ቅድመ ዳሰሳ | አዲስ አበባ ከተማ ከ ሀዲያ ሆሳዕና

የ21ኛ ሳምንት የመጨረሻ ቀን የመጀመሪያ ጨዋታን በሚከተለው መልኩ ዳሰነዋል።

በአዳማ ከተማ የሚደረጉት የሊጉ ጨዋታዎች ነገ ጥሩ ፍክክር እንደሚደረግባቸው በሚታሰቡ ሁለት መርሐ-ግብሮች ይቋጫሉ። ቀዳሚው ጨዋታ ደግሞ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት እየጣረ የሚገኘው አዲስ አበባ ከተማን ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ካልተሸነፈው ሀዲያ ሆሳዕና ያገናኛል። የመዲናው ክለብ አዲስ አበባ በአንፃራዊነት ከበድ ካሉት ፋሲል ከነማ እና አዳማ ከተማ ጋር ተጫውቶ ያገኘውን አንድ ነጥብ ወደ ሦስት ነጥብ አሳድጎ ከቀጠናው ለመውጣት እንደሚታትር ሲገመት በአዳማ ከተማ እስካሁን አንድም ሽንፈት ያላስተናገደው ሀዲያ ሆሳዕና ደግሞ በከተማው ያለውን አፈፃፀም አሳምሮ ነጥቡን ሰላሳ’ዎቹ ውስጥ ለማስገባት እንደሚጥር ይገመታል።

በእስካሁኖቹ 20 ጨዋታዎች በድምሩ 40 ነጥቦችን የጣለው አዲስ አበባ ከተማ በእንቅስቃሴ ደረጃ በየጨዋታው የሚያሳየው ነገር ከውጤቱ በተቃራኒ ነው። ኳስን መስርቶም ሆነ በፈጣን ሽግግር ተጋጣሚን ለማጥቃት የማይቦዝነው ቡድኑ ከፊት መስመር ያለበት የስልነት ችግር ዋጋ እያስከፈለው ነው እንጂ አሁን ከሚገኝበት ደረጃ ተመንድጎ በተቀመጠ ነበር። ባሳለፍነው ሳምንትም በመቀመጫ ከተማው ከሚጫወተው አዳማ ከተማ ጋር ተጫውቶ ነጥብ ሲጋራ የተሻለ ዒላማውም የጠበቀም ሆነ ያልጠበቀ ሙከራዎችን አድርጎ ወቷል። እርግጥ በጨዋታው ጫናዎች የበዙበት ጊዜዎች ቢኖሩም በዕለቱ ድንቅ በነበሩት ተከላካዮች አዩብ እና ቴዎድሮስ እንዲሁም የግብ ዘብ ዳንኤል ታግዞ ግቡን ሳያስደፍር ወጥቷል። ከላይ እንደገለፅነው ግን የተገኙ ዕድሎችን የመጠቀም ጉዳይ በጨዋታው የታየበት ከፍተኛው ክፍተት ነበር። የቡድኑ የፊት መስመር አጥቂዎች ላይ የሚነሳው የመረዳዳት ችግርም መቀረፍ እንደሚገባ ምስክር የሰጠ ጨዋታ ነበር። የሆነው ሆኖ በረጅሙ የተላኩ አንደኛ ኳሶችን ለማሸነፍ እና ሁለተኛ ኳሶችን ለማመቻቸት የተመቸው ሪችሞን አዶንጎ እንዲሁም ከመስመር እየተነሱ አጥበው የሚጫወቱት እንዳለ እና ፍፁም ነገ ለሀዲያ ተከላካዮች ፈተና እንደሚቸሯቸው መናገር ይቻላል።

