ቅድመ ዳሰሳ | አርባ ምንጭ ከተማ ከ ወልቂጤ ከተማ

አንድ ነጥብ እና አንድ ደረጃ ለይቷቸው በደረጃ ሰንጠረዡ የተቀመጡት አርባ ምንጭ እና ወልቂጤ ነገ የሚያረጉት ጨዋታ እንደሚከተለው ተዳሷል።

ከዘጠኝ ጨዋታዎች ያለ መሸነፍ ግስጋሴ በኋላ ባሳለፍነው ሳምንት በወቅቱ የሊጉ ዋንጫ ባለ ክብር ፋሲል ከነማ አንድ ለምንም የተረታው አርባ ምንጭ ከተማ ወደ ቀደመ ሪትሙ ለመግባት እና ከደረጃ ሰንጠረዡ አካፋይ ዕድገት ለማሳየት ድልን እያሰበ ወደ ሜዳ ሲገባ ወልቂጤ ከተማም ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች ያጣውን ሦስት ነጥብ በማግኘት የወራጅ ቀጠናው አፋፍ ላይ ከነበረው ድሬዳዋ ከተማ ጋር ሲፋለም ካሳየው ብቃት የተሻለ በማስመልከት በትንሹ ስጋት የሚሆንበትን ቀጠና ለመላቀቅ እንደሚጥር ይታመናል።

የአሠልጣኝ መሳይ ተፈሪ ቡድን በፋሲሉ ጨዋታ እንደ ከዚህ ቀደሙ በጥምር የአራት ተጫዋቾች ግርግዳ (Double block of four) ከኳስ ጀርባ በመሆን ለመጫወት ሲሞክር አስተውለናል። ይህ ሂደት ፋሲልን የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢሰጠውም የግብ ዕድሎችን በአጥጋቢ ሁኔታ መፍጠርን ግን የማይፈቅድ ነበር። መከላከል ከሚፈልገው ከፍተኛ ትኩረት ጋር ተያይዞ ቡድኑ በ62ኛው ደቂቃ ግብ አስቆጠረ እንጂ በጥሩ ሁኔታ ጨዋታውን ያለ ኳስ ለመቆጣጠር ሞክሮ ነበር። ከግቡ በኋላ ግን ከጨዋታው አንዳች ነገር ይዞ ለመውጣት ቢሞክርም ሳይሳካለት ቀርቷል። የነገው የአርባምንጭ ተጋጣሚ እንደ ፋሲል በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ጥራት ያላቸው ተጫዋቾች ያሉት ካለመሆኑ ጋር ተያይዞ ግን በመጠኑ ወደ ላይኛው ሜዳ የሚሄድበትን ድግግሞሽ ሊጨምር ይችላል። በተለይ በፋሲሉ ጨዋታ ጠፍተው የነበረው ረጃጅም ኳሶች እና ሽግግሮች ከተመለሱ ለወልቂጤ ተከላካዮች ፈተና ነው። አማካይ መስመር ላይም የሚከተለው ጉልበት የተቀላቀለበት አጨዋወት በአካላዊ ቁመና እምብዛም ፈርጠም ላላሉት ወልቂጤዎች የራስ ምታት መሆኑ አይቀርም። በዋናነት ግን እንደ ቀደሙት ጨዋታዎች ተሻጋሪ ኳሶች የቡድኑ የነገ መተዳደሪያ መሆኑ አይቀሬ ነው።

