ሪፖርት | ጅማ ከሰባት ጨዋታዎች በኋላ ባህር ዳር ከተማ ላይ ድል አግኝቷል

በወራጅ ቀጠናው የሚገኘው ጅማ አባ ጅፋር ከስድስት ጨዋታዎች በኋላ ከአንድ ጎል በላይ አስቆጥሮ የናፈቀውን ድል ባህር ዳር ከተማ ላይ ተጎናፅፏል።

ባሳለፍነው ሳምንት ከመከላከያ ጋር እንድ አቻ የተለያየው ባህር ዳር ከተማ ሁለት ነጥብ ከጣለበት ፍልሚያ አራት ተጫዋቾችን ለውጧል። በዚህም አሠልጣኝ አብርሃም መብራቱ በግርማ ዲሳሳ፣ ሳላምላክ ተገኝ፣ ኦሴ ማውሊ እና ፉዐድ ፈረጃ ምትክ መናፍ ዐወል፣ አህመድ ረሺድ፣ አብዱልከሪም ንኪማ እና ዓሊ ሱሌይማንን ወደ አሰላለፍ አስገብተዋል። ዋና አሠልጣኙ አሸናፊ በቀለን አግዶ ምክትል አሠልጣኙ የሱፍ ዓሊን በጊዜያዊነት የሾመው ጅማ አባ ጅፋር ደግሞ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ነጥብ ከተጋራበት ፍልሚያ ኢያሱ ለገሠ እና ወንድማገኝ ማርቆስን በዳዊት ፍቃዱ እንዲሁም በላይ አባይነህ ምትክ አስገብቶ ጨዋታውን ቀርቧል።

ከወትሮ በተለየ በጥሩ ተነሳሽነት መጫወት የጀመሩት ባህር ዳር ከተማዎች ገና በጅማሮ በ2ኛው ደቂቃ አለልኝ አዘነ ከአብዱልከሪም ንኪማ ከሳጥኑ ጫፍ ሆኖ ተረክቦ በሞከረው ኳስ ቀዳሚ ሊሆኑ ነበር። ከዚህ ሙከራ በኋላ የጨዋታውን የሀይል ሚዛን ወደ ራሳቸው አድርገው መንቀሳቀስ የቀጠሉት ጅማ አባ ጅፋሮች በበኩላቸው በጥሩ የኳስ ቅብብል በ8ኛው ደቂቃ በመሐመድኑር ናስር አማካኝነት ጥቃት ሰንዝረዋል። ከሦስት ደቂቃዎች በኋላም እዮብ አለማየሁ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ መሐመድኑር በግንባሩ ለመጠቀም ጥሮ የግብ ዘቡ ፋሲል ገብረሚካኤል አውጥቶበታል።

ሁለቱም ቡድኖች ሜዳውን ለጥጦ በመስመር በኩል ከማጥቃት ይልቅ መሐል ለመሐል የሚደረጉ ጥቃቶች ላይ ተጠምደው ታይተዋል። ከውሃ እረፍት በኋላ ግን በፈጣን ሽግግር ፍፁም ዓለሙ ከቀኝ መስመር መሬት ለመሬት ያሻገረውን ኳስ ኒኪማ ለመጠቀም ሲጥር ወንድማገኝ በጥሩ ሁኔታ በቦታው በመገኘት ኳሱን ወደ ውጪ አውጥቶበታል። ደቂቃ በደቂቃ ዕድገት እያሳዩ የመጡት ባህር ዳሮች ከአጋማሹ አካፋይ ሰዓት በኋላ የጅማን የግራ መስመር እንደ ዋነኛ የማጥቂያ ማዕከል በማድረግ ግቦችን ለማግኘት መታተር ይዘዋል። ጅማዎች ደግሞ የነበራቸውን የጨዋታ ቁጥጥር አተውት የባህር ዳርን ጫና መመከት ላይ ተጠምደው ተስተውሏል።

