ቅድመ ዳሰሳ | አዳማ ከተማ ከ ሲዳማ ቡና

በነገው ዕለት ከሚደረጉ ተጠባቂ ሁለት መርሐ-ግብሮች መካከል ቀዳሚውን እንዲህ ቃኝተናል።

ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ድል ማግኘት ያልቻለው አዳማ ከተማ በመቀመጫ ከተማው የመጨረሻ ጨዋታው የናፈቀውን ድል አግኝቶ ነጥብ እና ደረጃውን ለማሻሻል እንደሚጥር ሲገመት ሲዳማ ቡናም ከ12 ጨዋታዎች በኋላ በሊጉ መሪ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከደረሰበት ሽንፈት በማገገም በዋንጫ ፉክክሩ ለመዝለቅ ጠንክሮ እንደሚጫወት ይጠበቃል።

በ20ኛ ሳምንት የሊጉ ጨዋታ ከአዲስ አበባ ከተማ ጋር ያለ ግብ አቻ የተለያየው አዳማ ከተማ በዕለቱ ከወትሮ በተለየ ተጋጣሚን ከመጀመሪያው ደቂቃ አንስቶ አስጨንቆ ጫና የማሳደር እንቅስቃሴ ሲያደርግ ተስተውሏል። በበርካታ ጨዋታዎች መጀመሪያ ቀድሞ ግብ እየተቆጠረበት ጨዋታን ማሳደድ ላይ ሲጠመድ የሚታየው ቡድኑም በአዲስ አበባው ጨዋታ በጥሩ ተነሳሽነት ፈጣኖቹን አጥቂዎች በመጠቀም ግቦችን ቀድሞ ለማግኘት ከየአቅጣጫው ሙከራ ሲያደርግ ነበር። በተለይ ከመስመር እየተነሱ እንዲያጠቁ ሀላፊነት ተሰጥቷቸው የነበረው አሜ እና አብዲሳ ተከላካዮችን በመረበሽ የተዋጣለት ጊዜ ቢያሳልፉም ኳስ እና መረብን በማገናኘቱ ረገድ ግን ደካማ ነበሩ። የቡድኑ የማጥቃት መሐከል የሆነው ዳዋ ሁቴሳ ደካማ እንቅስቃሴ ደግሞ የፊት መስመሩን ያዶለዶመው ይመስላል። የነገ ተጋጣሚያቸው ደግሞ እንደ አዲስ አበባ የግብ ዕድሎችን በቀላሉ የማይፈቅድ ስለሆነ የሚገኙ ዕድሎችን በአግባቡ መጠቀም የግድ ይላል። በዚህም ቡድኑ የኳስ ቁጥጥር ድርሻውን በመውሰድ ሜዳውም ወደ ጎን እየለጠጠ የግብ ዕድሎችን ከመስመር ለማግኘት እንደሚውተረተር ይገመታል።

በተጠባቂው ጨዋታ በቅዱስ ጊዮርጊስ አንድ ለምንም የተረታው ሲዳማ ቡና በጨዋታው መጥፎ የሚባል እንቅስቃሴ ባያደርግም በተከላካዮች እና ግብ ጠባቂ የመግባባት ስህተት ግብ ማስተናገዱ ዋጋ እንዳስከፈለው ይታመናል። በኳስ ቁጥጥሩ ረገድ ጥሩ የነበረው ቡድኑም በጊዮርጊስ ሜዳ የነበረውን የኳስ ቅብብል ፍሬያማ አለማድረጉ የታየበት ክፍተት ነበር። ከዚህ በተጨማሪም ጠጣሩን የኋላ መስመር ለማስከፈት የጣረበት መንገድ ደካማ መሆኑ በጨዋታው አንዳች ነገር ይዞ እንዳይወጣ አድርጎታል። አዳማም ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል ጥቂት ግቦችን ያስተናገደ ጠንካራ የተከላካይ ክፍል ባለቤት ስለሆነ የማጥቃት አጨዋወቱን አስተካክሎ መቅረብ ይገባዋል። በቀጥተኛ አጨዋወትም ሆነ ኳስን ይዞ በመንቀሳቀስ ራሱን እንደየ ተጋጣሚው የሚለዋውጠው ሲዳማ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ይገዙ ቦጋለን ከቅጣት መልስ ማግኘቱ ከተከላካይ ጀርባ ለሚደረጉ ሩጫዎች ጠቀሜታ ይሰጠዋል።