አዳማ ከተማ የተመቸው የሚመስለው ሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታዎች ላይ ያለው ተፅዕኖ ጨዋታ በጨዋታ እያደገ ይገኛል። በተለይ የቡድኑ ችግር የነበረው ግብ የማስቆጠር ክፍተት ባለፉት ሦስት ጨዋታዎች እጅግ ተሻሽሏል። ዘጠኝ ግቦች በተቆጠሩበት ያለፉት ሦስት ጨዋታዎችም በድምሩ 56 የግብ ማግባት ሙከራዎችን አድርጎ ከሜዳ ወጥቷል። ይህ ደግሞ የፊት መስመሩ ምን ያህል እየተሳለ እንደመጣ ይጠቁማል። በመጨረሻው የሀዋሳ ጨዋታ ደግሞ ኳስ እና ጨዋታን በመቆጣጠር፣ አደገኛ ቦታዎች ላይ የሚደረጉ ፍልሚያዎችን በማሸነፍ እና የተጋጣሚን ስህተት አጎልቶ በመጠቀም የተሻለ ነበር። በተለይ ደግሞ የቡድኑ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ የሆነው ሀብታሙ ብቃት ለተከላካዮች የራስ ምታት እየሆነ ይገኛል። ከሀብታሙ በተጨማሪም በነፃ ሚና ከአማካይ መስመር እየተነሳ ወደ ተጋጣሚ ሳጥን የሚገባው ፍቅረየሱስም የመጨረሻ ኳሶቹ እና ግብ ፊት ያለው ዐይን አስገራሚ ነው። በነገውም ጨዋታ ሁለቱ ተጫዋቾች ለቡድኑ ውጤት አስገኚ ሊሆኑ ይችላሉ።

የአዲስ አበባ ከተማ ማገር የሆነው የተከላካይ አማካይ ቻርለስ ሪባኑ የቡድኑን ሚዛን በመጠበቅ ያለው ተሳትፎ እጅግ ከፍተኛ ነው። በመከላከሉ ለተከላካዮች ሽፍን በመስጠት በማጥቃቱም የጥቃቶች መነሻ ሲሆን የሚስተዋለው ተጫዋቹ ነገም ለቡድኑ የሚሰጠው ግልጋሎት ይጠበቃል። ሀዲያ ሆሳዕና ግን ሜዳውን አስፍቶ መጫወት የሚያዘወትር ቡድን ስለሆነ በመስመር የሚሰነዘሩ ጥቃቶችን በጥሩ ልዕልና ላይ ተገኝቶ መመከት ይገባዋል። ሀዲያ ተሻሽሏል ባልንባቸው የመጨረሻ አምስት ጨዋታዎች ከወገብ በታች የተወሰኑ ስህተቶችን ሲፈፅም ይታያል። በተለይ በመከላከሉ ረገድ መጠነኛ የመዘናጋት እና የአቋቋም ስህተቶችን ሲሰራ ይስተዋላል። ለዛም ይመስላል በ5ቱ ጨዋታዎች ሰባት ጎሎችን ያስተናገደው። ይህ ስህተት ነገም ከተደገመ ደግሞ ለአዲስ አበባዎች ምቾች የሚሰጥ ስለሆነ ሊጎዳ ይችላል።

አዲስ አበባ ከተማ በቅጣትም ሆነ በጉዳት ምክንያት የሚያጣው ተጫዋች የሌለ ሲሆን ሀዲያ ሆሳዕና ግን የግብ ዘቡ ሶሆሆ ሜንሳን ብቻ በጉዳት ምክንያት አያገኝም።

ጨዋታው በአባይነህ ሙላት የመሐል ሙስጠፋ መኪ እና ተስፋዬ ንጉሴ ረዳት እንዲሁም ሔኖክ አክሊሉ አራተኛ ዳኝነት እንደሚከወን ታውቋል።

እርስ በርስ ግንኙነት

– አዲስ አበባ እና ሀዲያ ሆሳዕና የነገው የሊጉ ግንኙነታቸው ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ዘንድሮ በአንደኛው ዙር ባደረጉት የመጀመሪያ ጨዋታ አዲስ አበባ ከተማ አንድ ለምንም በሆነ ውጤት አሸንፎ ነበር።

ግምታዊ አሰላለፍ


አዲስ አበባ ከተማ (4-3-3)

ዳንኤል ተሾመ

አሰጋኸኝ ጴጥሮስ – ቴዎድሮስ ሀሙ – አዩብ በቀታ – ሮቤል ግርማ

ሙሉቀን አዲሱ – ቻርለስ ሩባኑ – ኤሊያስ አህመድ

እንዳለ ከበደ – ሪችሞንድ ኦዶንጎ – ፍፁም ጥላሁን

ሀዲያ ሆሳዕና (3-5-2)

ያሬድ በቀለ

ግርማ በቀለ – ፍሬዘር ካሣ – ሔኖክ አርፌጮ

ብርሃኑ በቀለ – አበባየሁ ዮሐንስ – ተስፋዬ አለባቸው – ፍቅረየሱስ ተወልደብርሀን – ኢያሱ ታምሩ

ዑመድ ኡኩሪ – ሀብታሙ ገዛኸኝ