በእንቅስቃሴ ረገድ መጥፎ ያልሆነው ወልቂጤ ከተማ ከድሬዳዋ ከተማ ጋር አንድ አቻ ሲለያይ በጊዜ ግብ ማስተናገዱ ጎዳው እንጂ በብዙ መስፈርቶች የተሻለ ነበር። ቡድኑም ኳሱን በተሻለ በመቆጣጠር ከወገብ በታች በቁጥር በዝተው ሲከላከሉ የነበሩትን የድሬ ተጫዋቾች በቆሙ ኳሶች እና ክፍት ጨዋታዎች ለማስከፈት ታትሯል። ቡድኑ በድምሩ ከድሬዳዋ በ10 የላቁ ሙከራዎችን ቢያደርግም በወረዱ የውሳኔ አሰጣጥ ችግሮች እና የስልነት ችግር አጋጣሚዎቹን ወደ ግብነት መቀየር አልቻለም። አርባ ምንጭ ደግሞ እንደ ሌሎቹ ቡድኖች በቀላሉ ግቡን የሚያጋልጥ ስላልሆነ የሚገኙ አጋጣሚዎችን በስልነት መጠቀም አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው። በዋናነት ደግሞ ከአማካይ መስመር ከሚነሱት ኳሶች በተጨማሪ የመስመር ተከላካዮቹ እና አጥቂዎቹ ግጥግጥ ሊል የሚችለውን የተጋጣሚ የኋላ መስመር ለማዘርዘር አይነተኛ ሚና እንደሚወጡ ይታመናል። የቡድኑ አምበል እና አጥቂ ጌታነህ ከበደ ደግሞ ለተከላካዮች የሜዳ ስራ እንደሚያበዛ እሙን ነው።

ከ20 ጨዋታዎች አንድ ጊዜ ብቻ ከአንድ ግብ በላይ በጨዋታ ያስተናገደው አርባ ምንጭ ነገም ለመከላከል ቅድሚያ በመስጠት ኳሱን ትቶ እንደሚጫወት ይገመታል። ወልቂጤ በበኩሉ ጠንካራ ጎኑ የአማካይ መስመሩ ስለሆነ እርሱን የሚገጥሙ ቡድኖች ይህ ጠንካራ ክፍል በአግባቡ ሥራውን እንዳይሰራ የመሐል ሜዳ የተጫዋች ክምችት ብልጫ በመውሰድ ለጠንካራ ጎኑ ማምከኛ ለማበጀት ሲጥሩ ይታያል። ይህንን ተከትሎም መሐል ሜዳ ላይ የሚኖረው የኳስ ጋር እና ውጪ ፍትጊያ ቀልብን የሚስብ ይሆናል።

ባለፈው ሳምንት ጉዳት ላይ የነበረው ማርቲን ኦኮሮ አሁን የተመለሰ ሲሆን ለነገው ጨዋታ ባይደርስም አህመድ ሁሴንም ቀለል ያለ ልምምድ ጀምሯል። ከዚህ ውጪ አሸናፊ ፊዳ በአምስት ቢጫ ካርድ ጨዋታው ያልፈዋል። ወልቂጤ ከተማ በበኩሉ የቅጣት ዜና የሌለበት ሲሆን አማካዩ ሀብታሙ ሸዋለም ግን ቀለል ያለ ጉዳት ላይ መሆኑ ተጠቁሟል። ጫላ ተሺታ ደግሞ ከጉዳቱ ሙሉ ለሙሉ ማገገሙ ተመላክቷል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– አርባ ምንጭ ከተማ እና ወልቂጤ ከተማ በሊጉ ዘንድሮ ነው ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት። በአንደኛ ዙር የመጀመሪያ ግንኙነትም 0-0 በሆነ ውጤት ተለያይተዋል።

ግምታዊ አሰላለፍ

አርባምንጭ ከተማ (4-4-2)

ሳምሶን አሰፋ

ወርቅይታደስ አበበ – ማርቲን ኦኮሮ – በርናንድ ኦቼንግ – ተካልኝ ደጀኔ

ሙና በቀለ – አቡበከር ሸሚል – እንዳልካቸው መስፍን – ፀጋዬ አበራ

ፍቃዱ መኮንን – በላይ ገዛኸኝ

ወልቂጤ ከተማ (4-3-3)

ሮበርት ኦዶንካራ

ተስፋዬ ነጋሽ – ዳግም ንጉሴ – ዋሀብ አዳምስ – ረመዳን የሱፍ

በኃይሉ ተሻገር – አክሊሉ ዋለልኝ – አብዱልከሪም ወርቁ

ያሬድ ታደሠ – ጌታነህ ከበደ – ጫላ ተሺታ