢትዮጵያ ቡና በኩልም ከመሪው ጋር የ16 ነጥብ ልዩነት ከሁለተኛው ጋር ደግሞ የስድስት ነጥብ ልዩነት ላይ እንደመገኘቱ ከማሸነፍ ያነሰ ውጤት ተቀባይነት አይኖረውም።

መከላከያ በመጨረሻው የባህር ዳሩ ጨዋታ በብዙው መልኩ ተቀይሮ አይተነዋል። ጥንቃቄ ተኮር ሆኖ የዘለቀው ቡድኑ አንዴም ኢላማውን ሳይጠብቅ ይወጣ የነበረባቸው ጨዋታዎች የቅርብ ጊዜ ትውስታ ቢሆኑም ባሳለፍነው ሳምንት አምስት ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን ከማድረጉ ባለፈ ከአምስት ጨዋታዎች በኋላም ኳስ እና መረብን ማገናኘት ችሏል። አሰልጣኝ ዮሐንስ ሣህሌ ቡድናቸው ባቀደው መልኩ አጥቅቶ መጫወቱን እና በቀጣይ ደግሞ አጨራረስ ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንዳለባቸው በማንሳት የሰጡት አስተያየት ደግሞ ሁኔታው ገጠመኝ ሳይሆን ጦሩ በተጋጣሚው የሜዳ ክፍል ላይ ደጋግሞ ለመገኘት ወደሚረዳው የጨዋታ ዕቅድ መምጣት መጀመሩን የሚጠቁም ነበር። በእርግጥም የውድድሩን ከግማሽ በላይ ከዚህ የተለየ አካሄድ ለነበረው ቡድን በቀላሉ ወደተዋጣለት የማጥቃት ትግበራ ስኬት ላይ ይደርሳል ብሎ ማሰብ ባይቻልም በነገውም ጨዋታ ያሳለፍነውን ሳምንት ብቃት አሳድጎ ለመምጣት እንደሚሞክር ይታሰባል።

በዚህም በተለይም በባህር ዳሩ ጨዋታ ሁለተኛ አጋማሽ ቡድኑ ኳስ ነጥቆ በፈጣን ቅብብሎች ወደ ግብ ለመድረስ በሚያደርገው ጥረት የተነበበት አስፈሪነት የነገ ዋነኛ ስትራቴጂው የመሆን ዕድል የኖረዋል። ከዚህ ውስጥ ከወትሮው በተለየ የማጥቃት ኃላፊነተቸው ተነቃቅቶ የታዩት የመስመር ተከላካዮች (በተለይም በቀኝ) ለኢትዮጵያ ቡና ጥቃት ክፍተቶችን ሳይሰጡ ማጥቃትን ለማገዝ የሚመርጡት አካሄድ ትኩረት ሳቢ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም በመሰል ቅፅበቶች የመጨረሻ ኳሶችን የማድረስ ብቃት ያለው እና አሁንም የቡድኑ ዋነኛ የፈጠራ ምንጭ የሆነው ቢኒያም በላይ የተሻለ ነፃነትን ሊያገኝ በሚችልባቸው የማጥቃት ሽግግሮች ወቅት ከኢትዮጵያ ቡና የወገብ በታች ተሰላፊዎች ጋር የሚገናኝባቸው አጋጣሚዎች ለጦሩ የጠሩ የግብ ዕድሎች መገኘት ቁልፍ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ቡና ከሸገር ደርቢው ሽንፈት በኋላ ተከታታይ ድሎችን በማስመዝገብ ጥሩ ማንሰራራት ችሏል። ከውጤትም ባሻገር በመሰረታዊነት በማይለወጠው የቡድኑ አጨዋወት ውስጥ ከተጋጣሚ አቀራረብ አንፃር ክፍተቶችን ለማግኘት የሚረዱ መላዎችን በመቀየስ እና በማሳካቱ ረገድ የነበረው አፈፃፀም መልካም የሚባል ሆኖ አልፎ ነበር። በጅማ አባ ጅፋሩ ጨዋታ ግን እዚህ ላይ ቡድኑ ደከም ብሎ ታይቷል። ከሁለት ዘጠና ደቂቃዎች በኋላ መረቡ የተደፈረው ቡና ጨዋታውን መምራት ችሎ የነበረ መሆኑ ይበልጥ ለቡድኑ አጨዋወት ምቹ ሁናታዎችን ፈጥሮ ነበር። ይኸውም ተጋጣሚው ውጤቱን አጥብቆ የሚፈልግ የነበረ መሆኑና ይህንንም ለማሳካት በሚያደርገው ጥረት የተሻሉ ክፍተቶችን ማግኘቱ ነበር። ሆኖም ቡና ሰሞኑን በተለይም በዊሊያም ከመስመር የሚነሳ የማጥቃት ሂደት እና ከአማካይ ክፍል መነሻውን ካደረገው የሮቤል ተክለሚካኤል ሚና ጨምሮ በሌሎች የማጥቃት አማራጮቹም ጭምር ፍሰት ያለው ፣ ተጋጣሚ የከፈታቸው ቦታዎችን ያነጣጠረ የማጥቃት ስልት በተመግበሩ በኩል ተቀዛቅዞ ታይቷል።

