በሕንድ አስተናጋጅነት ለሚደረገው ከ17 ዓመት በታች ሴቶች የዓለም ዋንጫ የ3ኛ ዙር ማጣሪያ የመልስ ጨዋታን ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በደቡብ አፍሪካ አቻው 1ለ0 ቢሸነፍም በድምር ውጤት 3ለ1 በማሸነፍ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፉን አረጋግጧል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አቶ ኢሳይያስ ጂራ እና የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባላት ተገኝተው በተከታተሉት ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ የመጀመሪያዎቹን አስር ያህል ደቂቃዎች ደቡብ አፍሪካዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ወስደው የነበረ ቢሆንም በሂደት ግን የአሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ ልጆች ኳስን በመቆጣጠር ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል በመስመር በኩል በይበልጥ ባደላ አጨዋወት ለመጫወት ጥረት አድርገዋል፡፡ 8ኛው ደቂቃ ላይ ማሳባታ ሞታቦ ከግራ መስመር በረጅሙ ወደ ግብ ክልል ያሻገረችውን ኳስ ዞይ አስቤላ በግንባር ገጭታ ግብ ጠባቂዋ አበባ አጀቦ በቀላሉ መያዝ የቻለችሁ የጨዋታው ቀዳሚ ሙከራ መሆን ችላለች፡፡
ቀዝቀዝ ባለ እና ዝናባማ በሆነ አየር ታጅቦ የቀጠለው ጨዋታ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከሁለቱ የመስመር ኮሪደሮች በእየሩሳሌም ወንድሙ እና ቁምነገር ካሳ አማካኝነት ተደጋጋሚ ጥቃትን ለመፈፀም ቢቃጡም የመጨረሻ ውሳኔያቸው ተዳክሞ ታይቷል፡፡ 28ኛ ደቂቃ ላይ መሀል ሜዳ ላይ ልዩነት ለመፍጠር ጥረት የምታደርገው እሙሽ ዳንኤል ወደ ግራ ወዳዘነበለ ቦታ አመቻችታ ያቀበለቻትን ቁምነገር በቀጥታ ወደ ግብ ስትመታ የግቡ ቋሚ ብረትን ነክቶ የወጣባት የትንንሾቹ ሉሲዎች ቀዳሚው ሙከራ ሆኗል፡፡
የኢትዮጵያ የኳስ ንክኪ በማቋረጥ ረጃጅም ኳስን ለመጠቀም የሚሞክሩት ደቡብ አፍሪካዎች ያገኟትን አንድ ኳስ በቀላሉ ወደ ግብነት ለውጠው ቀዳሚ ሆነዋል፡፡ 37ኛው ደቂቃ ላይ አማካይዋ ትሁን አየለ ማፖ ሞሎጋዲ ላይ የሰራችውን ጥፋት ተከትሎ የሜዳው አጋማሽ መስመር ላይ ወደ ቀኝ መስመር ከተጠጋ ቦታ የተገኘውን ቅጣት ምት አጥቂዋ አድሪሌ ሚቤ በቀጥታ አክርራ ወደ ጎል ስትልከው የግብ ጠባቂዋ አበባ አጀቦ ስህተት ታክሎበት ጥቁር እና ነጭ እንስቶችን ወደ መሪነት አሸጋግራለች፡፡ ከጎሏ መቆጠር ሁለት ደቂቃዎች በኋላ ምላሽ ለመስጠት በፈጠነ እንቅስቃሴ በመልሶ ማጥቃት በቁምነገር ካሣ አማካኝነት ኢትዮጵያ ያለቀለትን ዕድል አግኝታ በግብ ጠባቂዋ ብሪድጌት ካጎሞትሶ ተመልሶባት ወደ መልበሻ 1ለ0 በሆነ ውጤት አምርተዋል፡፡
ከእረፍት መልስ የተዳከመ እንቅስቃሴን ማየት ብንችልም ኢትዮጵያ በኳስ ቁጥጥር ፣ በረጃጅም ተጫውቶ ግብ ለማግኘት ደቡብ አፍሪካ ያሳዩት የጨዋታ መንገድ ነበር፡፡ በመስመር እና መሀል ሜዳ ላይ በዝቶ በመገኘት በፍጥነት ተጫውቶ ጎል ለማግኘት በፈጠነ እንቅስቃሴ ለመጫወት የኢትዮጵያ ከ17 ዓመት በታች ቡድን ቢሞክርም ጎል ሊያገኙ ግን አልቻሉም ፡፡ በተለይ እሙሽ ዳንኤል በቀላሉ የምታገኛቸውን ዕድሎች ወደ ጎልነት አለመለወጧ ዋጋ ያስከፈለ ሆኗል፡፡ 60ኛው ደቂቃ ላይ ከግብ ጠባቂዋ ጋር አንድ ለአንድ ተገናኝታ ያመከነችው እና 71ኛው ደቂቃ እሙሽ የግል ጥረቷን ተጠቅማ በቀጥታ ወደ ጎል ስትልክ ቁምነገር አግኝታው አስቆጠረች ሲባል ግብ ጠባቂዋ ብሪጅጌት ያወጣችባት ሌላኛው የጠራች ዕድላቸው ነበረች፡፡
በቀሩት ደቂቃዎች ደቡብ አፍሪካዎች ወደ ግባቸው ሸሸት በማለት ለማስጠበቅ በሚመስል አጨዋወት ሲዘልቁ በአንፃሩ አሰልጣኝ እንዳልካቸው ጫካ የተጫዋች ለውጥን በማድረግ ግብ ለማግኘት ቢያልሙም ተጨማሪ መቆጠር ሳይችል በደቡብ አፍሪካ 1ለ0 አሸናፊነት ተደምድሟል፡፡ ከሜዳዋ ውጪ ከ15 ቀናት በፊት 3ለ0 አሸንፋ የመጣችው እና በዛሬው ጨዋታ ሽንፈትን ያስተናገደችው ኢትዮጵያ በድምር ውጤት 3ለ1 በመርታት ግብፅን ትላንት 4ለ0 ከረታችው ናይጄሪያ ጋር በመጨረሻው ዙር ማጣርያ የምትገናኝ ይሆናል፡፡