ወልቂጤ ከተማ ከሦስት ጨዋታዎች በኋላ አርባ ምንጭ ከተማን በማሸነፍ ከሦስት ነጥብ ጋር ታርቋል።
በፋሲል ከነማ አንድ ለምንም ተሸንፎ የዛሬውን ጨዋታ የቀረበው አርባምንጭ ከተማ ሦስት ነጥብ ካስረከበበት ፍልሚያ በቅጣት ምክንያት የሌለው አሸናፊ ፊዳን ጨምሮ በላይ ገዛኸኝ እና ኤሪክ ካፓይቶን በኡቸና ማርቲን፣ ፍቃዱ መኮንን እና ሀቢብ ከማል ሲተካ ባሳለፍነው ሳምንት ከድሬዳዋ ከተማ ጋር አንድ አቻ የተለያየው ወልቂጤ ከተማ ደግሞ ፋሲል አበባየሁ እና ጫላ ተሺታን አሳርፎ አበባው ቡጣቆ እና አክሊሉ ዋለልኝን ወደ ሜዳ አስገብቷል።
ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በ18ኛ ሳምንት አርባምንጭ ከተማ ከሀዲያ ሆሳዕና ጋር አራት አቻ ሲለያይ ሐት-ሪክ ሰርቶ በ72ኛው ደቂቃ ተጎድቶ የወጣው አህመድ ሁሴን በጨዋታው ያልተቀበለውን ኳስ ከአልቢትሩ ማኑኤ ወልደፃዲቅ (በዛን ጨዋታ ዳኛ የነበሩት ኤፍሬም ደበሌ መሆናቸው ልብ ይሏል) ተረክቧል።
ቀዝቀዝ ብሎ የጀመረው ጨዋታ ለግብ የቀረበ ሙከራ የተመለከትነው በ11ኛው ደቂቃ ነበር። በዚህም ግራ እግሩን አጉልቶ እንዲጠቀም በቀኝ መስመር የተሰለፈው እና እየሰበረ እንዲገባ ሀላፊነት የተሰጠው ሀቢብ ከማል ከሳጥኑ ውጪ ጥብቅ ኳስ ሞክሮ ዒላማውን ስቶበታል።
ቶሎ ቶሎ ኳስ መነጣጠቅ እና አካላዊ ጉሽሚያዎች በበረከቱበት ጨዋታ እስከ ሩብ ሰዓት ድረስ ብቻ ሦስት የጭንቅላት ላይ ጉዳቶች (ፍቃዱ፣ ፀጋዬ እና ዮናስ) ተስተናግደውበታል።
ሳቢ ያልነበረው ጨዋታ ቀጣዩን ሙከራ ያስተናገደው በ31ኛው ደቂቃ ነበር። በዚህም በግራ መስመር ወደ አርባምንጭ የግብ ክልል ያመሩት ወልቂጤዎች በአብዱልከሪም ወርቁ አማካኝነት የሞከሩትን ኳስ የግቡ ቋሚ ከግብነት ታድጎታል። ከዚህ ደቂቃ በኋላም ወደ ላይኛው ሜዳ መትመማቸውን የቀጠሉት ሠራተኞቹ በ38ኛው ደቂቃ የፍፁም ቅጣት ምት አግኝተው መሪ ሆነዋል። ጌታነህ ከበደ ራሱ ከሳጥን ውጪ የመታውን ኳስ ማርቲን ኦኮሮ በእጁ ሲነካው የተገኘውን የፍፁም ቅጣት ምት በጥሩ ሁኔታ ከመረብ ጋር አዋህዶታል።
አጋማሹ ተጠናቆ በተጨመረው ደቂቃ ግብ ጠባቂው ሳምሶን ከተፈቀደለት ክልል ውጪ ኳስ በእጁ ተጫውቷል በሚል ከወደ ቀኝ የተሰጠውን የቅጣት ምት አበባው ቡጣቆ ሲመታው ወርቅይታደስ በግንባሩ ጨርፎት ወልቂጤ ሁለተኛ ጎል አግኝቷል። የመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜም ሁለት ለምንም ተጠናቋል።
አንድም ዒላማውን የጠበቀ ሙከራ በመጀመሪያው አጋማሽ ያላደረገው አርባምንጭ ገና ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በስድስተኛ ደቂቃ ሦስተኛ ግብ አስተናግዷል። በተጠቀሰው ደቂቃም ረመዳን ከግራ መስመር መሬት ለመሬት ወደ ሳጥን የላከውን ኳስ ማርቲን ኦኮሮ በሚገባ ማፅዳት ተስኖት ጌታነህ አግኝቶት በግራ እግሩ ለራሱ ሁለተኛ ለቡድኑ ሦስተኛ ጎል አድርጎታል።
ጨዋታው ከእጃቸው የወጣባቸው አዞዎቹ ባላቸው ደቂቃ ከባዱን ፈተና በመጋፈጥ በጨዋታው ያላቸውን ነብስ ለማቆየት የማጥቃት ባህሪ ያላቸው ተጫዋቾችን ቀይረው ቢያስገቡም ግልፅ የግብ ማግባት ዕድል መፍጠር ተስኗቸዋል። ቡድኑ ከወትሮ በተለየ የኳስ ቁጥጥር ብልጫ ቢወስድም በ66ኛው ደቂቃ ሌላ ግብ ሊያስተናግድ ነበር። በዚህም ከመዓዘን ምት የተሻማውን ኳስ በቅድሚያ ጌታነህ ከዛም ጫላ እና ዋሀቡ አከታትለው ወደ ግብነት ለመቀየር ቢሞክሩትም ሳምሶን እና ተከላካዮች ተረባርበው አውጥተውታል።
ጨዋታው 73ኛው ደቂቃ ላይ ሲደርስ ፀጋዬ የአርባ ምንጭን የመጀመሪያ ለግብ የቀረበ ጥቃት ሞክሮ ለጥቂት ወጥቶበታል። 77ኛው ደቂቃ ላይ ደግሞ በላይ ከግራ መስመር የተሻገረውን ኳስ ራሱን ነፃ አድርጎ በመጠበቅ ለመጠቀም ጥሮ ዳግም ራሱን ለጉዳት ዳርጎ አምክኖበታል።
አሁንም ኳስን ከመረብ ጋር ለማገናኘት መታተት የያዙት የአሠልጣኝ መሳይ ተጫዋቾች ከሁለት ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ በአንዱዓለም አስናቀ አማካኝነት ከርቀት እጅግ ለግብ የቀረበ ኳስ ልከው ቁመታሙ ግብ ጠባቂ ሮበርት ኦዶንካራ በጥሩ ቅልጥፍና አውጥቶባቸዋል። በቀሪ ደቂቃዎች ቡድኑ የማስተዛዘኛ ጎል እንኳን ለማግኘት ቢጥርም ሳይሳካለት ጨዋታው ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ሦስት ነጥብ እና ሦስት ጎል የሸመተው ወልቂጤ ከተማ በ28 ነጥቦች ከ11ኛ ደረጃ ወደ 7ኛ ደረጃ ሲመነደግ በውድድር ዓመቱ ለሁለተኛ ጊዜ ከአንድ ጎል በላይ ያስተናገደው አርባ ምንጭ ከተማ ደግሞ በ26 ነጥቦች 10ኛ ደረጃን ተቆናጧል።