በረዳት አሰልጣኙ መሪነት መከላከያ ኢትዮጵያ ቡናን ከረታበት የምሽቱ ጨዋታ ፍፃሜ በኋላ አሰልጣኞች ሀሳባቸውን አጋርተዋል፡፡
ዮርዳኖስ ዓባይ – መከላከያ (ረዳት አሰልጣኝ)
ስለ ድሉ ስሜት…?
ደስ ይላል። ያለንበት ደረጃ በጣም ከባድ ቦታ ላይ ነው። በዚህ በአዳማ ውድድራችን ደግሞ በመጨረሻው ጨዋታ ከቡና ጋር ደስ በሚል ጨዋታ ማለት ሙሉ ፍላጎት የተሞላበት የጊዮርጊስ እና የባህር ዳር ጨዋታ ትልቅ መነሳሳት ፈጥሮልን ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ ከእዛ የተሻለ በጎል የታጀበ ውጤት ስላመጣን በጣም ደስተኛ ነን ሁላችንም፡፡
ጨዋታውን ስለ ተቆጣጠሩበት መንገድ…?
ቡና ሊመጡ የሚችሉበትን መንገድ አንድ እና አንድ እናውቀዋለን፡፡ ስለዚህ ከባህርዳር ጨዋታ በኋላ ያለን ጊዜ ውስን ነበር፡፡ ቢያንስ ሦስት ቀኖች ነው ያገኘነው። በእነዚህ ሦስት ቀኖች ከዋና አሰልጣኛችን ጋር ሆነን ለዚህ ጨዋታ ይሆናል ያልነውን ነገር ሰርተናል፡፡ ከእዛ ይበልጥ ደግሞ ሰርተህ አንዳንዴ ሜዳ ላይ የማትጠብቀው ነገር ሊያጋጥም ይችላል፡፡ ግን የተጫዋቾቹ ፍላጎት በጣም ከመቶ ፐርሰንት በላይ ነበር፡፡ ስለዚህ ፍላጎታቸው በመጨመሩ ስራውን ተግባራዊ ሊያደርጉ ችለዋል፡፡
አጥቂው ናቢ ሲይላ ወደ ተጠባባቂነት መውረዱ ለኢትዮጵያ ቡና መዘጋጀታችሁን ያሳያል…?
ትልቁ ነገር እኛ ለማሸነፍ ነው፡፡ እነርሱ የሚመጡበት መንገድ እናውቀዋለን፡፡ እኛ ደግሞ የእነርሱን ደካማ ጎን በምን አይነት መንገድ ነው የምንቆጣጠረው ብለን አስበናል። በዚህም ወደፊት ተጫዋች በማብዛት የተሻለ ነገር ለመስራት ነው። ዛሬ የሰጠናቸው የቤት ስራ በተለማመድነው መሠረት ሰርተዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ፍላጎታቸው በጣም በጣም በፊት ከነበሩት ሁለቱ ጨዋታዎች ከፍተኛ ነበር። ይሄ ውጤታማ ሊያደርጋቸው ችሏል፡፡
አሰልጣኝ ካሣዬ አራጌ – ኢትዮጵያ ቡና
ስለ ጨዋታው…?
የቀረብንበት መንገድ የተለየ ነገር የለውም። ከዚህ በፊት ከምንጫወትበት ግን በመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ከፍተኛ ጫና ነበር፡፡ በእዛ ጫና ውስጥ ሂደቱን ማስቀጠል አልቻልንም፡፡ በተለይ የመጀመሪያው አጋማሽ ላይ ከፍተኛ ድክመት ነበር። በእዛ አጋጣሚ ሦስት ጎሎችን ማስቆጠር ችለዋል፡፡ ከእዚህ በኋላ እንግዲህ ተስፋ የመቁረጥ ነገር አለ፡፡ በእረፍት እንዲነሳሱ እና የሚቀጥለውን አርባ አምስት ደቂቃ ያላቸውን ነገር ተጠቅመው የተሻለ ነገር እንዲያሳዩ ነበር፡፡ መጀመሪያ ግማሽ ላይ የሰራነው ስህተት ዋጋ አስከፍሎናል፡፡
ከተለመደው አጨዋወት ሌላ አማራጭ የጨዋታ መንገድን ስለ አለመከተል…?
አማራጮች አሉ። ግን እነዛን በትክክል የመጠቀም እና ያለ መጠቀም ጉዳይ ነው፡፡ እነሱ ፊት ላይ የመጡት በሦስት ሰው ነው፡፡ በሁለት ሰው ይመጣሉ ብለን ነበር ያሰብነው፡፡ በሦስት ሰው ቢመጡ እንዴት ነው ማድረግ ያለብን አማራጮችን እንዴት ነው መጠቀም የሚለው ከጀርባ ያሉ ተንጠልጣይ ሰዎችን ለመጠቀም ነበር፡፡ይሄንን በትክክል አልተጠቀምንም፡፡
ደጋፊዎች ስላሳዩት ተቃውሞ እና ሜዳ ውስጥ ስለ ፈጠረው ጫና…?
የሚጠበቅ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ ውስጥ የሚጠበቅ ነው፡፡ ውጤቶች ሲጠፉ እንደዚህ አይነት ጫናዎች ይኖራሉ ፤ ከበፊቱም ጀምሮ፡፡ ትጠብቀዋለህ አዲስ ነገር አይደለም፡፡ ትሰማለህ አንዳንድ ተገቢ ያልሆኑ ቃላቶች። ሰው ያለውን ነው የሚሰጥህ፡፡
በአጨዋወቱ ላይ ስለሚታዩ ክፍተቶች…?
የተጫዋች ጥራት ይጠይቃል፡፡ ምንም ጥያቄ የለውም ግን አጠቃላይ ዛሬ 4ለ0 ተሸንፈናል፡፡ ይሄ ለቡድናችን ጥሩ አይደለም፡፡ ግን የመጣንበትን አብዛኛውን ነገር ብትመለከተው ነጥብ የጣልንባቸው ያን ያህል በአጠቃላይ እንቅስቃሴው ብልጫ የተወሰደብን አይደለም፡፡ ከራሳችን አንፃር ስናየው ብዙ ድክመት አለ፡፡ ወደ ኋላ መለስ ብለን ነጥብ የጣልንባቸውን አብዛኛዎቹን ጨዋታዎች ስትመለከታቸው ጨዋታውን መቆጣጠር ባቃተን ሁኔታ ውስጥ አይደለም፡፡ የተጫዋች ጥራት የአዕምሮ ጥንካሬ ይጠይቃል። ብቁ አድርጎ ማቅረቡ ከአሰልጣኝ ጋር የተያያዘ ነው። ከእኛ ውጪ ወደ ሌላ የምትወረውረው አይደለም፡፡