ባህር ዳር ለማጥቃት ፍላጎት ቢኖረውም በአጋማሹ አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ ማድረግ ሳይችል ቀርቷል። ቡድኑ ግን በ43ኛው ደቂቃ በዓሊ አማካኝነት ግብ ቢያስቆጥርም ተጫዋቹ ኳስ በእጁ ነክቷል በሚል ግቡ ተሽሯል። የአጋማሹ ደቂቃ ተጠናቆ ጭማሪ ሊታይ ሲል እዮብ ላይ ሔኖክ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተገኘውን የቅጣይ ምት መስዑድ ሲያሻማው አማካዩ አስጨናቂ ፀጋዬ በነፃ አቋቋም ኳሱን በግንባሩ ከመረብ ጋር አዋህዶት ጅማን መሪ አድርጓል። ከግቡ በኋላም አድናን ሌላ ሙከራ ከሳጥን ውጪ አድርጎ መክኖበታል።

ባህር ዳሮች በሁለተኛው አጋማሽ የተከላካይ ቁጥር ቀንሰው የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ወደ ሜዳ ቢያስገቡም ፍሬያማ መሆን ቀላል አልሆነላቸውም። ጅማዎች ግን መሪ ሆነው ወደ መልበሻ ክፍል ቢያመሩም ያንን ግብ የማስጠበቅ እና የመከላከል ሀሳብ ሳይኖራቸው ጥሩ እንቅስቃሴ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። ይህ አጋማሽ ለግብ የቀረበ ሙከራ የተስተናገደበት በ58ኛው ደቂቃ ነበር። በዚህ ደቂቃም መሳይ አገኘው፣ ሔኖክ ኢሳይያስ እና ተመስገን ደረሰ ሳጥን ውስጥ ተገኝተው የሞከሩትን ኳስ የግብ ዘቡ አላዛር ማርቆስ ሦስቱንም በጥሩ ቅልጥፍና አምክኗቸዋል። ከደቂቃ በኋላም ፍፁም የከረረ ኳስ ልኮ በድጋሜ አላዛር አውጥቶበታል።

አስደናቂ አቋም እያሳዩ የሚገኙት ጅማዎች በ63ኛው ደቂቃ መሪነታቸውን ወደ ሁለት አሳድገዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም የተገኘውን የቅጣት ምት መስዑድ በድንቅ ሁኔታ ተንጠልጣይ ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ለሱራፌል ዐወል ሲልክለት ተጫዋቹ በግራ እግሩ የፈቱዲንን እግር አስነክቶ ኳሱን መረብ ላይ አሳርፎታል። ወደ ጨዋታው ለመመለስ መጣራቸውን የቀጠሉት የአሠልጣኝ አብርሃም ተጫዋቾች በፍቅረሚካኤል አማካኝነት የሰላ ሙከራ ቢያደርጉም አልቀመስ ያለው አላዛር አውጥቶባቸዋል። በ77ኛው ደቂቃም ዓሊ የሞከረውን ኳስ በግብ ብረቶቹ መካከል የቆመው ዘብ መልሶታል። በቀሪ ደቆቃዎችም ባህር ዳር ያለውን ዕድል ለመጠቀም ቢጥርም ሳይሳካለት ቀርቷል። ሙሉ ደቂቃው ሊጠናቀቅ ሰከንዶች ሲቀሩት ተቀይሮ የገበው ዱላ የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ሦስተኛ ግብ ሊያስቆጥት ተቃርቦ ነበር።  ጨዋታውም ተጨማሪ ጎል ሳይቆጠርበት ተገባዷል።

ውጤቱን ተከትሎ ጅማ ነጥቡን 16 ሲያደርስ ባህር ዳር ከተማ ደግሞ በ25 ነጥብ 15ኛ እና 9ኛ ደረጃ ላይ ፀንተው ተቀምጠዋል።