ከረጅም ጉዳት መልስ ፈረሰኞቹን በጥሩ አቋም እያገለለ ባለበት ወቅት ሌላ ጉዳት ያስተናገደው አዲስ ግደይ ስላለበት ሁኔታ ከሶከር ኢትዮጵያ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።
ጉዳት የእግርኳስ ህይወቱን ፈተና ውስጥ እየከተተው የሚገኘው አዲስ ግደይ ከዚህ ቀደም ጉልበቱ ላይ ባጋጠመው ጉዳት ሰባት ሰዓት የፈጀ የቀዶ ጥገና በማድረግ ከህመሙ በማገገም ለአንድ ዓመት ከሚጠጋ ጊዜ በኋላ በአስራ አምስተኛው ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ ከተማ ላይ ጎል በማስቆጠር ራሱን ወደ ሊጉ መመለስ ችሎ ነበር።
በማስከተል በተከታታይ ጨዋታ ጎል በማስቆጠር ወደ ቀድሞ አቋሙ ለመመለስ እየታተረ የሚገኘው አዲስ ግደይ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሀዋሳ ከተማን በረታበት ጨዋታ በመጀመርያው አጋማሽ ጉዳት አስተናግዶ ተቀይሮ ለመውጣት ተገዷል። ሶከር ኢትዮጵያም የጉዳቱ ዓይነት እና አሁን የሚገኝበት የጤንነት ሁኔታ አስመልክቶ ከአዲስ ግደይ ጋር አጭር ቆይታ አድርጋለች።
“እንደፈራሁት አይደለም ፤ ቀላል ነው ፈጣሪ ይመስገን። ትናንት ሃሌሉያ ሆስፒታል በመሄድ ኤም አራ አይ ምርመራ አድርጌአለሁ። ብዙም የከፋ እንዳልሆነ እና ከዚህ ቀደም ከተጎዳሁበት ቦታ ሌላ ቦታ ላይ ስለመሆኑ በምርመራው ውጤት ተገልፆልኛል። ዛሬ ደግሞ ከዚህ በፊት ጉልበቴን የቀዶ ጥገና ያደረጉልኝ ዶ/ር ማሞ ጋር በመሄድ ስለ ኤም አራ አይ ውጤቱ ማብራሪያ ሰጥተውኛል። ብዙ እንደማያሰጋ እና እስከ ሦስት ሳምንት ዕረፍት በማድረግ ፊዚዮቴራፒ እያደረኩ እንድቆይ ነግረውኛል። በሂደት የጉዳቱ መሻሻል እየታየ ወደ እንቅስቃሴ የምገባ ይሆናል።”