በወራጅ ቀጠናው ፉክክር ውስጥ ተጠባቂ በሆነው ጨዋታ ዙሪያ ተከታዮቹን ነጥቦች አንስተናል።
ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት ከአንድ ነጥብ በላይ ማሳካት ያልቻሉት ድሬዳዋ እና ሰበታ በሰንጠረዡ የታችኛው ክፍል ላይ ባለው ፉክክር ወሳኝ የሆነውን ጨዋታ ያደርጋሉ። ከድሬዳዋ በላይ የተቀመጠው መከላከያ እንዲሁም ከሰበታ በላይ የተቀመጠው ጅማ አባ ጅፋር ትናንት ያሳኳቸው ድሎች የዚህን ጨዋታ ዋጋ ይበልጥ ከፍ የሚያደርጉ ናቸው። ከዚህ ባለፈ ሁለቱም ተጋጣሚዎች ድል ቢቀናቸውም የደረጃ መሻሻልን የሚያገኙበት ዕድል ጠባብ ቢሆንም ከተፎካካሪዎቻቸው ላለመራቅ ግን አዳማን በድል መሰናበት አስፈላጊያቸው ይሆናል።
በደካማ የውድድር ዓመት እዚህ የደረሱት ሁለቱ ቡድኔች በቅርብ ሳምንታት በየፊናቸው ጥሩ መሻሻሎችን አሳይተዋል። በተለይም ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች አራት ነጥቦችን ያሳኩት ድሬዳዋ ከተማዎች ወደ ትክክለኛው ቅርፅ የመጡ ይመስላል። ለኳስ ቁጥጥር ትልቅ ቦታ የነበረው ቡድኑ ራሱን ከአጨዋወቱ ጋር ለማስማማት በርካታ የተጨዋቾች ሽግሽግ በማድረግ ጭምር ሙከራዎችን ቢያደርም ሳይሳካለት ቆይቷል። ሆኖም አሰልጣኝ ሳምሶን አየለ ቡድናቸው በ 3-5-2 ጨዋታውን ጀምሮ እንዳስፈላጊነቱ ለውጦችን እያደረገ ለቀጥተኝነት በቀረበ አጨዋወት መግባቱ ጥሩ ውጤት እያስገኘላቸው ነው። ትርጉም ያላቸው የማጥቃት ሂደቶችን በማሳየት ተጋጣሚን ጫና ውስጥ የሚከትባቸው አጋጣሚዎችም እንዲሁ ቀስ በቀስ መታየት ጀምረዋል።
ከቀናት በፊት አሰልጣኝ ደረጄ በላይን በምክትል አሰልጣኝነት የቀጠረው ሰበታም በድሬዳዋ መጠን መሻሻሎችን ባያሳይም በየጨዋታው ላይ በርንቅስቃሴ ደረጃ መልካም ነገሮችን እያስመለከተን ነው። አሁን አሁን ቡድኑ ውጥ በቋሚ ተሰላፊነት የሚጠቀምባቸውን ተጫዋቾች መለየት መቻሉ ከዚህ ውስጥ የሚካተት ሲሆን በተለይም ከአጥቂው ጀርባ ያሉት አማካዮቹ ከከዚህ ቀደሙ በተሻለ የግብ ዕድሎችን ሲፈጥሩ ይታያል። አጋር አሰልጣኝ ያገኙት አሰልጣኝ ብርሀን ደበሌ ኳስ ይዞ መጫወት በሚያዘወትርባቸው ቡድናቸው ከእንቅስቃሴ ባለፈ ውጤት ይዞ እንዲወጣ ማስቻል ቀጣዩ የቤት ሥራቸው ይመስላል።
በነገው ጨዋታ ድሬዳዋ ከተማ ዳንኤል ደምሴ እና እንየው ካሳሁንን ያለማግኘቱ ጉዳይ ትልቁ ፈተናው እንደሆነ ማንሳት ይቻላል። የቡድኑ የቀኝ መስመር ጥቃት ዋና መነሻ የሆነው እንየውን ማጣት ድሬዳዋ ጥሩ ሚና ተሰጥቶት ካየነው ጋዲሳ መብራቴ የግራ መስመር እንቅስቃሴ የግብ ዕድሎችን እንዲጠብቅ የሚያስገድደው ነው። ሰበታዎች የኳስ ስርጭታቸው መሀል ላይ ያለው ስኬት እንዳይስተጓጎል የዳንኤል በጨዋታው አለመኖር የሚሰጣቸው ጥቅም በቀላሉ የሚታይ አይሆንም። በዚህም የአብዱልሀፊስ ፣ ዱራሳ እና ሳሙኤል ጥምረት በመስመሮች መካከል ጥሩ ክፍተት ሊያገኝ የሚችል ሲሆን የቡድኑ የአጨራረስ ችግር ግን አሁንም እጅግ ተሻሽሎ መምጣት ያለበት ጎኑ ይሆናል።
ድሬዳዋ ከተማ በወልቂጤው ጨዋታ ጉዳት የገጠመው እንየው ካሳሁንን በጉዳት እንዲሁም ዳንኤል ደምሴን በአምስተኛ ቢጫ ካርድ ቅጣት ሲያጣ በሰበታ ከተማ በኩልም ኃይለሚካኤል አደፍርስ ጉዳት ላይ ይገኛል። ሰበታዎች ዮናስ አቡሌን ከጉዳት መልስ ሲያገኙ ዘካሪያስ ፍቅሬ ግን ሙሉ ለሙሉ ከጉዳቱ አልተመለሰም።
የእርስ በእርስ ግንኙነት
– ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን ዘጠኝ ጊዜ ተገናኝተው ሦስት ሦስት ጊዜ ሲሸናነፉ በቀሪ ሦስት ጨዋታዎች ደግሞ ነጥብ ተጋርተዋል። በእስካሁኑ የሊግ ታሪካቸው ሰበታ 7 ድሬዳዋ 6 ጊዜ ኳስ እና መረብን አገናኝተዋል።
ሰበታ ከተማ (4-2-3-1)
ምንተስኖት አሎ
ጌቱ ኃይለማሪያም – በረከት ሳሙኤል – አንተነህ ተስፋዬ – ዓለማየሁ ሙለታ
በኃይሉ ግርማ – ጋብርኤል አህመድ
ሳሙኤል ሳሊሶ – አብዱልሀፊዝ ቶፊቅ – ዱሬሳ ሹቢሳ
ዴሪክ ኒስባምቢ
ድሬዳዋ ከተማ (3-5-2)
ፍሬው ጌታሁን
አውዱ ናፊዩ – መሳይ ጳውሎስ – ያሲን ጀማል
ቢኒያም ጥዑመልሳን – ዳንኤል ኃይሉ – ብሩክ ቃልቦሬ – አብዱርሀማን ሙባረክ – ጋዲሳ መብራቴ
ሙኸዲን ሙሳ – ሄኖክ አየለ