በሊጉ ከቅዱስ ጊዮርጊስ በመቀጠል ጥቂት ጨዋታዎችን (ሦስት) በጣምራ የተረቱት አዳማ እና ሲዳማ ቡና የነገውን ጨዋታ እጅግ አጥብቀው ይፈልጉታል። በተለይ አዳማ ከተማ በመቀመጫ ከተማው ጨዋታዎችን እያሸነፈ ስላልሆነ ከፍተኛ ጫና እና ድባቴ ውስጥ የገባ ይመስላል። ከዚህ መጥፎ ስሜት ለመውጣት ደግሞ ጠንካራውን ሲዳማ መርታት አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። ሲዳማም እስከ ሁለተኛ ደረጃ የሚያስመነድገውን ሦስት ነጥብ ለማሳካት ተግቶ መጫወቱ አይቀርም። ይህንን ተከትሎ ፈጣን እና ከሳጥን ሳጥን የሚደረግ የማያቋርጥ እንቅስቃሴ በጨዋታው እንደሚከወን ቀድሞ መናገር ይቻላል።

አዳማ ከተማ በነገው ጨዋታ በጉዳት እና ቅጣት ምክንያት በእርግጠኝነት የሚያጣው ተጫዋች ባይኖርም ባሳለፍነው ሳምንት ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ የወጣው ዳዋ ሁቴሳ መግባት ግን አጠራጣሪ መሆኑን ሰምተናል። ሲዳማ ቡና ደግሞ ከላይ እንደገለፅነው ይገዙ ቦጋለን ከቅጣት መልስ ሲያገኝ ሁሉም ተጫዋቾቹም ጤነኛ እንደሆኑ ተመላክቷል።

ጨዋታው በዳንኤል ግርማይ የመሐል ዳኝነት ሲመራ ታምሩ አደም እና አማን ሞላ ረዳት ኃይለየሱስ ባዘዘው ደግሞ አራተኛ ዳኛ እንደሆኑ ተጠቁሟል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– አዳማ እና ሲዳማ ከዚህ ቀደም 21 ጊዜ ተገናኝተው ሲዳማ ቡና 8 አዳማ ከተማ ደግሞ 5 ጊዜ ያሸነፉ ሲሆን ቀሪዎቹን 8 ጨዋታዎች ደግሞ አቻ ተለያይተዋል። በሀያ አንዱ ጨዋታዎች ሲዳማ 18 አዳማ 17 ጎሎችን አስመዝግበዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ


አዳማ ከተማ (4-3-3)

ጀማል ጣሰው

ጀሚል ያዕቆብ – ቶማስ ስምረቱ – ሚሊዮን ሰለሞን – ደስታ ዮሐንስ

አማኑኤል ጎበና – ዮሴፍ ዮሐንስ – ዮናስ ገረመው

አቡበከር ወንድሙ – አብዲሳ ጀማል – አሜ መሐመድ

ሲዳማ ቡና (4-2-3-1)

ተክለማርያም ሻንቆ

አማኑኤል እንዳለ – ጊት ጋትኩት – ያኩቡ መሐመድ – መሐሪ መና

ዳዊት ተፈራ – ሙሉዓለም መስፍን

ይገዙ ቦጋለ – ፍሬው ሰለሞን – ሀብታሙ ገዛኸኝ

ሳላዲን ሰዒድ