በነገው ጨዋታ መከላከያ ከጅማ በተሻለ የመከላከል ጥንካሬ ያለው እና እንደቡድን ወደ መከላከል በሚደረግ ሽግግር ውስጥ በቶሎ ቅርፁን በሚያግኝ ቡድን እንደመሆኑ የቡናዎች ከላይ የተነሳው እና ድል ባደረጉባቸው ሁለት ጨዋታዎች ላይ የተስተዋለው የማጥቃት ዑደት በጥሩ አፈፃፀም ላይ መገኘት የግድ ይለዋል። ለመልሶ ማጥቃት የማያጋለጡ ቅብብሎች ፣ የሜዳውን ስፋት በጥልቀት የሚጠቀሙ የመስመር ተከላካዮች እንዲሁም በትክክለኛው ሰዓት ላይ በሳጥን ውስጥ የሚገኙ አማካዮች መናበብ ለቡና እጅግ አስፈላጊው ይሆናል። ቡድኑ ከጅማው ጨዋታ የሚወስደው መልካም ነገር በብዙው ሲተች የሚሰማው አጥቂ እንዳለ ደባልቄ ወደ ግብ አስቆጣሪነት መምጣቱ ሲሆን ነገም ተጫዋቹ ጨራሽነቱን ከማስቀጠል ባለፈ በመስመሮች መካከል እየተገኘ የቡድኑን ቅብብሎች የሚያሳልጥበት አኳኋን ልዩነት ሊፈጥር ይችላል።

በጨዋታው መከላከያ ጉዳት ላይ ከሰነበተው ሰመረ ሀፍተይ በተጨማሪ ዳዊት ማሞንም በጉዳት ሲያጣ
የኢትዮጵያ ቡና ቡናዎቹ ወንድሜነህ ደረጀ ፣ አቤል እንዳለ እና የአብቃል ፈርጃም እንዲሁ በጉዳት ሳቢያ ለነገው ጨዋታ አይደርሱም። በሌላ በኩል ወሳኙ አጥቂው አቡበከር ናስር ከጉዳት መልስ በዕለቱ የጨዋታ ስብስብ ውስጥ እንደሚኖር ይጠበቃል።

ጨዋታው በማኑሄ ወልደፃዲቅ የመሀል ዳኝነት ሲከናወን ፋሲካ የኋላሸት እና ሙስጠፋ መኪ በረዳትነትን ሀብታሙ መንግሥቴ ደግሞ በአራተኛ ዳኝነት ተመድበዋል።

እርስ በእርስ ግንኙነት

– ቡድኖቹ ከዚህ ቀደም 29 ጊዜ ተገናኝተው ኢትዮጵያ ቡና 15 ሲያሸንፍ 8 ጊዜ አቻ ተለያይተው መከላከያ 6 አሸንፏል። በ29 ግንኙነቶች ቡና 42 ሲያስቆጥር መከላከያ ደግሞ 25 አስቆጥሯል።

ግምታዊ አሰላለፍ

መከላከያ (4-2-3-1)

ክሌመንት ቦዬ

ገናናው ረጋሳ – ኢብራሂም ሁሴን – ልደቱ ጌታቸው – ግሩም ሀጎስ

ኢማኑኤል ላርዬ – አሚን ነስሩ

ተሾመ በላቸው – ምንተስኖት አዳነ – ቢኒያም በላይ

ባዳራ ናቢ ሲላ

ኢትዮጵያ ቡና (4-3-3)

በረከት አማረ

ሥዩም ተስፋዬ – አበበ ጥላሁን – ቴዎድሮስ በቀለ – አስራት ቱንጆ

ሮቤል ተክለሚካኤል – አማኑኤል ዮሐንስ – ታፈሠ ሰለሞን

ሚኪያስ መኮንን – እንዳለ ደባልቄ – ዊሊያም ሰለሞን