የአሰልጣኞች አስተያየት | ባህር ዳር ከተማ 0-2 ጅማ አባ ጅፋር

በጅማ አሸናፊነት ከተጠናቀቀው የ21ኛው ሳምንት ቀዳሚ ጨዋታ በኋላ አሰልጣኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አሰልጣኝ አብርሀም መብራቱ – ባህር ዳር ከተማ

ስለጨዋታው

“በመጀመሪያው አጋማሽ እንደአሰላለፋችን ብልጫ ነበረን ብዬ አስባለሁ። ግብም አስቆጥረን ምክንያቱ ግልፅ ባልሆነ ሁኔታ ነው የተሻረብን። ያ ለእኔ ጥሩ ስሜት አልሰጠኝም ፤ ለምን እንደተሻረም አላውቅም። ጥሩ በሆንበት ሰዓት ከቆመ ኳስ የገባብን ጎል እና የገባበት ሰዓት የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሁለት ደቂቃዎች እየቀሩት ነበር። ያ ትንሽ ልጆቻችንን አውርዶብናል ፤ መልበሻ ክፍላችንንም አቀዝቅዞብናል። በሁለተኛው አጋማሽ በተቻለ መጠን በ4-3-3 ወደ ማጥቃት ለመሻገር ሞክረናል። እንደገባን ተደጋጋሚ ሙከራዎች አደርገን ግን ግብ ሊገባ አልቻለም። አሁንም ከቆመ ኳስ የተጠቀሙበትን ግብ አስቆጠሩ። ያ ደግሞ አሁንም ተጫዋቾቻችንን እንዳይነሱ አድርጓቸውል። በአጠቃላይ ይዘነው የገባነው ዕቅድ እና ሜዳ ላይ የተገበርነው የተጣጣመ ነው ማለት አልችልም።

ስለደጋፊዎች

“ረጅም ጉዞ ተጉዘው ጥቂት ሆነው ግን እንደብዙ የደገፉንን ደጋፊዎቻችን እጅግ አድርጌ ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ። ውጤቱ ባለማማሩ ደግሞ ይቅርታ መጠየቅ እፈልጋለሁ። በእርግጠኝነት ወደ ባህር ዳር ስንመነስ እነዚህ የታዩትን ችግሮች ቀርፈን ቡድናችንን ወደነበረበት ደረጃ እንመልሳለን ብዬ ነው የማስበው።

በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ውጤት ለመያዝ ስላላቸው ዕምነት

“እኔ ሙሉ ዕምነት አለኝ። ምክንያቱም በርካታ ጨዋታዎች ላይ በጥቃቅን ስህተቶች ዋጋ እየከፈልን እየወጣን ነው ያለነው። በጎል ሙከራ ፣ በኳስ ቁጥጥር ቁጥሮች እኛ የተሻልን እንደሆንን ነው የሚያሳዩት። ነገር ግን አሁንም ሥነ ልቦናው ላይ ሰርተን በሜዳችን ላይ ዘጠኝ ጨዋታዎች አሉ ያ ማለት 27 ነጥቦች ናቸው። ስለዚህ በአብዛኞቹ ጨዋታዎች በደጋፊያችን ፊት ውጤት እናሳካለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።”

ጊዜያዊ አሰልጣኝ የሱፍ ዓሊ – ጅማ አባ ጅፋር

ስለቡድኑ መነሳሳት

“ከልምምድ ነው የጀመረው እና መነሳሳታቸው በጣም ደስ የሚል ነበር። የሆነ ነገር እንዳለ ነው ከፊታቸው የሚታየው እና ያንን ነገር ነው ሜዳ ላይ የታየው።

ስለተከተሉት አሰልጣኝ

“በአንድ ሁለት ልምምድ ላይ በድግግሞሽ ስንሰራ የነበረው ነው። ያለን አማራጭ ስለሆነ በ 4-3-3 ነው የተጫወትነው ፤ ሦስቱ አጥቂዎች እይመለሱም። ከዚህ በፊት ይመለሱ ነበር ፤ አንዱ ለውጥ ይሄ ነበር። መጨረሻ ላይም ስለደከሙ ነው የቀየርናቸው እንጂ ብዙውን ጊዜ የተጫወትነው በ4-3-3 በማይመለሱ አጥቂዎች ነው። የምንፈልገውን ነገር ተጠቅመን ነው ወደ መከላከሉ ወደ 4-5-1 የቀየርነው። ተጋጣሚ ጎል ላይ እንበዛ ነበር። ከዚህ የበለጠም እናገባ ነበር።

ከዚህ በኋላም በዚህ አጨዋወት ስለመቀጠላቸው

“ግድ ነው በቃ ፤ ይሄ የእኛ ነው። እኛ በዚሁ ነው የምንጀምረው ፤ በዚሁ ነው የምንጨርሰው።

በሊጉ ስለመቆየት ዕድላቸው

“አሁን ሂሳቡን ስንሰራ የትኛውንም ቡድን እንዲህ ነው የምትለው አይደለም። አንደኛም የሆነው ዋንጫ ላይበላ ይችላል ፤ መጨረሻ የሆነውም ላይወርድ ይችላል። ደረጃው አሁን ሳይሆን ጨዋታዎች በቀነሱ ቁጥር ነው ፤ አሁን ግን ውድድሩ ገና ነው።”

ያጋሩ