ሪፖርት | ፈረሰኞቹ ወደ ዋንጫ የሚያደርጉትን ግስጋሴ አጠናክረው ቀጥለዋል

በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከቀጥተኛ የዋንጫ ተፎካካሪው ሀዋሳ ከተማ ሦስት ነጥብ እና ጎል ሸምቶ መሪነቱን አጠናክሯል።

ባሳለፍነው ሳምንት በሀዲያ ሆሳዕና የ3ለ1 ሽንፈት ያስተናገደው ሀዋሳ ከተማ ሦስት ነጥብ ካስረከበበት ጨዋታ በጉዳት እና በቅጣት ምክንያት አራት ተጫዋቾችን ለውጦ ወደ ሜዳ ገብቷል። በዚህም በመሐመድ ሙንታሪ፣ ኤፍሬም አሻሞ፣ ፀጋሰው ድማሙ እና ዳዊት ታደሠ ምትክ ዳግም ተፈራ፣ ዳንኤል ደርቤ፣ ሔኖክ ድልቢ እና መስፍን ታፈሰ በአሰላለፉ ተካተዋል። ዘለግ ላሉ ጨዋታዎች ቀዳሚ አሰላለፉን ያለዋወጠው ቅዱስ ጊዮርጊስ በበኩሉ ሲዳማ ቡናን አንድ ለምንም ካሸነፈበት ፍልሚያ ሁለት ተጫዋቾችን ቀይሯል። በለውጦቹም ደስታ ደሙ እና ከነዓን ማርክነህ የሱሌይማን ሀሚድ እና ሀይደር ሸረፋን ቦታ ተክረው ወደ ሜዳ ገብተዋል።

ሀዋሳ ከተማን በአመራርነት ያገለገሉት አቶ ንጉሴ ኑኔን ህልፈት ተከትሎ በአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት የተጀመረው ጨዋታ ገና በጊዜ መሪ ሊያገኝ ነበር። በ2ኛው ደቂቃም ከነዓን ከተከላካይ ጀርባ በመሮጥ የሞከረውን ኳስ ግብ ጠባቂው ዳግም ተፈራ ሲያወጣው የተገኘውን የመዓዘን ምት ተከላካዩ ፍሪምፖንግ ሜንሱ በግንባሩ ወደ ግብነት ለመቀየር ጥሮ ነበር። ወደ ግብ በመድረስ ረገድ የተሻሉት ፈረሰኞቹ በ11ኛው ደቂቃም ሔኖክ ከግራ መስመር አሻምቶ ከነዓን በግንባሩ በሞከረው ኳስ ቀዳሚ ለመሆን ሞክረዋል።

ገና ከጅምሩ ጫናዎች የበረከተባቸው ሀዋሳዎች ወደ ራሳቸው ሜዳ ወረድ ብለው ለመከላከል ቢገደዱም በ17ኛው ደቂቃ ግን ግብ አስተናግደው መመራት ጀምረዋል። በተጠቀሰው ደቂቃም ጊዮርጊስ ያገኘውን የመዓዘን ምት ሔኖክ ሲያሻማው በሩቁ ቋሚ የነበረው እና ለተከላካዮች ፈተና የሆነው ከነዓን ኳስ እና መረብን አገናኝቷል።

ግብ ከተቆጠረባቸው በኋላ በአንፃራዊነት በተሻለ መንቀሳቀስ የጀመሩት ሀዋሳ ከተማዎች የተወሰደባቸውን ብልጫ በማግኘት ወደ ግብ ማምራት ይዘዋል። በተለይ ፈጣኖቹን አጥቂዎች በመጠቀም ቡድኑ ግብ ለማስቆጠር ቢጥርም ጠጣሩን የተከላካይ መስመር በቀላሉ መስበር ተስኖታል። በጭማሪው ደቂቃ ግን መስፍን ከወንድማገኝ የተላከለትን ተከላካይ ሰንጣቂ ኳስ ለመጠቀም ዳድቶ ግብ ጠባቂው ሉክዋጎ ደርሶ አምክኖበታል። መሪው ቡድን ደግሞ ግብ ካገኘ በኋላ ያለ ኳስ ጨዋታውን መቆጣጠር ላይ ተጠምዶ አጋማሹን አገባዷል።

በሁለተኛው አጋማሽ የማጥቃት አጨዋወታቸውን በማስተካከል የቀረቡት ሀይቆቹ ግልፅ የግብ ዕድል አይፍጠሩ እንጂ አስጨንቀው ሲጫወቱ ታይቶ ነበር። ለማጥቃት ነቅለው በወጡበት ሰዓት ግን ሁለተኛ ግብ በፈጣን የመልሶ ማጥቃት አስተናግደው ፈተናቸው አይሏል። በዚህም በ54ኛው ደቂቃ ቸርነት ከአማኑኤል የተቀበለውን ኳስ ወደ ሳጥን እየገፋ ሲሄድ የተነጠቀውን ኳስ ራሱ አማኑኤል አግኝቶት በቀኝ እግሩ ከመረብ ጋር አዋህዶታል።

ሁለተኛው ጎል ያወረዳቸው ሀዋሳዎች ከ60ኛው ደቂቃ በኋላ የነበራቸውን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ እና የማጥቃት መነሳሳት ጊዮርጊስ ተቆጣጥሮ ጨዋታው ቀጥሏል። ሙከራ አልባው ፍልሚያም መሐል ሜዳ ላይ ያመዘነ እንቅስቃሴ ተስተውሎበታል። ሙሉ የጨዋታ ክፍለ ጊዜው ሊጠናቀቅ በጣት የሚቆጠሩ ደቂቃዎች ሲቀሩት ደግሞ የሁለተኛው ጎል ባለቤት አማኑኤል ከግራ መስመር ያሻገረውን ኳስ የአብስራ ለመጠቀም ሲጥር መድሐኔ ደርሶ ሊያፀዳው ሲሞክር ሚዛኑን መጠበቅ ተስኖት ራሱ ላይ አስቆጥሮታል። ጨዋታውም ሦስት ለምንም ተጠናቋል።

ፈረሰኞቹ ድሉን ተከትሎ ነጥባቸውን 47 በማድረስ መሪነታቸውን ሲያጠናክሩ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ተከታታይ ሽንፈት ያስተናገዱት ሀዋሳ ከተማዎች ደግሞ በግብ ልዩነት ከአራተኛ ወደ አምስተኛ ደረጃ በ34 ነጥቦች ሸርተት ብለዋል።