የአሰልጣኞች አስተያየት | ሀዋሳ ከተማ 0-3 ቅዱስ ጊዮርጊስ

ቅዱስ ጊዮርጊስ ሀዋሳን በመርታት መሪነቱን ካጠናከረበት ጨዋታ መጠናቀቅ በኋላ ተጋጣሚ አሰልጣኞች ኃሳባቸውን አካፍለዋል።

አሰልጣኝ ዘርዓይ ሙሉ – ሀዋሳ ከተማ

ስለጨዋታው

“በእንቅስቃሴ ደረጃ ከባለፈው ጨዋታ ይሻላል። ወደ ፊት ስንሄድ ጥሩ ነበርን ፤ ትንሽ ከኋላ መስመራችን ላይ ክፍተቶች ነበሩ። ጥሩ በነበርን ሰዓት ጎሎች በመግባታቸው በተለይ ሁለተኛው ጎል ሲገባ አውርዶናል። በተደጋጋሚ እየተቆጠሩብን ያሉት የቆሙ ኳሶች (እያንዳንዱ ጨዋታ ላይ ተቆጥሮብናል) ባህር ዳር ላይ ለምናደርገው ውድድር ጠንክረን እንሰራለን። ከዛ ውጪ የተከላካይ መስመራችንን ማስተካከል ይኖርብናል። ምክንያቱም ዋጋ ከፍለናል። የአቋቋም ችግር አለ ፣ የማርኪንግ ችግር አለ የመሮጫ ክፍተት ስንሰጥ ነበር። የተከላካይ መስመሩን በሰራንበት መንገድ አላገኘነውም ፤ እናርማለን። ከሽንፈት ስለመጣን ቶሎ ለማገገም ትንሽ ከብዶን ነበር። ቀጣይ ባሉ ጨዋታዎች ግን ቶሎ ወደ አሸናፊነት እንመለሳለን።

ስለቡድኑ የማጥቃት ጥረት

“እንቅስቃሴው ጥሩ ነው። መሀል ላይ ኳሱን ተቆጣጥረው ተጫውተው ወደ ፊትም ቶሎ ቶሎ ይደርሱ ነበር። በዛ መኃል ሁለተኛው ኳስ መግባቱ ልጆቼን አወረዳቸው ማለት ይቻላል። ግን እስከመጨረሻውም ዋጋ ከፍለዋል ፤ ተጋድሎ አድርገዋል በእንቅስቃሴ ደረጃ ዛሬ አልተከፋሁም። ጎሎቹ ቢበዙም እስካሁን ከነበሩት ጨዋታዎች በእንቅስቃሴ የተሻለ ነበር ብዬ ነው የማስበው።”

አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ – ቅዱስ ጊዮርጊስ

ስለቡድኑ እንቅስቃሴ አሳማኝነት

“100% አሳምኖኛል። የሰራነውን ፣ የተነጋገርንበትን እና እንደዕቅድ የያዝነውን ተጫዋቾቼ ጥሩ ነገር ሰርተውልኛል። በዚሁ ለተጫዋቾቼ ምስጋናዬን አቀርባለሁ።

የአዲስ ግደይ ጉዳት ስለፈጠረው ተፅዕኖ

“እንደተጫዋች ማንም ጉዳት ሲደርስበት ቅር ይላል። ያ ስሜት ይሰማሀል ፤ ከአንድ ዓመት ጉዳትም ስለመጣ። የአሁኑ ጉዳት መጠነኛ ይሁን አይሁን ገና አላወኩም። እንደተጫዋች ይጎዳኛል። ግን እንደቡድን ስለሆነ የምንሰራው ስብስባችንም ጥልቀት ያለው ስለሆነ እሱም ወጥቶ አሸንፈን መውጣት ችለናል።

ስለደጋፊዎች አስተዋፅዖ

“ሀዋሳም ፣ ድሬዳዋም ሆነ አሁን አዳማ ላይ እየመጡ ቡድናችንን 12ኛ ሰው በመሆን በጣም በጣም በጣም እየደገፉ ስለሆነ አሁንም ላደረጉልን ነገር በጣም ከልቤ አመሰግናለሁ። ሊጉ እስኪያልቅ አብረውን እንደሚሆኑ እርግጠኛ ነኝ ፤ በዚህ አጋጣሚ እንኳን ደስ ያላችሁ ለማለት እወዳለሁ።”